የስደተኝነት ከለላ የማግኘት መብት ያለው ማን ነው? ይህስ በማን ይወሰናል?

በጀርባ የታዘሉ እና በእጅ የተያዙ ህጻናት እየተራመዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ጊዜ በየዓመቱ በአሜሪካ ተቀባይነት የሚያገኙ ስደተኞች ቁጥር 125 ሺህ ላይ ተገድቦ ነበር

ባለፈው ሳምንት 59 ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን የጥገኝነት ከለላ መብት ማግኘታቸውን ተከትለው ዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ ወደሚገኘው ደለስ አየር ማረፊያ ደርሰው ነበር።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የዘር ሐረጋቸው ከአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች የሚመዘዘው እና ህዳጣን የሆኑት አፍሪካነሮች "የዘር መድልዎ" እና "ዘር ማጥፋት" ሰለባ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ይህ ክስ ከእውነት የራቀ እንዲሁም የሚደገፍበት ማስረጃ የሌለው እንደሆነ ገልጸዋል።

እንደነገሩ ለብለው እና አሜሪካን ባንዲራ እያውለበለቡ የታዩት ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት በሀገሪቱ ባለሥልጣናት ደማቅ አቀባበል ተደረጎላቸዋል። ተቺዎች ይህ ድርጊት የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞችን በተመለከተ ከያዘው አቋም ጋር እጅጉን የሚቃረን እንደሆነ ይናገራሉ።

ትራምፕ ጥር ላይ የአገራቸው ስደተኞችን የመቀበል እና የማስፈር ፕሮግራም እንዲታገድ ያደረገ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል። የስደተኞችን ቅበላ ሥርዓት መቋረጥ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን ጉዳይ በእንጥልጥል አስቀርቷል።

ይሁን እንጂ ትዕዛዙ፤ የተወሰኑ የስደተኝነት ጥያቄዎች በልዩ ሁኔታ አንድ በአንድ እንዲታዩ ፈቅዷል። በየካቲት ወር ደግሞ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አፍሪካነሮች የስደተኝነት ከለላ እንዲያገኙ የሚያስችል ሌላ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

አፍሪካነሮች ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ድርሻ ሰባት በመቶ ሆኖ ሳለ ከሀገሪቱ የእርሻ መሬት ግማሹን በሚቆጣጠሩባት ደቡብ አፍሪካ፤ የትራምፕ ውሳኔ ሰፊ ትችት እና ቁጣን ቀስቅሷል። ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ወደ አሜሪካ የተጓዙትን ሰዎች "ፈሪዎች" ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።

"በሀገራችን ያሉትን ሁሉንም የጎሳ ቡድኖች ከተመለከትን ጥቁር እና ነጭ፤ እዚህ ሀገር የቆዩት ሀገራቸው ስለሆነ ነው። ከችግሮቻችን መሸሽ የለብንም፤ እዚሁ መቆየት እና ችግሮቻችን መፍታት አለብን" ብለዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና አስተያየት ሰጪዎች እርምጃውን ተችተዋል። የኤፒስኮፓሊየን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ "ለዘር ፍትህ እና እርቅ" ባላት ቁርጠኝነት ምክንያት አፍሪካነሮችን ለማስፈር እገዛ እንደማታደርግ በመግለጽ ለ40 ዓመታት ገደማ የቆየውን ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ያላትን ትብብር አቋርጣለች።

ቢቢሲ በመንግሥታቸው የሚወሰድባቸውን እርምጃ በመሸሽ ወደ አሜሪካ ከሚገቡ እንደ አፍጋኒስታውያን ባሉ ግለሰቦች ፈንታ ለምን አፍሪካነሮች የስደተኝነት ከለላ እንዳገኙ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዲኤታ ጆን ላንዳው ጥያቄ አቅርቧል።

ሚኒስትር ዲኤታው፤ ስደተኞች ምን ያህል በቀላሉ ከማኅበረሰቡ ጋር ሊዋሃዱ ይችላሉ የሚለው መስፈርት ከግምት ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል። ይህ ማብራሪያ የስደተኝነት ከለላን የሚያገኘው ማነው የሚለውን ለመወሰን ፖለቲካ እና ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች ያላቸውን ሚና በተመለከተ ክርክር አስነስቷል።

በብዙ ሰዎች መከካል ያሉ ሁለት ህጻናት የብረት መከለያን ተደግፈው፤ አጠገባቸው ያለች ሴት ህጻን ልጅ አቅፋ ትታያለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው እስከ ሰኔ 2024 ድረስ በዓለም ዙሪያ 43.7 ስደተኞች ይገኛሉ

ስደተኛ ማነው

እ.አ.አ በ1951 የተፈረመው የስደተኞች ስምምነት፤ ስደተኛ ለሚለው ትርጉም ሲሰጥ "በዘር፣ በሃይማኖት፣ በዜግነት፣ የአንድ የተለየ ማኅበራዊ ቡድን አባል በመሆን ወይም በፖለቲካዊ እሳቤ ምክንያት እርምጃ እንደሚወሰድበት ፍርሃት የሚፈጥር ተጨባጭ ስጋት ያለበት እና ዜግነቱን ከያዘበት ሀገሩ ውጪ የሆነ" ሰው እንደሆነ ይገልጻል።

በተጨማሪም ስደተኛ የሚባለው "የዚያን ሀገር ጥበቃ ለማግኘት የማይችል ወይም ከፍርሃት የተነሳ ጥበቃ ለማግኘት ፈቃደኛ ያልሆነ፤ ወይም ዜግነት የሌለው እና ከቀድሞ መኖሪያው ሀገር ውጪ የሆነ፤ ለመመለስ የማይችል ወይም ከፍርሃት የተነሳ የማይፈልግ" ሰው መሆኑን ያስረዳል።

ስደተኛ ለሚለው ሃሳብ የተሰጠው የመጀመሪያው ትርጓሜ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተሰደዱ አውሮፓውያንን ብቻ ይመለከተ የነበረ ሲሆን፣ በ1967 በስምምነቱ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ተከትሎ ግን መልክዓ ምድራዊ ገደቦች ተነስተዋል።

ስምምነቱ ከስደተኝነት ትርጓሜ በተጨማሪም የስደተኞችን መብት ዘርዝሯል።

ስደተኞች በቁጥር

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) መረጃ እንደሚያመለክተው እስከ ሰኔ 2024 ድረስ በዓለም ዙሪያ 43.7 ሚሊዮን ስደተኞች ይገኛሉ። ተቋሙ ስር ከሚገኙት ስደተኞች መካከል 65 በመቶው የመጡት ከአራት ሀገራት ነው፤ ከሶርያ፣ ከቬንዙዌላ፣ ከዩክሬን እና ከአፍጋኒስታን።

71 በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች የተጠለሉት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ነው። ኢራን፣ ቱርክ፣ ኮሎምቢያ፣ ጀርመን እና ኡጋንዳ ዋናዎቹ ስተደተኛ ተቀባይ አምስት ሀገራት ናቸው። 70 በመቶ ገደማ ስደተኞች የተጠለሉት በጎረቤት ሀገራት ነው።

በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ስር በየዓመቱ በአሜሪካ ተቀባይነት የሚያገኙ ስደተኞች ቁጥር 125 ሺህ ላይ ተገድቦ ነበር።

በባይደን የመጨረሻው የፕሬዝዳንትነት ዓመት ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች የስደተኝነት መብት ያገኙ ሲሆን፣ ይህም በሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ነው።

በብረት መደገፊያ ትይዩ የተሰለፉ በርካታ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በስደተኛ፣ በጥገኝነት ጠያቂ እና በፍልሰተኛ መከከል ያለው ልዩነት ምንድነው?

ስደተኛ የሚባለው በጦርነት፣ በአመጽ ወይም በፍርድ ምክንያት ሀገሩን ጥሎ የሸሸ ሰው ነው። ግለሰቡ የስደተኝነት ከለላ ሲሰጠው ሕጋዊ ጥበቃ ያገኛል።

ጥገኝነት ጠያቂ የሚባለው ደግሞ በአመጽ፣ በጦርነት ወይም በፍርድ ምክንያት ከሀገሩ የሸሸ፤ ነገር ግን ስደተኛ ስለመሆኑ ገና የሕግ ዕውቅና ያላገኘ ሰው ነው።

እንደ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ገለጻ "ፍልሰተኛ" ለሚለው ቃል ወጥ የሆነ ፍቺ የለም። ነገር ግን በአጠቃላይ ተቀባይነት ያለው ፍቺ፤ "በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ድንበሮች፤ ሁልጊዜ መኖሪያው ከነበረ ቦታው/ቦታዋ በተለያዩ ምክንያቶች በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት የለቀቀ/የለቀቀች" የሚል ነው።

የስደተኝነት ከለላን ማን እንደሚያገኝ የሚወስኑ ጉዳዮች ምንድናቸው?

ስደተኞች እውቅና የሚያገኙት በዓለም አቀፍ ሕግ በተቀመጡ ፍቺዎች መሠረት ነው። ነገር ግን ሀገራት ማን ይህንን መብት ለማግኘት ብቁ እንደሆነ የሚወስኑበት የየራሳቸው ሂደቶች አሏቸው።

በስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር እና የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት የዘር እና የዘር መድልዎ ራፖርተር የሆኑት ቴንዳዪ አቺዉሜ፤ የስደተኝነት ከለላን የሚያገኘው ማን ነው? የሚለውን በተመለከተ አድልዎ እንዳለ ይናገራሉ።

ፕሮፌሰሯ እንደሚገልጹት፤ አንዳንድ ሀገራት ግንኙነት የሚጋሯቸውን ሰዎች ለማገዝ የሚመርጡ ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜም ነጭ ስደተኞች፤ ነጭ ያልሆኑ ስደተኞች የማያገኙት "ልዩ ጥቅም እና ጥበቃ" ይሰጣቸዋል።

"ዩክሬን ለዚህ ትክክለኛ እና ግልጽ ምሳሌ ነች" ይላሉ።

"ከዚያ ሀገር እየሸሹ የነበሩ ሰዎችን ምሥል እና ከዩክሬን የሸሹ ነጭ ያልሆኑ ሰዎች የሚሰጣቸውን የተለየ አቀባበል ስንመለት ተገቢ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ጩኸት ተስተጋብቶ ነበር" ብለዋል።

አቺዉሜ፤ የሀገራት ስትራቲጂካዊ ፍላጎት የሚቀበሏቸውን ስደተኞችን ማንነት እንደሚቀርጽ ይናገራሉ። ለምሳሌ፤ አንድ ሀገር ራሱ በፈጠረው ችግር የሚፈናቀሉ ሰዎችን መቀበልን በተመለከተ የተለየ ፍላጎት ሊያሳይ ይችላል።

ፕሮፌሰሯ፤ "አንዳንድ ጊዜ ሀገራት እንደ ሴቶች፣ ህጻናት ያሉ ተጋላጭ ስደተኞችን ወይም የተለየ ዓይነት ፍርድ እየተፈጸመባቸው ያሉ አረጋውያንን መቀበል ምርጫቸው እንደሆነ ይገልጻሉ" ይላሉ።

"ነገር ግን የዓለም አቀፍ ሕግ እንደ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ብሔራዊ ማንነት ባሉ አድሏዊ አቅጣጫዎች የተመሠረቱ አግላይ ምርጫዎችን ይከለክላል"

አየር ማረፊያ ውስጥ የተቃውሞ መፈክር የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስደተኞች እውቅና የሚያገኙት በዓለም አቀፍ ሕግ በተቀመጡ ፍቺዎች መሠረት ቢሆንም ሀገራት ማን ይህንን መብት ለማግኘት ብቁ እንደሆነ የሚወስኑበት የየራሳቸው ሂደቶች አሏቸው

በአሜሪካ የሚገኙ ስደተኛ ማኅበረሰቦች ስለሰሞኑ ሁነት ምን ምላሽ ሰጡ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሜሪካ የሚገኙ ስደተኛ ማኅበረሰቦች በድንገተኛው የፖሊሲ ለውጥ ፍርሃት እንደተሰማቸው በአሜሪካ የሚገኙ አፍሪካውያን ስደተኞችን የሚረዳው 'አፍሪካን ኮሚዩኒቲስ ቱጌዘር' የፌደራል ፖሊሲ ኃላፊ ኒልስ ኪኗኒ ይናገራል።

"ሰዎች ምን መጠበቅ እንዳለባቸው እና ሕይወታቸውን እንዴት እንደሚያቅዱ ግራ ገብቷቸዋል" ይላል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የስደተኝነት መብት በማግኘት ሂደት ውስጥ ዓመታትን እያሳለፉ ባሉበት ጊዜ አፍሪካነሮች በፍጥነት የስደተኝነት ከለላ ማግኘታቸው "የሚረብሽ መልዕክት" እንደሚያስተላልፍም ይገልጻል።

"አሜሪካ የተገነባችው አደጋ ውስጥ ላሉ ሰዎች ጥበቃ የምትሰጥ ተቀባይ ሀገር ናት በሚል መሠረት ላይ ነው። አሁን ይህ አስተዳደር እያሳየን ያለው አቋም እነዚያን ከለላዎች የሚያገኙት እጅጉን ልዩ ጥቅም ያላቸው ሰዎች ናቸው የሚል ነው" በማለት ይናገራል።

ኪኗኒ፤ የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ "በዘረኝነት" የተቃኘ ነው ይላል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአፍሪካነሮች የጥገኝነት ማመልከቻ ከሌሎች ቡድኖች አንጻር ለምን በፍጥነት ተቀባይነት እንዳገኘ በተጠየቁበት ወቅት፤ ምክንያቱ ዘር እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ትራምፕ፤ "አርሶ አደሮች እየተገደሉ ነው፤ [የሚገደሉት ሰዎች] ነጭ ሆነው ተገኙ። ነገር ግን ነጭ ሆኑ ጥቁር ለእኔ ምንም ልዩነት የለውም" ብለዋል።

ኪኗኒ፤ የትራምፕ ውሳኔ አሜሪካ ውስጥ ዘረኝነትን ለመፍታት የተቀመጡ እንደ 'አፈርማቲቭ አክሽን' ያሉ እርምጃዎችን ወደኋላ ከመለሰው ከወቅታዊው የሀገር ውስጥ ፖሊሲ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ይገልጻል።

ቴንዳዪ አቺዉሜም በዚህ ይስማማሉ።

"የትራምፕ አስተዳደር የመሬት ሪፎርም ፕሮግራሞችን፣ አፈርማቲቭ አክሽንን አፍሪካነሮችን ለመለየት እንደተወሰዱ እርምጃዎች አድርጎ ይጠቅሳል" ይላሉ።

"ፀረ አፓርታይድ እርምጃዎችን ነጮች ላይ እንደተላለፉ ዘረኛ ፍርዶች አድርጎ ይገልጻል። ይህ አስገራሚ የእኩልነት እና ፀረ አድልዎ መሠረታዊ እሴቶችን ጥምዘዛ ነው" ሲሉ ይተቻሉ።