ስደተኞችን እያሳደደች ወዳለችው አሜሪካ የመጀመሪያዎቹ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ስደተኞች ተጓዙ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዶናልድ ትራምፕ በስደተኛነት የሚቀበሏቸው የመጀመሪያው የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ቡድን ወደ አሜሪካ አቀና።
በቡድኑ ውስጥ 49 ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ይገኙበታል። ትናንት እሑድ ከጆሀንስበርግ የተነሱት ነጭ ደቡብ አፍሪካውያኑ ዛሬ ሰኞ ዋሽንግተን ዲሲ ያርፋሉ። ከዚያም ወደ ቴክሳስ ይጓዛሉ።
አሜሪካ ከተቀረው ዓለም የስደተኞችን ጥያቄ ላለመቀበል ወስና ሃብታም ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን እንደ ስደተኛ ለመቀበል መፍቀዷ ያለውን ተቃርኖ ትችት ቀርቦበታል።
አፍሪካነርስ በመባል የሚታወቁት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ነጭ ዜጎችን አሜሪካ በስደተኛነት ልትቀበል መሆኑን ደቡብ አፍሪካ መተቸቷ ይታወሳል።
በደቡብ አፍሪካና አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ከገባ ወራት ተቆጥረዋል።
ባለፈው የካቲት ወር ትራምፕ አፍሪካነርስ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ "የዘር መድልዎ" ሰለባ ናቸው ብለው የተናገሩ ሲሆን፣ እነዚህ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ወደ አሜሪካ መጥተው መኖር የሚያስችላቸውን ውሳኔ አሳልፈዋል።
ደቡብ አፍሪካ የነጮችን መሬት ያለ ካሳ ነጥቃለች ሲልም የትራምፕ አስተዳደር ከሷል። ደቡብ አፍሪካ ይህንን አስተባብላለች።
በአሜሪካ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢብራሒም ራሶል ከአሜሪካ መባረራቸው ይታወሳል።
ነጭ አፍሪካውያን ወደ አሜሪካ ገብተው የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት ዶናልድ ትራምፕ "ቅድሚያ" የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑ መገለጹን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ አሜሪካ "በፖለቲካ ምክንያት" የምትፈጽመው ይህ ድርጊት የደቡብ አፍሪካን "ሕገ መንግሥታዊ የዴሞክራሲ ሥርዓትን" የናቀ ነው ብሏል።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ወደ አሜሪካ መሄድ የሚፈልጉ ሰዎችን እንደማያስቆም ገልጾ፤ በዚህ ሂደት ወደ አሜሪካ የሚወሰዱት ግለሰቦች የወንጀል ክስ ያለባቸው አለመሆናቸው መረጋገጥ እንዳለበት አሳስቧል።
ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን መድልዎ ደርሶባቸዋል የሚለውን ክስን ግን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አጣጥሎታል። በእርሻ አካባቢዎች በሚደርሱ ጥቃቶች ነጮች በተለየ ሁኔታ ዒላማ አለመደረጋቸውንም አክሏል።












