ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ እና የመሐል ዳኛው ፖል ቲየርኒ ተደጋጋሚ ግጭት
ትናንት እሁድ በተደረገ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 34ኛ ሳምንት ጨዋታ ሊቨርፑል ባለቀ ሰዓት ባስቆጠረው ግብ ቶተንሃምን አሸንፏል።
ጨዋታውን 4 ለ 3 በሆነ ጠባብ ውጤት ካሸነፉ በኋላ የሊቨርፑሉ አለቃ የርገን ክሎፕ የመሐል ዳኛው ፖል ቲየርኒ በቡድናቸው ጋር የሆነ ችግር ያለበት ይመስላል ሲሉ ተናግረዋል።
ጨዋታው በሊቨርፑል የበላይነት ሊጠናቀቅ ነው ሲባል ሪቻርለሰን ቡድኑን አቻ ማድረግ ቢችልም ከ99 ሰከንድ በኋላ ዲያጎ ጆታ ባስቆተረው ጎል ቀያዮቹ ሦስት ነጥቡን ጠቅልለው ወስደዋል።
ስፐርሶች አቻ የሆኑበት ኳስ የተገኘበት ቅጣት ምት መስጠት አልነበረበትም ሲሉ በማለት አራተኛውን ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ወደ አራተኛው ዳኛ መሮጥ ጀምረው ነበር።
ሆኖም ዳኛው ጋር ከመድረሳቸው በፊት እግራቸውን ተጎድተው ሩጫቸውን ሲያቆሙ በቴሌቪዥን መስኮት ታይተዋል።
ደስታቸውን ከገለጹ በኋላ የማስጠንቀቂያ ካርድ በሐል ዳኛው ተመዞባቸዋል።
“ከቲየርኒ ጋር ብዙ ታሪክ አለን። በእርግጥ እሱ በእኛ ላይ ያለውን ነገር አላውቅም። እሱ ችግር የለብኝም ቢልም እውነት አይመስለኝም” ሲሉ ክሎፕ ለስካይ ስፖርት ተናግረዋል።
“እንዴት እንደሚመለከተኝ አልገባኝም። እንግሊዝ ውስጥ ማንም ሰው እነዚህን ሁኔታዎች ግልጽ ማድረግ የለበትም። በእውነቱ ውስብስብ እና ለመረዳት አስቸጋሪ ነው” ብለዋል።
“ቢጫ ካርዱን ሲሰጠኝ የተናገረው ነገር ጥሩ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
የፕሪሚየር ሊጉ የዳኞች አስተዳደር ኮሚቴ በበኩሉ “ቡድናቸው ከቶተንሃም ሆትስፐር ጋር ካደረገው ጨዋታ በኋላ የርገን ክሎፕ የሰጡትን አስተያየት ኮሚቴው ያውቃል” ብሏል።
“በፕሪሚየር ሊጉ ዳኞች በሁሉም ጨዋታዎች የሚያደርጉት ንግግር የሚመዘገቡበት ሥርዓት አለ።”
“የዛሬው የመሐል ዳኛው ፖል ቲየርን ድምጽ ሙሉ በሙሉ ከገመገምን በኋላ ለሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ቢጫ ካርድን የሰጠበትን ጨምሮ በሕጋዊ መልኩ መሥራቱን እናረጋግጣለን።”
“ስለዚህ የቲየርኒ ድርጊት አግባብ አይደለም የሚለውን ማንኛውንም አስተያየት አጥብቀን እንቃወማለን” ብሏል።
የቀድሞ የእንግሊዝ የፊት መስመር ተጫዋች አለን ሺረር ለቢቢሲ ማች ኦቭ ዘ ዴይ “ፖል ቲየርኒ የሊቨርፑሉን ዲዮጎ ጆታን ከሜዳ ሊያወጣው ይችል ነበር። እሱ [ክሎፕ] ግን ይህን ለመጥቀስ ብዙም አልቸኮለም” ሲል ተናግሯል።
“የርገን ክሎፕ ወደ አራተኛው ዳኛ ሲሄድ ቢጫ ካርድ ብቻ በማግኘቱ ዕድለኛ ነው። እሱ እንዲህ ሲያደረግ የመጀመሪያው አይደለም” ብሏል።
ጉዳታቸውን በተመለከተ ክሎፕ ለቢቢሲ ስፖርት እንደተናገሩት “ምኔን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም። ግን ተቀጥቻለሁ።”
“ደስታዬን ለመግለጽ ዞርኩኝ ምክንያቱም አራተኛው ዳኛ በጨዋታው ሙሉ ጊዜ ምንም አላጠፋም” ብለዋል።
ጉዳቱ ክሎፕ ደጋፊዎቻቸው ፊት ደስታቸውን ከመግለጽ አላገዳቸውም።
ጀርመናዊው ክሎፕ ከመሐል ዳኛው ፖል ቲየርኒ ጋር ያላቸው አለመግባባት ለረዥም ጊዜ የቆየ ይመስላል።
እአአ በ2020 ሊቨርፑል ከአስቶን ቪላ ጋር ባደረገው ጨዋታ ጆርጆዮ ዋይናልደም ላይ የተሠራውን ጥፋት ማለፋቸውን በመግለጽ ክሎፕ አጋጣሚውን “እንዲያልፉ” በቲየርኒ እንደተነገራቸው ተዘግቧል።
ከአንድ ዓመት በኋላ ሁለቱ ቡድኖች አቻ ሲለያዩ የቶተንሃሙ ሃሪ ኬን የሊቨርፑሉ አንዲ ሮበርትሰን ላይ በሠራው ጥፋት ቀይ ካርድ አልተመለከተም በማለት ክሎፕ ወደ ቲየርኒ ቀርበው “ካንተ በስተቀር ከማንም ዳኛ ጋር ምንም ዓይነት ችግር የለብኝም” ብለዋል።
ባለፈው ጥር ላይ ቡድናቸው በብሬንትፎርድ ከተሸነፈ በኋላ ክሎፕ ቲየርኒን ጨምሮ ጨዋታውን የመሩ ዳኞችን ስለውሳኔዎቻቸው ማነጋገራቸውን ተናግረዋል።
“ከማይክሮዌቬ ጋር ከማውራት ጋር ተመሳሳይ ነው። ምንም ምላሽ አያገኙም። ሁልጊዜም ተመሳሳይ ነው” ሲል ለቢኢን ስፖርት ተናግሯል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ደግሞ የሊቨርፑሉን የግራ መስመር ተከላካይ አንዲ ሮበርትሰን ከመስመር ዳኛው ኮንስታንቲን ሃትዚዳኪስ ጋር በነበረው ግጭት በቲየርኒ ቢጫ ካርድ ተመዞበታል።
በትላንትናው የአንፊልድ ጨዋታ በመሐል ዳኛው የተናደዱት ክሎፕ ብቻ አልነበሩም። የስፐርስ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሪያን ሜሰንም በዳኛው ውሳኔ ተበሳጭተዋል።
የጨዋታውን አሸናፊነት ጎል ያስቆጠረው ጆታ በ81ኛው ደቂቃ ላይ እግሩን አንስቶ የኦሊቨር ስኪፕን ፊት ከመታ በኋላ በቢጫ ካርድ የታለፈበትን ምክንያት ጠይቀዋል።
“ማብራሪያ እፈልጋለሁ። በሜዳው ላይ ያለው ዳኛ ብቻ ሰይሆን የቴሌቭዥን ተባባሪ ዳኛው (ቫር) በድጋሚ እንዲታይ ለምን እንዳለደረጉ ማወቅ እፈልጋለሁ” ሲሉ ሜሰን ለቢቢሲ ስፖርት ተናግረዋል።
“እንደ እውነቱ ከሆነ በእግር ኳስ ሜዳ ላይ የምታዩት በጣም ግልፅ የቀይ ካርድ ነው። ተጋጣሚውን አደጋ ላይ ከመጣል ባለፈ የስኪፕ ፊት ስፌት አስፈልጎታል። ጆታ በሜዳ ላይ መቆየት ሳይገባው ጎል አስቆጥሮብናል” ብለዋል።
ምንም እንኳን ክሎፕ በዳኛው ላይ የራሳቸውን ትችት ቢሰነዝሩም የሜሰንን አስተያየት የተረዱ ይመስላሉ።
“እረዳዋለሁ። ራያን ስለ ሌሎች ነገሮች መጨነቅ አለበት። ይህ ቡድን መልሶ በማጥቃት ብቻ ሳይሆን ከዚህ የተሻለ ኳስ መጫወት አለበት።”
“ዲዮጎ ጆታ እግሩን ከፍ ቢያደርግም ጭንቅላቱን ለመምታት አይደለም የሄደው። ኦሊቨር ስኪፕ ቀደም ብሎ ቀይ ካርድ ሊያይ እንደሚገባ ሰምቻለሁ [ሉዊስ ዲያዝ ላይ በፈጸመው ጥፋት]። እሱስ ስለዚህ ተናግሯል?”
“ዲያጎ ጆታ ከሜዳ እንዲባረር ከመፈለግ ስለሌሎች ነገሮች ይጨነቅ” ብለዋል።
ሺረር “ይህ ተጋጣሚን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ጆታ ቀይ ካርድ ባለማግኘቱ ዕድለኛ ያደርገዋል” ብሏል።