ከዜሮ በታች የአየር ሁኔታ በተመዘገበባት ኢትዮጵያ የቀጣይ ቀናት ትንበያዎች ምን ያሳያሉ?

እየተገባደደ ባለው የበጋ ወቅት በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከዜሮ በታች ዝቅተኛ የሙቀት መጠን መመዝገቡን ብሔራዊ የሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲቲዩት አስታወቀ።

የተቋሙ የሚቲዮሮሎጂ ትንበያ ቅድመ ማሰጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው ተሾመ በዚህ ወቅት እየተስተዋለ ያለው የቅዝቃዜ መጠን በሚቀጥሉት ቀናትም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሌሊት እና የማለዳ ቅዝቃዜ የበረታው ባለፉት ቀናት ከሳይቤሪያ በመነሳት ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ደረቅ እና ቀዝቃዛ አየር እየተስፋፋ እና እየተጠናከረ በመምጣቱ እንደሆነ ምክትል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት በጥቂት የምሥራቅ አማራ፣ በመካከለኛ እና በምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ደጋማ አካባቢዎች የሌሊት እና የማለዳ ቅዝቃዜ ተስተውሏል።

በእነዚህ አካባቢዎች የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ5 ዲግሪ ሴልሽየስ በታች ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በተለይም በጨለንቆ የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከዜሮ በታች -1 ዲግሪ ሴልሽየስ ሆኗል።

"ከዜሮ በታች ሲሆን በረዶ ይሆናል ማለት አይደለም። በትሮፒካል ክልል ስለምንኖር በረዶ ባይሆንም የቀኑ ዝቅተኛ መጠን -1 ሆኖ ይመዘገባል" ብለዋል።

በሚቀጥሉት ቀናትም ይህ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን እንደሚቀጥል ትንበያዎች እንደሚያመለክቱ ዶ/ር አሳምነው አስጠንቅቀዋል።

በምሥራቅ የአማራ አካባቢዎች ማለትም በደብረ ብርሃን፣ በባቲ፣ በኮምቦልቻ፣ ጉጉፍቱ፣ አምባ ማሪያም፣ በምሥራቅ የአገሪቷ ክፍሎች፣ በአዲስ አበባ፣ በሐረር እና ባሌ ሮቤ የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ5 ዲግሪ ሴልሽየስ በታች ሆኖ እንደሚመዘገብ ተተንብይዋል።

ዝቅተኛ የሙቀት መጠን በሚመዘገብብት ወቅት በሰው፣ በእንስሳት እንዲሁም በግብርና ምርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያስከትል ስለሚችልም ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ዶ/ር አሳምነው ተሾመ መክረዋል።

"የአየር ሁኔታ በአንድ አገር ብቻ የሚከሰት አይደለም" ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ በሌሎች አህጉሮች፣ ውቅያኖሶች እንዲሁም የብሶች ላይ የሚፈጠር ሁኔታ በአንድ አገር ውስጥ ያለውን የአየር፣ የሙቀት እና የዝናብ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አብራርተዋል።

በመሆኑም በዚህ በበጋ ወቅት ከሩሲያ ሳይቤሪያ በመነሳት ወደ አገሪቱ የሚገባው ደረቅ እና ቀዝቃዛ አየር ሁኔታ እየተስፋፋ ሲመጣ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች የሌሊት እና የማለዳ ቅዝቃዜ ይስተዋላል ብለዋል።

"በበጋ ወቅት የደመና ክምችት ስለማይኖር ከመሬት ላይ የሚነሳው የፀሐይ ኃይል በቀጥታ ወደ ከባቢ አየር ውስጥ በሚሄድበት ወቅት ከፍተኛ ቅዝቃዜ ያይላል" ብለዋል።

በሚቀጥሉት ቀናትም ሦስተኛው የበጋ ወር ታኅሣሥ በአዲስ አበባ ከተማ የቀኑ የሌሊት እና የማለዳ የቅዝቃዜ መጠን የሚቀጥል ሲሆን፣ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን 7 ዲግሪ ሴልሺየስ ሆኖ እንደሚመዘገብ ትንበያዎች እንደሚያሳዩ ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የደመና ሽፋን እየተስተዋለ በመሆኑ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚስተዋል ትንበያዎች ቢያመለክቱም የቅዝቃዜ መጠኑ ግን ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በመሆኑም ማኅበረሰቡ የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን በመከታተል አለባበሱን እና አመጋገቡን ከአየር ሁኔታው ጋር አስማምቶ ሕይወቱን እንዲመራ መክረዋል።

ኢትዮጵያ እያንዳንዳቸው አራት ወራት ያላቸው ክረምት፣ በጋ እና በልግ የተባሉ ሦስት ወቅቶች አሏት።

በጋ የሚባለው ከጥቅምት እስከ ጥር የሚዘልቀው ሲሆን ይህ ለደቡብ አጋማሽ ኢትዮጵያ ማለትም ለሶማሌ ክልል፣ ለደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ ስፍራዎች ማለትም ለጉጂ እና ቦረና፣ ለሲዳማ ክልል፣ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል፣ ለጋሞ ጎፋ፣ ለኮንሶ እና ለደቡብ ኦሞ ሁለተኛው የዝናብ ወቅታቸው ነው።

ሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ግን በጋ ላይ ደረቅ፣ ፀሐያማ እና ነፋሻ ናቸው።

የአየር ሁኔታ ከዜሮ በታች አንድ ዲግሪ ሴሊሺየስ በሚሆን ጊዜ ቅዝቃሴ የሚኖር ሲሆን ውሃ በጣሙን ስለሚቀዘቅዝ ከሌላው ጊዜ የተለየ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን ሁኔታው ንፋስ እና እርጥበት ካልተጨመረበት በስተቀር ከፍተኛ የሆነ ቅዝቃዜ ላይፈጠር ይችላል።

እንዲህ ያለው የአየር ሁኔታ በሚያጋጥምበ ጊዜ ከወትሮው በተለየ የሰውነትን ሙቀት የሚጠብቅ አለባበስ ሊያስፈልግ እና ጥንቃቄን ማድረግ ያስፈልጋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ የረጉ የውሃ አካላት ቀዝቅዘው ወደ በረዶነት ሊቀየሩ ይችላሉ። በተጨማሪም የመኪና መንገዶችን እና የሰዎች መረማመጃ ድንጋያማ ጥርጊያዎችን አንሸራታች እንዲሆኑ ያደርጋል።

በቤቶች ጣሪያ፣ በመስኮቶች፣ በመኪኖች እና በሳር መስኮች ላይ ቅዝቃዜው ጤዛን ይፈጥራል።