ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁት የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች እገታ ሰቀቀን የሆነባቸው መርከበኞች
ቤተሰቦቻቸው ሲራቡ ማየት ወይም ሥራ ብለው በወጡበት በሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች እጅ የመውደቅ ዕጣ እንደተጋረጠባቸው ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፓኪስታን እና የኢራን መርከበኞችን ተናግረዋል።
የባሕር ላይ ዝርፊያ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የሚንቀሳቀሱ ዓሳ አስጋሪዎችን በድጋሚ ለጭንቀት ዳርጓቸዋል። የአፈና፣ የግድያ እና የሌሎች አሰቃቂ ጥቃት ታሪኮች ደጋግመው መሰማት ቢጀምሩም ብዙዎች ለሥራ ወደ ውቅያኖሱ እየተመለሱ ነው።
የጀልባ ባለቤቶች በበኩላቸው በአካባቢው እየታየ የሚገኘው ሕገ-ወጥ ተግባር አካል ናቸው ብለው ለሚያምኗቸው የሶማሊያ የፀጥታ አካላት በሺህ የሚቆጠሩ ዶላሮችን እጅ መንሻ ለመክፈል መገደዳቸውን ተናግረዋል።
መርየም ሁት እና ባለቤቷ ጉል መሐመድ የ20 ዓመት ልጃቸው ራሱል ባክሽ ከሕንድ ውቅያኖስ እስኪመለስ በጉጉት ጠብቀውታል።
“ልጃችን ለምን እንደማይመለስ መጠየቅ ጀመርን” በማለት መርየም ታስታውሳለች። ማንም መልስ አልሰጣትም።
ከሳምንታት በኋላ ግን ሌሎች ዓሣ አስጋሪዎች ዜናውን ይዘውላቸው መጡ።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው ራሱል በሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ተይዞ ነበር።
ከዚህም በኋላ እናት እና አባት ምንም መረጃ ሳያገኙ ወራትን በጭንቀት አሳለፉ።
አንድ ቀን የስልክ ጥሪ ደረሳቸው። ኔትዎርኩ ደካማ ቢሆንም ድምጹ ይለይ ነበር።
ረሱል ባኽሽ ነበረ።
“እያለቀሰ መላው ሰውነቱ ላይ መቁሰሉን ነገረኝ” ሲላት እናቱ ረዳት የማጣት ስሜት ተሰማት። “እንዲፈታ እንድንረዳው ለመነን።”
"ምን ያህል የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንደተሰማኝ መገመት ይከብዳል። ለልጄ ልነግረው የምችለው ነገር ቢኖር ‘ድሆች መሆናችንን አንተም ታውቃለህ’ ማለት ብቻ ነው” ትላለች መርያም።
የማስለቀቂያ ገንዘብ
ረሱልን ለመልቀቅ የባሕር ላይ ወንበዴዎቹ ወደ 12 ሺህ ዶላር ይከፈለን አሉ። ይህ ለቤተሰቡ የማይታሰብ ገንዘብ ነው።
የሚኖሩት በኢራኗ ቻባሃር ግዛት ውስጥ በምትገኝ አነስተኛ መንደር ነው። በቅርቡ በአካባቢው ተከሰተው ድርቅ በርካታ ወጣቶች መንደራቸውን ለቀው ወደ ሕንድ ውቅያኖስ እንዲያቀኑ አስገድዷቸዋል።
እርጅና እና ህመም ተጭኗት ለመራመድ የምትታገለው የራሱል እናት ለልጇ ገንዘብ ለማሰባሰብ ከመንደር መንደር ዞራለች።
ቤተሰቡ ያሉትን ከብቶች እና የተከበሩትን የዘንባባ ዛፎችን ጨምሮ አለኝ የሚለውን ሀብት እና ንብረት በሙሉ ሸጠ።
እገታ ወይስ ረሃብ
አሳ አስጋሪዎች ያለውን ስጋት ቢያውቁም ግን ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
የፓኪስታኗ ርዕሰ መዲና ካራቺ ነዋሪው የ38 ዓመቱ ሳሌም ኻህን “አልፈራሁም ካልኩኝ ዋሽቻለሁ ማለት ነው። ወደ ሞት እንደመሄድ ነው። ካልሄድን ግን ረሃቡ ቤት ውስጥ ይገድለናል” ብሏል።
ሳሌም ኻህን እአአ በ2018 በሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ታግቶ ተወስዷል። እገታው በድጋሚ መስፋፋቱ ያለፈ ቁስሉን እየመለሰበት መሆኑን ተናግሯል።
“ጀልባችንን በመጥለፍ ትላልቅ መርከቦችን ለማጥቃት ተጠቀሙበት” ሲል መርከበኛው ያስታውሳል።
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ምድረ በዳ ወሰዷቸው። ለ20 ቀናት ያለ ምግብ እና ውሃ አሳለፉ።
"ሌሎች እንዳያዩን በማለት ሌሊት ሌሊት እናለቅስ ነበር” ሲል ያለፈበትን ያስታውሳል።
በመጨረሻም ከባሕር ላይ ወንበዴዎቹ ጋር ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነው የተለቀቁት።
ሳሌም ወደ ውቅያኖቹ ለሥራ መመለሱን በመፍራት ሌላ ሥራ ለማግኘት ሞከረ።
ባለፈው ዓመት ግን ሌሎች ዓሣ አስጋሪዎች አካባቢው ሰላማዊ እንደሆነ ነገሩት።
በድጋሚ ሲመለስ ግን ከእገታ ለጥቂት ተረፈ።
“[የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች] ከፊት ሲመጡ አየዋቸሁ። የዓሣ ማጥመጃ መረባችንን ቆርጠን አመለጥን።”
የባሕር ላይ ወንበዴዎቹ በአቅራቢያው ያገኙትን የጓደኛውን ጀልባ በማጥቃት ገደሉት።
“ጥገኛ ተህዋስያን”
የዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎች ዋነኛው ዒላማቸው አይደሉም። እነሱን የሚጠቀሙት ትላልቅ መርከቦችን ለመያዝ ነው።
የባሕር ላይ ወንበዴዎቹ የሚሠሩት ልክ እንደጥገኛ ተህዋስያን ነው ይላሉ ዓሣ አስጋሪዎቹ። ጀልባዎቻቸውን ይወራሉ፤ ንብረታቸውን ይመገቡ እና መርከቦቹን በሚያጠቁበት ጊዜ ጥቃት ከተሰነዘረባቸው ዓሣ አስጋሪዎቹን እንደ ሰብአዊ ጋሻ ይጠቀሙባቸዋል።
በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ የባሕር ላይ ወንበዴዎችን የሚከላከለው የአውሮፓ ኅብረት ፀረ የባሕር ላይ ውንብድና ተልዕኮም (ዩናቭፎር) ተመሳሳይ ጉዳዮች እንዳሉ ዘግቧል።
“ይህ በአካባቢው እየጨመረ ያለ አዲስ የባሕር ላይ ውንብድና ድርጊት ነው” ሲል ዩናቭፎር ለቢቢሲ ገልጿል።
መስመሩ በመርከቦች ከሚጨናነቁ የዓለማችን የባሕር ላይ መንገዶች አንዱ ነው። በቀይ ባሕር እና በሱዩዝ ካናል በኩል ለማለፍ የሶማሊያ የባሕር ዳርቻዎችን አቋርጠው ያልፋሉ። አውሮፓ እና እስያን የሚያገናኘው አጭር የባሕር መስመርም ነው።
ከዓለም አቀፍ የባሕር ንግድ 12 በመቶ ያህሉ በቀይ ባሕር በኩል ያልፋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን አካባቢው መረጋጋት ርቆታል።
በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ አማጺያን በጋዛ ከእስራኤል ጋር እየተፋለመ ያለውን ሐማስን በመደገፍ መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
እነዚህ ጥቃቶች የምዕራባውያን የባሕር ኃይልን ያሳሰቡ ሆነዋል። በዓሣ አስጋሪዎች ላይ የሚፈጸመው ዝርፊያ እንዲበረታ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ይህ እንደሆነ ያምናሉ።
ትርፋማው ንግድ
ካፒቴን መሐመድ አሽራፍ ካራቺ ወደብ ላይ ግዙፍ የሆነችው የኢራን የዓሣ ማጥመጃ መርከብ ግንባታ እስኪትጠናቀቅ እየጠበቀ ነው።
አሽራፍ ጀልባዋን ለማሠራት 18 ወራት እና 150 ሺህ ዶላር አውጥቷል። በቅርቡም ሥራ ይጀምርባታል።
“የባሕር ላይ ወንበዴዎች ሊይዙን ስለሚችሉ በጣም ፈርቻለሁ። ያሉንን ካልፈጸምን ተኩሰው ሊገድሉን ይችላሉ” ሲል አሽራፍ ተናግሯል።
ኢራናዊው መረከበኛ ካፒቴን ቃዩም በዚህ መስመር ተመላልሶ ዓሣ አስግሯል።
ልክ እንደ ካፒቴን አሽራፍ እና ሌሎች መርከበኞች ሁሉ ራሱን ከባሕር ላይ ወንበዴዎች ለመከላከል በሺህዎች የሚቆጠር ዶላር ለሶማሊያ የደኅንነት ባለሥልጣናት ይከፍላል።
ከፍተኛ የደኅንነት ጥበቃ አጃቢዎች ፍላጎት በመኖሩ ለ40 ቀናት ለአንድ ጠባቂ እስከ 18 ሺህ ዶላር መጠየቅ ተጀምሯል።
ክፍያው ግን ለጥበቃ ሠራተኞች ብቻ የሚከፈል አይደለም። በሶማሊያ የውሃ ክልል ውስጥ ዓሣ የማስገር ፈቃድ ለማግኘትም ክፍያ ያስፈልጋል። “ሁሉም የውሸት መሆኑን እናውቃለን” ብሏል ቃሲም።
ትክክለኛ የባሕር ጠባቂዎች ካጋጠሟቸው ፈቃዶቹን እንዳያሳዩ ይነገራቸዋል። ይልቁኑም በሚሰጧቸው ቁጥር ደውለው “እንዲያስተካክሉ” ይነገራቸዋል።
የደኅንነት ጥበቃ አገልግሎት አቅራቢዎቹ ሕጋዊ ስለመሆናቸውም ግልጽ አይደለም። ዓሣ አስጋሪዎች ፈቃዱን የሚያገኙት ወደ ባሕር ዳርቻው አቅራቢያ በመሄድ በአነስተኛ ጀልባ የሚመጣውን ጠባቂ እና ፈቃድ በመውሰድ ነው።
ከ40 ቀናት በኋላ ኩባንያው ገንዘቡ መስተላለፉ እስኪያረጋግጥ ጀልባው እና ሠራተኞቹ ተይዘው እንደሚቆዩ ካዩም እና ሌሎች የጀልባ ባለቤቶች ተናግረዋል።
ፓኪስታናውያን እና ኢራናውያን አሳ አስጋሪዎች በበኩላቸው ገንዘቡን ለኢራን ገንዘብ መንዛሪዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
እነሱ ደግሞ ዱባይ ላሉ ደላሎች በመስጠት ወደ ሶማሊያ እንዲተላለፍ ይደረጋል። የባሕር ላይ ወንበዴዎቹ ታጋቾችን ለማስለቀቀም ተመሳሳይ የክፍያ መንገዶችን ይጠቀማሉ ብለዋል።
እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች
የካራቺ ወደብ በአሳዛኝ ታሪኮች የተሞላ ነው። ለበርካታ ዓመታት ያገለገለው መርከበኛው ጉላም ራሺድ የጓደኛቸው ጀልባ ባለፈው ዓመት በባሕር ወንበዴዎች ጥቃት እንደደረሰባት እና ለማምለጥ ሲሞክሩ በጥይት እንደመቱት ተናግሯል።
በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እያለ ጀምሮ ዓሣ ማስገር ላይ የተሠማራው የ43 ዓመቱ ራሺድ “አንድ የመርከቧ አባል በመቁሰሉ የባሕር ላይ ወንበዴዎቹ ከነሕይወቱ ወደ ባህር ወረወሩት” ብሏል።
እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚረብሹ ምሽቶችን ይፈጥራሉ። “ዓይኖቻችንን እንጨፍናለን፣ ልባችን ግን አይተኛም” ሲል ገልጿል።
ከአንድ ዓመት በላይ ታግቶ የቆየው የቻባህሩ ራሱል ባኽሽ ተፈትቶ ከወላጆቹ ጋር ለመገናኘት በቃ። ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ከተፈቱ በርካታ መርከበኞች አንዱ ለመሆን በቃ።
የካራቺው ሳሌም ኻህን ደግሞ ሴት ልጁ ኔምራንን በእጆቹ አጥብቆ ይዟታል። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ውቅያኖቹ ይመለሳል።
ቤተሰቦቹ የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግላቸው ያውቃሉ። መሰነባበት ግን መቼም ቀላል ሆኖለት አያውቅም።
ሌላ ጥቃት እንዳይገጥመው ይፈራል። ምሽቶች ለእሱም በጣም ከባድ ናቸው።
“ዓይኖቼን ከመዝጋቴ በፊት ስልኬን ከፍቼ የእናቴን ፎቶ፤ ከዚያም የባለቤቴን እና የሴት ልጆቼን ፎቶ እያየሁ አለቅሳለሁ። ቀጥሉ ደግሞ ስልኩን ደረቴ ላይ አድርጌ እተኛለሁ” ይላል።