ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተከታታይ ድሎችን ያስመዘገቡት ትራምፕ የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ለመሆን ተቃርበዋል
ቅዳሜ ዕለት ተከታታይ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ውድድርን ያሸነፉት ዶናልድ ትራምፕ፣ የፓርቲው ዕጩ ለመሆን ተቃርበዋል።
ከድላቸው በኋላም ተቀናቃኛቸውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ስደተኞች ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ እንዲገቡ መንገድ ከፍተዋል ሲሉ ከሰዋቸዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሚዙሪ፣ ሚቺጋን እና አይዳሆ የውክልና ድምጽ ሰጪዎችን [ካውከስ] ድጋፍ ሙሉ በሙሉ በማግኘት አሸነፈዋል።
የ77 ዓመቱ ትራምፕ በቨርጂኒያ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ለደጋፊዎቻቸው እንደተናገሩት “ለሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆነው ለመቅረብ እንደሮኬት እየተተኮስኩ ነው” ብለዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት ዕጩ መሆናቸውን እንደሚያረጋግጡም ይጠበቃል።
በውድድሩ የቀሩት ብቸኛ ተቀናቃኛቸው የቀድሞዋ የደቡብ ካሮላይና ገዢ ኒኪ ሄሊ እስካሁን አንድም ድል አላስመዘገቡም።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው ከሆነ በሚዙሪ እና በአይዳሆ የሚገኙትን ሁሉንም ውክልናዎች እና በሚቺጋን የቀሩትን ሁሉ ትራምፕ እንደሚያሸንፉ ገምቷል።
በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ልዑካን ትራምፕ አሳማኝ በሆነ መንገድ ካሸነፉበት የመጀመሪያ ውድድር በኋላ በዚህ ሳምንት መጀመሪያም የሚፈልጉትን ድል አግኝተዋል።
ልዑካን የሚባሉት በፓርቲያቸው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ ክልላቸውን ወይም አካባቢያቸውን የሚወክሉ እና ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ማን እንደሚሆን የሚወስኑ ናቸው።
ትራምፕ እስካሁን 247 የሪፐብሊካን ተወካዮችን ድጋፍ ማግኘታቸውን ሲቢኤስ ዘግቧል። ሄሊ 24 ብቻ ነው ያሳኩት።
ቅዳሜ ዕለት በቨርጂኒያ ዋና ከተማ ሪችመንድ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ትራምፕ በአካቢው የስብሰባ ማዕከል ሲናገሩ ለመስማት ለብዙ ሰዓታት ተሰብስበው ቆይተዋል።
15 ግዛቶች ፕሬዝዳንታዊ ዕጯቸውን በሚመርጡበት በዕለተ ማክሰኞ “ትልቅ ድል” በማስመዝገብ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ለመሆን ከጫፍ የሚያደርሳቸውን ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ቃል ገብተዋል።
“ዛሬ የማይታመኑ ቁጥሮችን አግኝተናል” ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
በቨርጂኒያ እና ቀደም ሲል ደግሞ በሰሜን ካሮላይና በተካሄደው ዝግጅት ላይ ያደረጉት ንግግር በአብዛኛው ያተኮረው በዩናይትድ ስቴትስ-ሜክሲኮ ድንበር ላይ ስላለው የፍልሰተኞች ጉዳይ ነው።
ይህም የደጋፊዎቻቸው ትልቅ ትኩረት መሆኑ ታይቷል። ቅዳሜ ዕለት ሃሳባቸውን ለቢቢሲ የሰጡ ከደርዘን በላይ የሚቆጠሩ የትራምፕ ደጋፊዎች ጉዳዩ ቀዳሚ ስጋታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
እአአ በ2018 ልጇን ሺንን ፌንታኒል የተባለ መድኃኒትን ከመጠን በላይ በመውሰድ ያጣችው ሻሮን ሮበርትስ “ከቁጥጥር ውጭ” የሆነ ድንበር ሌሎች ቤተሰቦችም በተመሳሳይ የሚወዷቸውን እንዲያጡ ያደርጋል የሚል ስጋት ጭሮባታል።
“እኔ ድጋፌ 100 በመቶ ለትራምፕ ነው። ምክንያቱም እሱ እነዚህን ድንበሮች ይዘጋቸዋል” ስትል ተናግራለች።
ባይደን እና ትራምፕ ባለፈው ሳምንት የድንበር አካባቢዎችን ከጎበኙ በኋላ፣ ትራምፕ በቀጥታ ችግሩን ወደ ባይደን በመውሰድ እንደገና ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ሆን ብለው ስደተኞችን ከሜክሲኮ ድንበር እንዲሻገሩ እያበረታቱ ነው የሚል የሴራ ሃሳብ በመሰንዘር ትራምፕ ባይደንን ከሰዋል።
“ባይደን እና ግብረ አበሮቹ የአሜሪካን ሥርዓት በማፍረስ፣ የእውነተኛ የአሜሪካ መራጮችን ፍላጎት ውድቅ በማድረግ እና ትውልድን የሚቆጣጠሩበት አዲስ የኃይል መሠረት ማቋቋም ይፈልጋሉ። በሚቀጥለው ምርጫ ድምጽ እንዲሰጡ ለማስመዝገብ እየሞከሩ ነው” ብለዋል ትራምፕ።
ለዚህም ከባይደን የምርጫ ዘመቻ ቡድን ፈጣን ምላሽ ተሰጥቶታል። የቡድኑ ቃል አቀባይ አማር ሙሳ የሁለትዮሽ የኢሚግሬሽን ሕግን በመጥቀስ “ትራምፕ በድጋሚ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ፍትሃዊ እና ከባድ የሆነውን የድንበር ደኅንነት ሕግን ገድሏል ከሚለው እውነታ የአሜሪካን ሕዝብ ለማዘናጋት እየሞከረ ነው። ምክንያቱም ይህ ዘመቻውን ይረዳል ብለው ስለሚያምኑ ነው” ብለዋል።
ቅዳሜ ዕለት የተለቀቀው አዲስ የኒውዮርክ ታይምስ እና የሲዬና የሕዝብ አስተያየት እንዳመለከተው 48 በመቶ አሜሪካውያን መራጮች ትራምፕን እንደሚደግፉ ገልጸው፤ ለአሁኑ ፕሬዝዳንት ድጋፋቸውን የሚሰጡት 43 በመቶ ናቸው። ከሁለቱ ወገኖች መካከል በባይደን ላይ ጠንካራ ቅሬታዎችን መኖራቸው ተለይቷል።
በሪችመንድ ሰልፍ ላይ ትራምፕ ወደ ምርጫው ጣቢያ ጠቁመው ደጋፊዎቻቸው ማክሰኞ ዕለት ግልጽ “መልዕክት እንዲያስተላልፉ" አሳስበዋል። ባገኙት ድጋፍም “አከብራችኋለው” ብለዋል።
በምርጫው ግን 45 በመቶ የሚሆኑት መራጮች ሄሊን ሲመርጡ 35 በመቶዎቹ ደግሞ የወቅቱን ፕሬዝዳንት እንደሚደግፉ አሳይተዋል።
“በአጠቃላይ ምርጫ ጆ ባይደንን በሁለት አሃዝ አሸንፌአለሁ። ትራምፕ ግን ከዚህ ውጪ ናቸው” ሲሉ ሄሊ የሕዝብ አስተያየቱ ውጤት ይፋ ተደረጎ ብዙም ሳይቆይ ተናግረዋል።
ትራምፕ በሪችመንድ ባደረጉት ንግግር ሄሊን ላይ አነጠጥረው ሪፐብሊካኖች በኅዳር ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርበዋል።