አሜሪካ የገቡ የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን የጥገኝነት ጥያቄ ከሌሎች በተለየ በተቀላጠፈ ሁኔታ ምላሽ እንደሚያገኝ ተገለጸ

የመጀመሪያው የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ቡድን አሜሪካ ገብቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የመጀመሪያው የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ቡድን አሜሪካ ገብቷል።

ዶናልድ ትራምፕ በስደተኛነት የሚቀበሏቸው የመጀመሪያው የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ቡድን አሜሪካ ገብቷል።

በቡድኑ ውስጥ ያሉት 49 ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ስደተኞች ሆነው እንደሚመዘገቡ ተገልጿል።

ትራምፕ አፍሪካነርስ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ "የዘር መድልዎ" ሰለባ ናቸው ብለው የተናገሩ ሲሆን፣ እነዚህ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን በአሜሪካ የጥገኝነት ጥያቄያቸው በተቀላጠፈ መንገድ መልስ ያገኛል ብለዋል።

ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን መድልዎ ደርሶባቸዋል የሚለውን ክስን ግን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አጣጥሎታል።

አሜሪካ ከተቀረው ዓለም የስደተኞችን ጥያቄ ላለመቀበል ወስና ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን እንደ ስደተኛ ለመቀበል መፍቀዷ ያለውን ተቃርኖ ሂውማን ራይትስ ዋች ተችቷል።

ከጆሀንስበርግ የተነሱት ነጭ ደቡብ አፍሪካውያኑ ዋሽንግተን ዲሲ ሲደርሱ በአሜሪካ ባለሥልጣናት ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በአሜሪካ የጥገኝነት ጥያቄ ረዥም ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም የነጭ ደቡብ አፍሪካውያኑ ግን ተፋጥኗል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም በዚህ ሂደት ውስጥ እጁ እንደሌለ ለቢቢሲ ገልጿል።

አፍሪካነርስ በመባል የሚታወቁት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ነጭ ዜጎችን አሜሪካ በስደተኛነት ልትቀበል መሆኑን ደቡብ አፍሪካ መተቸቷ ይታወሳል።

ለምን ለአፍሪካነርስ ቅድሚያ እንደተሰጠ የተጠየቁት ትራምፕ ነጭ አርሶ አደሮች ላይ ዒላማ መደረጋቸውንና "የዘር ጭፍጨፋ" መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

"አርሶ አደሮች እየተገደሉ ነው። እነዚህም ነጮች ናቸው። በእርግጥ ነጭ ወይም ጥቁር መሆናቸው ለኔ ልዩነት የለውም" ብለዋል።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ከትራምፕ ጋር በስልክ ሲነጋገሩ ይህ እውነት አለመሆኑን ገልጸዋል።

"ስደተኛ ማለት በፖለቲካ ምክንያት ወይም እስራትን ፈርቶ አልያም በምጣኔ ሃብት ወይም በሃይማኖት መድልዎ አገሩን ጥሎ መውጣት የተገደደ ነው" ብለዋል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ክሪስቶፈር ላንዱ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያኑን ለመቀበል አውሮፕላን ማረፊያ ሳሉ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ "ንግግሩ አይገርምም። የትኛውም አገር ዜጎቹ ስደተኛ መሆናቸውን አይቀበልም" ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካ የነጮችን መሬት ያለ ካሳ ነጥቃለች ሲልም የትራምፕ አስተዳደር ከሷል። ደቡብ አፍሪካ ይህንን አስተባብላለች።

በእርሻ አካባቢዎች በሚደርሱ ጥቃቶች ነጮች በተለየ ሁኔታ ዒላማ አለመደረጋቸውንም አክሏል።

ራማፎሳ ከወራት በፊት በፈረሙት ሕግ መሠረት በአንዳንድ ሁኔታዎች መንግሥት የእርሻ መሬትን ያለ ካሳ መውሰድ ይችላል።

ይህም "ለሕዝብ ጠቀሜታ" ሲባል መሆኑ ተገልጿል።

እስካሁን ግን የተነጠቀ መሬት እንደሌለ መንግሥት ገልጿል።

የደቡብ አፍሪካ የመሬት ሕግ በዘረኛ መድልዎ የተሞላና የአፓርታይድ ጊዜ ቅሪት በመሆኑ ትችት የሚሰነዘርበት ሲሆን ላለፉት ሦስት አሥርታት ባለመሻሻሉም ተነቅፏል።

ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን 90 ሕዝብ ሆነው 4 በመቶ ብቻ መሬት እንዳላቸው እአአ በ2017 የወጣ ሪፖርት ይጠቁማል።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያደገው የትራምፕ አማካሪ ኢሎን መስክ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ነጭ አርሶ አደሮች ላይ "የዘር ጭፍጨፋ" ፈጽሟል ሲል በተደጋጋሚ ይሰማል።

ነጭ ደቡብ አፍሪካውያኑ ዋሽንግተን ዲሲ ሲደርሱ በአሜሪካ ባለሥልጣናት ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ነጭ ደቡብ አፍሪካውያኑ ዲሲ ሲደርሱ በአሜሪካ ባለሥልጣናት ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዴሞክራቱ ግሪጎሪ ሚክስ የትራምፕ ውሳኔ "ዘረኛ ብቻ ሳይሆን ታሪክን ዳግመኛ ለመጻፍ የተቃጣ የፖለቲካ እርምጃ" ነው ብለዋል።

ለነጭ ደቡብ አፍሪካውያን በተለየ ሁኔታ ጥገኝነት ለመስጠት የተጀመረው ሂደት "መድልዎ የተሞላው" ስለሆነ ከአሜሪካ ፌደራል መንግሥት ጋር ከዚህ በኋላ አብራ እንደማትሠራ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን አስታውቃለች።

ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጠበቃ መሊሳ ኬኒ እንዳሉት የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን የጥገኝነት ጥያቄ ከሌሎች ስደተኞች ጉዳይ በፍጥነት እንዲታይ መወሰኑ "ፍትሐዊነት የጎደለውና ግብዝነት የተስተዋለበት" ነው።

120,000 ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥያቄያቸው ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ጉዳያቸው እንዲስተጓጎል ትራምፕ በመወሰናቸው የጠበቃዋ ቢሮ ትራምፕን ከሷቸዋል።

አፍሪካነሩ ጸሐፊ ማክስ ዱ ፔሬዝ እንዳለው ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ጥቃት እየደረሰባቸው ነው መባሉ "መሠረተ ቢስና ሙሉ በሙሉ ትርጉም የሌለው ነው" ሲል ተችቷል።

እአአ በ2024 በእርሻ ሥፍራ 44 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ ብቻ ናቸው ነጮች።

ደቡብ አፍሪካ ወንጀል ሲፈጸም በቆዳ ቀለም ለያይታ መረጃውን አታቀርብም። አብዛኞቹ የአገሪቱ አርሶ አደሮች ነጮች ሲሆኑ በእርሻው ላይ የሚሠሩት በብዛት ጥቁሮች ናቸው።

በአሜሪካ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢብራሒም ራሶል ከአሜሪካ መባረራቸው ይታወሳል። ትራምፕን "ነጮችን ተጎጂ ለማስመሰል የሚሞክሩ" በማለታቸው ነበር የተባረሩት።

ነጭ አፍሪካውያን ወደ አሜሪካ ገብተው የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት ዶናልድ ትራምፕ "ቅድሚያ" የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑ መገለጹን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ አሜሪካ "በፖለቲካ ምክንያት" የምትፈጽመው ይህ ድርጊት የደቡብ አፍሪካን "ሕገ መንግሥታዊ የዴሞክራሲ ሥርዓትን" የናቀ ነው ብሏል።

በደቡብ አፍሪካና አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ከገባ ወራት ተቆጥረዋል።