በመላው ዓለም ከገና አከባበር ጋር የተያያዙ ለየት ያሉ ክስተቶች

ፎቶ የሚነሱ ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በየዓመቱ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታኅሣሥ 25 በዓለም ላይ እጅግ ዝነኛ ከሆኑ ክብረ በዓላት አንዱ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ይከበራል።

በመላው ዓለም በ150 አገራት መከበር ብቻ ሳይሆን ለክርስትና እምነት ሆነ ለሌላ እምነት ተከታዮች በዓመታዊ የቀን አቆጣጠራቸው ላይ ቁልፍ ቦታ አለው።

ዓመት በመጣ እና በሄደ ቁጥር ቤተሰቦች በአንድ ገበታ ተሰባስበው ማዕድ የሚቆርሱበት፣ ቤተሰባዊ ትስስራቸውን የሚጠናክሩበት በዓልም ነው።

በዓሉ በቤተሰብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃም የተለያዩ ነገሮችን በመከወን ይከበራል። በገና በዓል ወቅት ከምዕራቡ ዓለም ተነስተው በመላው ዓለም እየተለመዱ የመጡ እና ከበዓሉ ጋር ከሚጠቀሱ ነገሮች መካከል የገና አባት እና የገና ዛፍ ተጠቃሽ ናቸው።

ይህ በምዕራባውያን ዘንድ እጅጉን የተለመደ ሲሆን መንገዶች በመብራት፣ በገና ዛፍ እና በገና አባት ትርዒቶች ይደምቃሉ።

የገበያ አዳራሾች፣ አውደ ርዕዮች እንዲሁም የመንግሥት እና የግል ተቋማት የገና ዛፍን አስውበው እና አስጊጠው ያስቀምጣሉ።

በለንደን ትራፋላጋር አደባባይ የቆመ የገና ዛፍ

ኖርዌይ በየዓመቱ የምትልከው ስጦታና የምትደብቀው መጥረጊያ

በለንደን ትራፋላጋር አደባባይ በታኅሣሥ ወር በየዓመቱ ትልቅ የገና ዛፍ ተውቦ ይቀመጣል።

በብሪታኒያ የገና በዓል አከባባር ወቅት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የገና ዛፉ በስጦታ የምትልከው አገር ኖርዌይ ናት።

በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ብሪታኒያ ለኖርዌይ መንግሥት እና ንጉሥ ጠንካራ አጋር ነበረች።

በወቅቱ ኖርዌይ በናዚ ቁጥጥር ሥር የነበረች ሲሆን፣ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ኖርዌይ ለክፉ ቀን ወዳጇ ምስጋናዋን ለመግለጽ በየዓመቱ የገና ዛፍ ወደ ለንደን በስጦታ መልክ መላክ ጀመረች።

ይህ ልማድ ከአውሮፓውያኑ 1947 ጀምሮ የሚከናወን ሲሆን፣ በዚህ ዓመት በስጦታ የላከችው ዛፍ ርዝመት 25 ሜትር ይደርሳል ተብሏል።

ኖርዌይ ወደ ለንደን ስጦታ ስትልክ በዋዜማው ደግሞ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ቤቶች መጥረጊያዎቻቸውን ይደብቃሉ።

ይህንን የሚያደርጉት ክፉ መናፍስት መጥተው ይሰርቁታል በሚል እምነት ምክንያት ነው።

በኖርዌይ ባህል ክፉ መናፍስት በገና ዋዜማ በየሰዉ ቤት በመምጣት የሚጋልቡት መጥረጊያ ይፈልጋሉ የሚል የቆየ ልማድ አላቸው።

ይህንንም ለመከላከል በገና ዋዜማ ወደ መኝታቸው ከመሄዳቸው በፊት በቤት ውስጥ ያሉትን መጥረጊያዎች በሙሉ ይደብቃሉ።

ከገና እራት በኋላ በሻማ ብርሃን ታሪክ የሚያነቡት አይስላንዳውያን

ሻማ ለኩሳ መፍሐፍ የምታነብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአይስላንድ መጽሐፍ አሳታሚዎች በገና ሰሞን አዳዲስ መጻሕፍትን ለገበያ ያቀርባሉ።

ይህም "የገና መጻሕፍት ጎርፍ" የሚሰኝ ሲሆን፣ ባሕሉ የጀመረው በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት እንደሆነ ይታመናል።

በወቅቱ በርካታ ነገሮች ተቆጥቦ እና ተቆጥሮ ሲሰጥ ወረቀት ግን በገፍ ይቀርብ ነበር። ስለዚህ በገና ወቅት ስጦታ ለመስጠት የነበረው ብቸኛ አማራጭ መጽሐፍት ነበሩ።

በአሁኑ ወቅት የአይስላንድ የሕትመት ኢንዱስትሪን በእጅጉ የረዳው ይህ ባሕል በገና ዋዜማ ቤተሰቦች ተሰባስበው ስጦታ እየተለዋወጡ፣ ምግባቸውን እየበሉ ከዚያም ምሽቱን ሻማ ለኩሰው መጽሐፍት በማንበብ ያከብሩታል።

ምናልባት ቼኮሌት እና የሚጎነጩት መጠጥም ሊይዙ ይችላሉ። መጽሐፍ ግን የማይቀር ስጦታቸው ነው።

ገና ሕገወጥ የሆነበት ዓመት

በአውሮፓውያኑ 1647 በብሪታኒያ በገና ዕለት የሚኖር ፈንጠዝያ ታግዶ ነበር።

በወቅቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በገና ዕለት፣ በፋሲካ እና ዊትሱን (Whitsun ) በዓላት ወቅት የሚኖር ፈንጠዝያን በአገሪቱ ውስጥ አግደዋል።

በወቅቱ የምክር ቤቱ አባላት ከነበሩት መካከል የካቶሊክ እምነት ተከታዮች የገና በዓልን ማክበራቸውን የሚቃወሙ ሃይማኖታዊ እና ሞራላዊ እሴታቸው የሚለዩ ፒዩሪታን (Puritan) የበላይነት ነበራቸው።

ስለዚህ በታኅሣሥ 25 ከፌሽታ ይልቅ በምትኩ የጾም ጊዜ መሆን እንዳለበት ወሰኑ።

ከገና ጋር የተያያዙ ክብረ በዓላት የተከለከሉ በመሆናቸው ወታደሮች በሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች በዓሉን ሲያከብሩ የሚያገኟቸውን እንዲበትኑ እና በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ ይሰማሩ ነበር።

በለንደን ወታደሮች መጾም ሲገባቸው ለገና አከባበር ምግብ የሚያበስሉ ሰዎችን ለመፈለግ በየአውራ ጎዳናው ላይ ይሰማሩም ነበር።

የገና በዓላትን የሚዘክሩ መዝሙሮች፣ ቤትን እና አደባባይን ለበዓሉ ማስዋብን ተከልክሎ ቆይቷል።

አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል እገዳውን የተቃወመ በመሆኑ በአውሮፓውያኑ 1660 ገና ዳግም መከበር ጀመረ።

ቀበጥ ብለው የሚያሳልፉት ጃፓናውያን

በርካታ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ባሉባት ጃፓን ገና በተለየ መንገድ ይከበራል። ገናን ከቤተሰብ ጋር ሰብሰብ ብሎ ከማክበር ይልቅ የገና ዋዜማን ጥንዶች ወጣ ብለው ማክበር ይመርጣሉ።

በገና መብራቶች የሚደምቁት የጃፓን ጎዳናዎች፣ ምግብ ቤቶቻቸው እንዲሁም ሆቴሎች የተለየ መስተንግዶ አዘጋጅተው ደንበኞቻቸውን ይጠብቃሉ።

ምግብም ቢሆን ከሌሎቹ አገራት በተለየ መልኩ ጃፓናውያን ኩሪሱማሱ ኬኪ (kurisumasu keki) የተባለ ጣፋጭ በመመገብ ያከብራሉ።

በብሪታኒያ በገና ምሽት ተወዳጅ ከሆኑ ምግቦች መካከል ተርኪ የተባለችው የዶሮ ዝርያ ቀዳሚዋ ናት። በገና ምሽት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ተርኪ በማብሰል ተሰባስበው ይመገባሉ።

በጃፓን በገና በዓል ወቅት የተጠበሰ ዶሮ ተወዳጅ ሲሆን 3.6 ሚሊዮን ቤተሰቦች ይህንኑ ለመመገብ ወደ ኬኤፍሲ መደብሮች ጎራ ይላሉ።

ይህ የተጠበሰ ዶሮ የሚሸጠው መደብር በ1970ዎቹ ከሠራው የገበያ ማስተዋወቂያ ወዲህ ጃፓናውያን ከሳምንት አስቀድመው ምግባቸውን ያዝዛሉ።

በዚህም የተነሳ ከተለመደው የገበያ ቀን በ10 እጥፍ በላቀ ሁኔታ የገና ዕለት ምግብ ቤቶች በደንበኞች ይጨናነቃሉ።

የቼክ ሪፐብሊክ የጫማ ውርወራ እና ገና

በቼክ ሪፐብሊክ የገና ዋዜማ ቤተሰብ ተሰብስቦ የሚያከብረው በዓል ብቻ አይደለም።

ያላገቡ ሴቶች ጫማ በመወርወር መልካም ነገር እንዲገጥማቸው የሚመኙበት ባሕልም አላቸው።

ያላገቡ ሴቶች ተራ በተራ ጫማቸውን ከትከሻቸው በላይ እየወረወሩ ፊት ለፊት ወደሚገኘው በር ያመራሉ።

የጫማው አቅጣጫ የወደፊት የፍቅር ሕይወታቸውን እንደሚተነብይ ይታመናል።

የጫማው ጫፍ ወደ በሩ ከዞረ ትዳር ለመያዝ እየተቃረቡ ነው የሚባል ሲሆን፣ የጫማው የኋላ ክፍል፣ ተረከዙ ወደ በሩ ከዞረ ደግሞ ሌላ ዓመት የላጤነት ሕይወት እንደምትመራ ያሳያል።

ይህ በአፈ ታሪክ ላይ የተመሠረተው ወግ በአገሪቱ የገና አከባበር ላይ እንደ ጨዋታ ተደርጎ በሰፊው ይዘወተራል።

ለገና ብቻ ገበያ ላይ የሚቀርበው የሜክሲኮ ቢራ

ኖቼ ቡዌና (Noche Buena) የተሰኘው የሜክሲኮ ቢራ በገና በዓል ሰሞን ብቻ ለገበያ የሚቀርብ ነው

የፎቶው ባለመብት, Heineken Mexico

የምስሉ መግለጫ, ኖቼ ቡዌና (Noche Buena) የተሰኘው የሜክሲኮ ቢራ በገና በዓል ሰሞን ብቻ ለገበያ የሚቀርብ ነው

ሜክሲኮ በዓለም ትልቋ ቢራ ላኪ አገር ናት። ነገር ግን በጣም ተወዳጅ ከሆኑት ቢራዎች መካከል አንዱ በአገሪቱ ውስጥ ብቻ የሚገኝ እና ለገና በዓል ለጥቂት ሳምንታት ብቻ ለገበያ ይውላል።

በርካታ አገራት ለገና በሚያዘጋጇቸው መጠጦች ይታወቃሉ። ፖርቶ ሪኮ ጣፋጭ በሆነው ኮኪቶ፣ ጀርመን ደግሞ በቅመማ ቅመም በተሞላው ትኩስ ወይን ይታወቃሉ።

ሜክሲኮ ደግሞ ኖቼ ቡዌና የሚባል የቢራ ዓይነት ለገና በዓል ብቻ ታቀርባለች። ይህ የአልኮል መጠጥ የገና በዓል ሲቃረብ ብቻ ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን ከአገር ውጭ በየትኛውም ስፍራ አይገኝም።

ኖቼ ቡዌና "መልካም ምሽት" ወይንም "ቅዱስ ምሽት" እንደማለት ነው።

ይህም በስፔን፣ ላቲን አሜሪካ እና ፊሊፒንስ የሚከበረውን የገና ዋዜማ ለማመልከት ጥቅም ላይ ይውላል።

በኖቼ ቡዌና ወይንም በገና ዋዜማ ምሽት ቤተሰብ ተሰባስቦ፣ የተዘጋጀውን ልዩ ምግብ በጋራ የሚቋደስ ሲሆን ሙዚቃ እና ዳንስም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ይኖራል።

ኖቼ ቡዌና የተሰኘው ቢራ በሜክሲኮ ብቻ የሚገኝ ሲሆን ገበያ ላይ የሚውለውም የገና በዓል ሲቃረብ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላም ሆነ በፊት አይመረትም።

የገና ዝማሬ በህዋ ላይ

ፈረንጆች ለገና ደጋግመው ከሚሰሙት ሙዚቃ መካከል 'ጂንግል ቤል' የተሰኘው ዝማሬ ቀዳሚው እና ተወዳጁ ነው።

ይህ ሙዚቃ እንደ በአውሮፓውያኑ 1965 የናሳ ጄሚኒ 6ኤ የተሰኘችው መንኮራኩር በመጠቀችበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በህዋ ላይ እንዲጫወት ተደርጓል።

የጄሚኒ 6 ጠፈርተኞች የናሳን ተልዕኮ የሚቆጣጠረውን አካል በራሪ አካላትን (ዩፎ) ተመለከትን በማለት ካታለሉ በኋላ በሐርሞኒካ እና በትንሽ ደወል ጂንግል ቤልን ተጫውተዋል።

የገና አባት

ከዓመት ዓመት በመላው ዓለም የሚገኙ ሕጻናት ለገና አባት ደብዳቤ ይጽፋሉ።

የገና አባት ወይንም ሳንታ ክላውስ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ደብዳቤዎች ከመላው ዓለም እንደሚጻፉለት ይገመታል።

በዩናይትድ ኪንግደም የገና አባት ደብዳቤዎቹ እንዲደርሷቸው በማለት ሮያል ሜል የሳንታን ይፋዊ አድራሻ ያስተዋውቃል።

በዚህም የተነሳ በተለያዩ አገራት ሳንታ የሚለውን ስም ያካተቱ የቦታ ስሞች ይገኛሉ፤ በተለይም በምዕራቡ ዓለም።

በቤታቸው ክሪኬት የሚጫወቱት አውስትራሊያውያን

የገና ቀን በአውስትራሊያ በፀሐይ ብርሃን የደመቀ፣ በምግብ የተሞላ እና በቤተሰብ የታጀበ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ትንሽ ቢራ እና የክሪኬት መጫወቻ በየቤቱ አይጠፋም።

ይህ የአውስትራሊያውያን የቤተሰብ ባሕል የሆነው ክሪኬት ለገና መጫወት በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙትን ያሳተፈ ነው።

ክሪኬት ለአንድ ቀን ብቻ የማሸነፍ ጉዳይ አይሆንም። ሁሉም ሰው የሚሳተፍበት ጨዋታ ነው።

የቤቱ የአምስት ዓመት ልጅ ኳሱን ሲመታ ቢሳሳት ሁሉም እንዳላየ በማለፍ ዳግመኛ ዕድል ይሰጠዋል። የጨዋታው ደንቦቹ ከቤተሰብ ወደ ቤተሰብ ይለያያሉ።

ክሪኬት የሚጫወት ቤተሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሞቱ ዘመዶቻቸውን የሚጎበኙት ፊንላንዶች

በፊንላንድ በገና ወቅት የሞቱ ዘመዶችን መጎብኘት የተለመደ ነው።

በገና ዋዜማ ቤተሰቦች የሞቱ ዘመዶቻቸውን የቀብር ስፍራ በመሄድ ሻማ ለኩሰው ያስታውሷቸዋል። 'ዚስ ኢዝ ፊንላንድ' የተሰኘው ድረ ገጽ ሦስት አራተኛው ፊንላንዳዊ ይህንን ያደርጋል ሲል ዘግቧል።

በገና ዋዜማ ምሽት የመቃብር ስፍራዎች በበረዶ ተሸፍነው በሻማ ብርሃን ደምቀው የተለየ ትዕይንት ይፈጥራሉ።

የመቃብር ስፍራ ላይ የተለኮሱ ሻማዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ገናን በሸረሪት ድር የሚያስውቡት ዩክሬናውያን

በምዕራብ ዩክሬን የገና ዛፍን በአብረቅራቂ ትንንሽ ኳሶች ወይንም በኮከብ ማድመቅ አልተለመደም። ከዚያ ይልቅ የተጌጠ የሸረሪት ድር ይጠቀማሉ።

ይህ ታሪክ መነሻውን ያደረገው ከገና ሸረሪት ነው። በምሥራቅ አውሮፓ ተረክ ውስጥ የአንዲት ደሃ ሴትን የገና ዛፍ በድሩ ስላስዋበ ሸረሪት የሚተርክ ተረት አለ።

ሴትየዋ ማለዳ ስትነቃ የሚያብረቀርቅ የሸረሪት ድር የገና ዛፏን አስውቦት ታገኛለች። ከዚያ በኋላ ቤተሰቧ የገና ዛፉን ለማስዋብ ሌላ ነገር መጠቀም አላስፈለገውም።

ዩክሬናውያንም ይህንን በማሰብ ከወረቀት እና ከሽቦ ድሮችን በመሥራት እና በዛፎቻቸው ዙሪያ በመጠቅለል ያስውባሉ።

በገና ዛፍ ዙሪያ ሸረሪት ወይም ድሯን ማግኘት እንደ መልካም ዕድል ይቆጠራል። ስለዚህ በገና ሰሞን የገና ዛፉ ያለበት አካባቢን አለማጽዳት የተለመደ ነው።

ሀው ዘ ግሪንች ስቶል ክሪስማስ (2000)

የምንጊዜም ዝነኛ የገና ፊልም

በገና ሰሞን በብዛት በፊልም አፍቃሪያን ዘንድ የታየ እና ከፍተኛ ገቢ ያስገባው ፊልም 'ዘ ግሪንች' (2018) ነው።

ይህ ፊልም በመላው ዓለም ከኅዳር 2018 እስከ ታኅሣሥ 2020 ድረስ ለዕይታ በበቃበት ጊዜ ውስጥ 379 ሚሊዮን ፓውንድ አስገብቷል።

ከአውሮፓውያኑ 1990 ጀምሮ በገና ሰሞን በከፍተኛ በሁኔታ በመታየት ክብረ ወሰኑን ይዞ የነበረው 'ሆም አሎን' የተሰኘውን ፊልም የበለጠው ይህ ፊልም በተከታታይ በተለያዩ ርዕሶች ዳግም ተጀርቶ ለዕይታ በቅቷል።