እስራኤል በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ የሚገኙ 19 አዲስ ሠፈራዎችን አጸደቀች

በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ የሚደረጉ ሠፈራዎችን ይበልጥ ለማስፋፋት እየሠራ ያለው የእስራኤል መንግሥት፤ በግዛቱ ለተገነቡ 19 አዲስ ሠፈራዎች ዕውቅና ሰጠ።

ከእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ጋር በመሆን ይህንን ዕቅድ ለአገሪቱ የደኅንነት ምክር ቤት ያቀረቡት ቀኝ አክራሪው የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች ናቸው። ሚኒስትሩ ውሳኔው የአገረ ፍልስጤም ምሥረታን ለማገድ የተላለፈ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት፤ እስራኤል በዌስት ባንክ የምታካሂዳቸው ሰፈራዎች ሕገ ወጥ ተደርገው ይቆጠራሉ።

ሳዑዲ አረቢያ እርምጃውን ተቃውማለች። የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ደግሞ የእስራኤል "እረፍት አልባ" ሠፈራ የማስፋፋት እርምጃ ውጥረትን የሚያቀጣጥል፣ ፍልስጤማውያን መሬቱን እንዳያገኙ የሚያግድ እንዲሁም የሉዓላዊት አገረ ፍልስጤምን እውን መሆን አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።

መስከረም 2016 ዓ.ም. በጋዛ ጦርነት ከተጀመረበት አንስቶ በዌስት ባንክ የሚፈጸመው ጥቃት በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። የሠፈራ መስፋፋት የእስራኤል ወረራ የሚያጠናክር እና የሁለት አገር መፍትሔን እውን መሆን ያቀጭጫል የሚል ስጋት አይሏል።

የሁለት አገር መፍትሔ የሚለው ሐሳብ፤ ዌስት ባንክ እና የጋዛ ሰርጥን የያዘች እንዲሁም ምሥራቅ እየሩሳሌምን ዋና ከተማዋ ያደረገች ፍልስጤም እንደ አገር የምትመሠረትበትን ዕቅድ የሚያመለክት ነው። ይህ ዕቅድ በአውሮፓውያኑ 1967 ከተካሄደው የአረብ-እስራኤል ጦርነት በፊት በነበረው የድንበር መስመር ላይ የተመሠረተ ነው።

የአሁኑ የእስራኤል መንግሥት በ2022 ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ የሚጸድቁ ሠፈራዎች ብዛት በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ከዚህ ቀደም ፈቃድ ሳያገኙ የተመሠረቱ ሠፈራዎችንም የማጽደቅ ሂደት አስጀምሯል።

በቅርቡ የተሰጠው ውሳኔ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ የጸደቁ ሠፈራዎች ብዛት 69 እንዳደረሰው የፋይናንስ ሚኒስትሩ ስሞትሪች ተናግረዋል።

የደኅንነት ምክር ቤት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ የተባበሩት መንግሥትታት የእስራኤል ሠፈራዎች ከአውሮፓውያኑ 2017 ወዲህ ባልታየ መጠን መጨራቸውን ከተናገረ ከቀናት በኋላ ነው።

እስራኤል፤ ባለፉት አሥርት ዓመታት ባልታየ ሁኔታ ሰኔ ላይ በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ የሚገኙ 22 አዲስ ሠፈራዎችን አጽድቋል።

በተጨማሪም የአገሪቱ መንግሥት በእየሩሳሌም እና በማሌ ኡዱሚም መካከል በሚገኙ ሠፈራዎች ላይ ከ3,000 በላይ ቤቶች እንዲገነቡ ነሐሴ ላይ አጽድቋል። ይህ ዕቅድ ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ደረጃ በደረሰበት ውግዘት ምክንያት እንዲቆም ተደርጎ የነበረ ነው።

ስሞትሪች፤ ዕቅዱ "የአገረ ፍልስጤም ሐሳብን እንደሚቀርብረው" በወቅቱ ተናግረው ነበር።

በዌስት ባንክ እና በምሥራቅ እየሩሳሌም ባሉ 160 ገደማ ሠፈራዎች ውስጥ ከ700 ሺህ ገደማ ሠፋሪዎች እንደሚኖሩ ጸረ ሠፈራ ቡድን የሆነው የእስራኤሉ 'ፒስ ናው' መረጃ ያመለክታል። ሠፈራ የሚፈጸመው ፍልስጤማውያን የወደፊት አገራቸውን መመሥረት በሚፈልጉበት መሬት ላይ ነው።

የሠፈራዎች መስፋፋት፤ ይህ አካሄድ የሁለት አገር መፍትሔ ያቀጭጫል በማለት የሚሟገቱትን የአረብ አገራትን አስቆጥቷል። በወረራ የተያዘው ዌስት ባንክ ተቆርጦ ሊወሰድ ይችላል የሚል ስጋትም አጭሯል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው እስራኤል ይህንን ዓይነቱን እርምጃ እንዳትወስድ አስጠንቅቀዋል። ፕሬዝዳንት ከታዋቂው ታይም መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ ይህ እርምጃ የሚፈጸም ከሆነ እስራኤል የአሜሪካን ድጋፍ እንደምታጣ ተናግረዋል።

መስከረም ላይ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ እና ካናዳ ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ሰጥተዋል። ምንም እንኳ ውሳኔ ከትእምርታዊነት የማያልፍ ቢሆንም በመንግሥታቱ ፖሊሲ ላይ ትልቅ ለውጥ አድርጓል።

እስራኤል፤ ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መሰጠቱት ተቃውማለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ የፍልስጤም አገርነት "መቼም አይፈጸምም" ብለዋል።