ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን በእስራኤል ጥቃት ለተገደሉባት ወታደራዊ አዛዦቿ ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት አካሄደች
ኢራን ለ12 ቀናት በዘለቀው የእስራኤል ግጭት የተገደሉ ወታደራዊ አዛዦች እና የኒውክሌር ሳይንቲስቶችን ጨምሮ 60 ለሚሆኑ ዜጎቿ ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት እያካሄደች ነው።
በኢራን ሰንደቅ ዓላማ የተሸፈኑ የአስክሬን ሳጥኖች እንዲሁም የተገደሉ የጦር አዛዥ ምስሎች በበርካታ ነዋሪዎች ታጅቦ ወደ ማዕከላዊ ቴህራን ኤንሄላብ አደባባይ ተምሟል።
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እየተፈጸሙ ካሉ መካከል የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሆኑት መሐመድ ባግሔሪ አንዱ ናቸው።
በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት መሐመድ በጠቅላይ ኤታማዦር ሹምነታቸው የአገሪቱን ጦር እንዲሁም የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዋነኛ መሪ ነበሩ።
ጥቁር ልብስ የለበሱ በርካታ ኃዘንተኞች መፈከሮችን በማሰማት፣ የኢራንን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ እና የተገደሉ ሰዎችን ምስል ይዘው በአደባባዩ ላይ ታይተዋል።
በዛሬው ዕለት ቀብራቸው የሚፈጸመው ሌላኛው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ የነበሩት ሆሴን ሳላሚ ናቸው።
በእስራኤል ጥቃቶች ከተገደሉት በርካታ የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መካከል የአገሪቱ የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ኃላፊ የነበሩት ፍሬይዱን አባሲ እንዲሁም በቴህራን የሚገኘው የእስላሚክ አዛድ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት መህዲ ቴራንቺ ቀብራቸው ይፈጸማል።
ሌሎች በዚህ ግጭት የተገደሉት ጎላሚሊ ራሺድ የኢራን ጥምር ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያስተባብረው የአብዮታዊ ዘቡ ካህታም አል አንቢያ የተሰኘው ማዕከላዊ ዋና መስሪያ ቤት ኃላፊ አንዱ ናቸው።
በተጨማሪም የአብዮታዊ ዘቡ የኤሮስፔስ ኃይል አዛዥ የነበሩት እና የሃገሪቱን የሚሳኤል ፕሮግራም የመሩት አሚር አሊ ሃጂዛዴህ ሌላኛው ናቸው።
አሜሪካ ከእስራኤል ጋር ተሰልፋ በኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ የአስራ ሁለት ቀናቱ ግጭት ቆሟል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ድጋሚ ጥቃት ለመፈጸም "ፍጹም" እንደማያወላውሉ በትናንትናው ዕለት ተናግረዋል።
በዋይት ሃውስ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ትራምፕ ኢራን ዩራንየም በከፍተኛ ደረጃ ማበልጸጓ ስጋት ፈጥሯል የሚል የተረጋገጠ መረጃ ከደረሳቸው "ያለምንም ጥያቄ" አገሪቷ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል።
ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ወድሟል በሚለው አቋማቸው አሁንም እንደጸኑ ነው።
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የአሜሪካ ጥቃት የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ለማደናቀፍ ያቀደውን ስኬት አላገኘም" በማለት ከሰሞኑ ገልጸዋል።
ኻሜኒ በዚሁ መግለጫቸው ላይ በእስራኤል እና አሜሪካ ላይ ድል ተቀዳጅተናል ያሉ ሲሆን ፤ለዚህ ምላሽ የሰጡት ትራምፕ "በጦርነት የተመታችው ኢራን 'ጠቅላይ መሪ' እየተባለ የሚጠራው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እንዴት በሃሰት ከእስራኤል ጋር ያለውን ጦርነት አሸንፌያለሁ ይላል" ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስፍረዋል።
ትራምፕ "የተጠለለበትን ትክክለኛ ቦታ አውቀው ነበር። እስራኤል ወይም የአሜሪካ ጦር ኃይሎች እንዲገድሉት አልፈለኩም" ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም "ከአስቀያሚ እና አሳፋሪ ሞት አዳንኩት። አመሰግናለሁ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሚል ምላሽ አልጠብቅም" ብለዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው ትራምፕ የኻሜኒን "ክብር ዝቅ የሚያደርግ" አስተያየቶች ከመስጠት እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል።
"ፕሬዚዳንት ትራምፕ እውነተኛ የሆነ ስምምነት ላይ መድረስ የሚፈልግ ከሆነ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን አክብሮት በጎደለው ድምጸት መናገር ሊያቆም ይገባል" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው አጋርተዋል።
አክለውም "የሚሳኤሎቻችንን ኃያልነት ያልቻለው የእስራኤል መንግሥት ወደ 'አባቱ' [አሜሪካ] ከመሮጥ ውጭ ምንም አማራጭ እንደሌለው ታላቁ እና ኃያሉ የኢራን ህዝብ ለዓለም አሳይቷል። ይህ ህዝብ ዝልፊያ እና ማስፈራቶችን ዝም ብሎ አይመለከትም" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሜሪካ በአገራቸው በፈጸመችው ጥቃት የኒውክሌር ይዞታዎች ላይ "ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን" አምነዋል።