የሴኔጋል የሴቶች የቅርጫት ኳስ ቡድን ቪዛ በመከልከሉ በአሜሪካ ሊያደርገው የነበረው ልምምድ ተሰረዘ

የፎቶው ባለመብት, Basket Sénégal
የሴኔጋል የሴቶች የቅርጫት ኳስ ቡድን አባላት ቪዛ በመከልከላቸው በአሜሪካ ሊያደርጉት የነበረው ልምምድ መሰረዙን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ።
የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኦስማን ሶንኮ፣ ቡድኑ በመዲናዋ ዳካር "ሉዓላዊ " እና "ምቹ በሆነ" ሥፍራ ልምምድ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ስፖርተኞቹ ቪዛ መከልከላቸው የተሰማው አሜሪካ ሴኔጋልን ጨምሮ በ25 ተጨማሪ የአፍሪካ አገራት ላይ አዲስ የጉዞ እገዳ ለማጣል ማቀዷ በተሰማበት ወቅት ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አሜሪካ የ12 አገራት ዜጎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ እገዳ የጣለች ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሰባቱ በአፍሪካ የሚገኙ አገራት ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ አሜሪካ ሦስት የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ በሌሎች ሰባት አገራት ዜጎች ላይ ከፊል የጉዞ እገዳ ጥላለች።
የሴኔጋል የቅርጫት ኳስ ቡድን በሚቀጥለው ወር በአይቮሪ ኮስት ለሚካሄደው የ2025 የሴቶች አፍሮባስኬት ውድድር ለመዘጋጀት በአሜሪካ ለ10 ቀናት ልምምድ ለማድረግ አቅዶ ነበር።
ሆኖም አምስት ተጨዋቾች እና ሰባት ባለሥልጣናት ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ያቀረቡት የቪዛ ማመልከቻ ተቀባይነት ሳያገኝ እንደቀረ የቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን ገልጿል።
ይህም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርን አስቆጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሶንኮ ሐሙስ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ በተጋራ መግለጫቸው " በርካታ የሴኔጋል የሴቶች የቅርጫት ኳስ ቡድን አባላት ቪዛ መከልከላቸው ሲነገረኝ በአሜሪካ ለ10 ቀናት ሊያደርጉት የነበረው የዝግጅት ልምምድ ወዲያው እንዲሰረዝ ለስፖርት ሚኒስቴር ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ።" ብለዋል።
የቡድኑ አባላት ለምን ቪዛ እንደተከለከሉ ግልጽ አይደለም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በቢቢሲ ተጠይቀው የቪዛ መረጃዎች በአሜሪካ ሕግ ምስጢራዊነታቸው የተጠበቀ በመሆኑ በግለሰቦች የቪዛ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ሴኔጋል በአፍሪካ ምርጥ የሚባል የሴቶች የቅርጫት ኳስ ቡድን አላት።በአፍሮባስኬት ውድድር ላይ በተደጋጋሚ ፍፃሜ ላይ የደረሰች ሲሆን ተጫዋቾቿን በአሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በግብፅ ባሉ ከፍተኛ ሊጎች ታሰለጥናለች።
አሁን ላይ ቡድኑ ቪዛ መከልከሉም ብዙዎችን አስገርሟል።
በቅርቡ በሌሎች አገራት ላይ ሊጣል ስለታቀደው የጉዞ ገደብ በዝርዝር የሚያስረዳውና ሾልኮ የወጣው መረጃ አገራት አሜሪካ ገደቡን ለመጣል ምክንያት ነው ያለቻቸውን ችግሮች እንዲያስተካክሉ የ60 ቀናት ቀነ ገደብ እንደተሰጣቸው ያስረዳል።
አሜሪካ እንደ ችግር ከጠቀሰቻቸው ምክንያቶች መካከልም ከተሰጠው ጊዜ በላይ መቆየት፣ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ትብብር አለማድረግ እና ከሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ እንዲሁም ፀረ ሴማዊነት ወይ ፀረ አሜሪካዊ ድርጊት ላይ መሳተፍ የሚሉት ይገኙበታል።
አዲስ የጉዞ እገዳ እንደምትጥል ማቀዷን ተከትሎም የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ዜጎች በአሜሪካ ከተሰጣቸው ጊዜ በላይ እንዳይቆዩ እና የተፈቀደላቸውን የመቆያ ጊዜ እንዲያከብሩ አሳስበዋል።
ሚኒስቴሩ ምንም እንኳን አዲስ የጉዞ ገደብ ሊጣልባቸው ከታቀደው አገራት ዝርዝር ውስጥ ሴኔጋል መካተቷን በተመለከተ በቀጥታ አስተያየት ባይሰጥም፤ከአሜሪካ አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ቱጋር በበርካታ አገራት ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ለአሜሪካ ሊያቀርቡ በሚችሉት የኃይል እና የብርቅዬ ማዕድናት ስምምነቶችን ሊያደናቅፍ ይችላል ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ግን የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶች እና በአንዳንድ አገራት የሚታየው ከተፈቀደ ጊዜ በላይ የመቆየት ችግር መስተካከል እንዳላባቸው ይገልጻል።















