ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ሰው ሁኑ፤ ሰውነት ይቀድማል" ታላቁ የእስልምና ሃይማኖት አባት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር
የቀድሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ባደረባቸው ህመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥቅምት እሁድ 9/2018 ዓ.ም. አርፈዋል።
ከኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች መካከል በተለየዩ እምነት ተከታዮች ዘንድ ተወዳጅነት እና ተከባሪነት ያተረፉት የሐጂ ሙፍቲ ዑመር ኅልፈት ከተሰማ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሐዘን መግለጫ በስፋት እየተጋራ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም በሃይማኖት አባቱ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን እየገለጹ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ኅልፈት የተሰማትን ሐዘን "የሰላም የፍቅር፣ የአንድነት ተምሳሌት አባት ነበሩ። በአገልግሎት ዘመናቸው ለአገር አንድነትና ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጡ፣ የርህራሄ እና የፍቅር ሰው ናቸው" በማለት የገለጸች ሲሆን በመላው ኢትዮጵያውን ዘንድ በመልካም ሰብዕናቸውና ሲታወሱ ይኖራሉ ብላለች።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የተወለዱት ግንቦት 21/1929 ዓ.ም. በወቅቱ አጠራር ወሎ በሚባለው ክፍለ ሀገር ነው።
ከልጅነታቸው ጀምሮ የእስልምና ትምህርቶችን እየተከታተሉ ያደጉት ሐጂ ዑመር ወደ አዲስ አበባ የመጡት በደሴ ጀምረውት የነበረውን የሃይማኖት ትምህርት ለመቀጠል ነበር።
ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከተለያዩ መምህራኖቻቸው የሚፈልጉትን የሃይማኖት ትምህርት ከተከታተሉ በኋላም በአንዋር መስጂድ እና በመስጂድ ኑር እንዲያስተምሩ ተመደቡ።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር በተለያዩ ስፍራዎች በመመረጥም ሙስሊሙን ሕብረተሰብ በቅንነትና ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል።
በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችን ከመሠረቱት ሰዎች መካከል አንዱ የነበሩት ሐጂ ዑመር ኢድሪስ፣ በ1967 የምክር ቤቱ አባል እና የዑለማ ሊቀመንበር በመሆን አገልግለዋል።
ከዚያ በኋላም በተከታታይ ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሠርተዋል።
ከ25 ዓመታት በፊት በአመራር ላይ የነበረው የአዲስ አበባ የመጅሊስ ምክር ቤት ማንኛውንም ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች በመላው አገሪቱ ቢመጣ የመመለስ አቅም እንዳላቸው በመግለጽ የሙፍቲነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል።
ከ10 ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ በሙስሊሞች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት እና በእውቀት ላይ ተመሥርቶ ለመፍታት የበኩላቸውን ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን የእምነቱ መሪዎች ይናገራሉ።
በኢህአዴግ የአመራር ዘመን በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ አስነስቶ የነበረው ከሃይማኖቱ ተወካዮች እስር ጋር በተያያዘ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ሐጂ ዑመር የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በእስር በነበሩበት ጊዜ ከሌሎች የሙስሊም መምህራን እና አባቶች ጋር በመሆን ለአራት ዓመታት መንግሥትን ከኮሚቴዎቹ ጋር ለማስታረቅ እንዲፈቱ እና መንግሥትም ይቅር እንዲል ብዙ ጥረት አድርገዋል።
በ2011 ዓ.ም. ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሆነው ተመርጠው አገልግለዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ጠቅላይ ምክር ቤቱ ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ የማድረግ ትልቅ ሥራን ማከናወናቸውን የሃይማኖቱ አባቶች ይጠቅሳሉ።
ይህ ሥራቸው ምክር ቤቱ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሥልጣን እና ኃላፊነት የሰጠ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች መጅሊስ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ክብር እንዲሁም ተሰሚነት ከፍ ያደረገ ነው በሚል ይነገራል።
ብዙዎች ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ "ዕድሜ ዘመናቸውን ለአንድነታችን የተጉ፣ የአገር ዋርካ ባለውለታ" ሲሉ ይገልጿቸዋል።
ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ አንድነት መጠናከር ዘመናቸውን በሙሉ መልፋታቸውን የሚገልጹ ወገኖች የነበራቸው ጥረት ሁልጊዜ የማኅበረሰቡን ሰላምና አብሮነትን ማስጠበቅ ነበር ይላሉ።
ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ከማስተማር ባሻገር ከ50 በላይ ሃይማኖታዊ መጻሕፍትን ጽፈዋል፤ ቅዱስ ቁርዓንን ተርጉመዋል፤ የቁርዓን ትርጉም ሥራቸውም በሲዲ ተሠራጭቷል፡፡
ከ50 ዓመታት በላይ በዘለቀ የአገልግሎት ዘመናቸውም ቅዱስ ቁርዓንን ከ300 ጊዜ በላይ በትርጉም ያስተማሩ ሲሆን፣ ከጻፏቸው መጻሕፍት አንዱ የሕትመት ብርሃን አግኝቶላቸዋል።
የሃይማኖት አባቱ በተለያዩ ጊዜያት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በአገሪቱ አንጋፋ ከሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ2011 ዓ.ም. የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ መሞት በኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ እና በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ጥልቅ ሐዘንን ፈጥሯል።
"እሳቸውን ማጣት እጅግ ከባድ መሆኑን" እና "በእጅጉ ትልቅ ሀዘን ነው" በማለት በርካቶች የገለጹ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "በአመራር ዘመናቸው የተለያዩ ወገኖች ወደ አንድነት አንዲመጡ እና የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት በሕግ እውቅና እንዲኖረው" ባደረጉት አስተዋጽኦ ሁሌም አንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ በበኩላቸው "እጅግ ትሁት፣ የአገር ወዳድ ምልክት በሁሉም ዘንድ የሚወደዱ፣ የሚደመጡ እና የሚከበሩ አባታችን ነበሩ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተቀዳሚ ሙፍቲ የሕዝበ ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆኑ በምክራቸውና በተግሳፃቸው በመላው ኢትዮጵያውያን መወደድን እና ክብርን የተጎናፀፉ ታላቅ አባት እና መሪ፣ የአገር ሽማግሌ እና ዋርካ በመሆን ኢትዮጵያዊያንን በእምነት፣ በጎሳ እና በብሔር የማይነጣጥሉ አባት እንደነበሩ ጉባኤው አስታውሷል።
በአንድ ወቅት ለመላው ኢትዮጵያውያን "ሰው ሁኑ፤ ሰውነት ይቀድማል" በሚለው ምክራቸው እና ተግሳጻቸው እንደሚታወሱም ጉባኤው ጠቅሷል።
ተቀዳሚ መፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የቀድሞው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ በመሆን አገልግለዋል።
የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር የቀብር ሥነ ሥርዓት ሰኞ ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት ይፋዊ የሽኝት ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ በ10 ሰዓት ይፈጸማል።