በአውስትራሊያ ከጥቃት አድራሽ ላይ መሣሪያ የቀማው 'የቦንዲ ጀግና' 1.6 ሚሊዮን ዶላር ተሰበሰበለት

በገንዘብ ማሰባሰቢያው ድረ ገጽ 'ጎ ፈንድ ሚ' ላይ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አዋጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በገንዘብ ማሰባሰቢያው ድረ ገጽ 'ጎ ፈንድ ሚ' ላይ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አዋጥተዋል።

በአውስትራሊያ አይሁዶች ላይ ጥቃት ከፈጸሙት የአንዱን መሣሪያ የቀማው 'የቦንዲ ጀግና' አሕመድ አል አሕመድ 1.65 ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቦ ተሰጠው።

አሕመድ በጥቃቱ ወቅት የአንደኛውን ጥቃት ፈጻሚ መሣሪያ ታግሎ ከቀማ በኋላ ተተኩሶበት በደረሰበት ጉዳት ሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ የተሰበሰበለትን የገንዘብ ስጦታ ተቀብሏል።

ቦንዲ የባሕር ዳርቻ ላይ በተከፈተው ተኩስ ቢያንስ 15 ሰዎች ተገድለዋል። 'የቦንዲ ጀግና' የተባለው አሕመድ ከጥቃት አድራሹ መሣሪያ ባይቀማ ኖሮ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ይሆን ነበር።

የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ አሕመድን ሆስፒታል ሄደው ጠይቀዋል። የሁለት ልጆች አባት የሆነው አሕመድ "የአገራችን ምርጥ ሰው ነው" ብለውታል።

በጎ ፈቃደኞች በበይረ መረብ ለአሕመድ ገንዘብ አሰባስበዋል።

ጥቃቱ ያለፈው እሑድ ሲፈጸም አሕመድ ከመኪና ጀርባ ተደብቆ ድንገት ከጥቃት አድራሹ ጀርባ በመዝለል ታግሎት መሣሪያውን ቀምቷል። ሁለተኛው ጥቃት አድራሽ አሕመድ ላይ በተደጋጋሚ ተኩሶበታል። አሕመድ እጁን ሊያጣም ይችላል።

በገንዘብ ማሰባሰቢያው ድረ ገጽ 'ጎ ፈንድ ሚ' ላይ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አዋጥተዋል።

በአውስትራሊያ የተፈጸመው ጥቃት በባሕር ዳርቻ የሐኑካህ በዓልን ሲያከብሩ የነበሩ አይሁዶችን ዒላማ ያደረገ ነበር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በአውስትራሊያ የተፈጸመው ጥቃት በባሕር ዳርቻ የሐኑካህ በዓልን ሲያከብሩ የነበሩ አይሁዶችን ዒላማ ያደረገ ነበር።

የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪው ዛከሪ ደርኒዎስኪ የጎ ፈንድ ሚ ገጹን ከከፈቱት አንዱ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሴንት ጆርጅ ሆስፒታል ውስጥ እየታከመ ላለው አሕመድ ትልቅ ቼክ ሲያስረክበው የሚያሳይ ቪድዮም ወጥቷል።

ዛከሪ 1.6 ሚሊዮን ዶላር እንደተሰባሰበ ለአሕመድ ሲነግረው፤ አሕመድ "ይገባኛል?" ብሎ ሲጠይቅ ይደመጣል።

ዛከሪም "እያንዳንዱ ሳንቲም ይገባሀል!" ይለዋል። አሕመድ እጁን ደረቱ ላይ አድርጎ "እጅግ በጣም አመሰግናለሁ" ሲል ይመልሳል።

"ገንዘቡን ላሰባሰቡልህ ሰዎች አንድ ነገር ማለት ብትችል ምን ትላለህ?" ሲል ዛከሪ አሕመድን ይጠይቃል።

"ሁሉንም መጥፎ ነገር እንርሳው እና ሁላችንም የሰዎችን ሕይወት ለማዳን እንሞክር። ሕይወት እናትርፍ። እኔ ሰዎቹን ሳድን ከልቤ ነው። ይቺ አገር ከዓለም ምርጧ ናት። ዝም ብለን ቆመን ማየት የለብንም። ሲበቃ ይበቃል! ፈጣሪ አውስትራሊያን ይጠብቅ" ሲል መልሷል።

"ቀኑ ውብ ቀን ነበር። ሁሉም ሰው በክብረ በዓሉ እየተደሰተ ነበር። ልጆች፣ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ታዳጊዎች ሁሉም ደስተኛ ነበሩ። ደስተኛ መሆን ደግሞ ይገባቸዋል" ሲልም አሕመድ ተናግሯል።

በጥይት ያልተጎዳ እጁን በድል አድራጊነት ከፍ አድርጎም "ኦዚ፣ ኦዚ፣ ኦዚ" በማለት ንግግሩን አጠናቋል።

'ኦዚ' አውስትራሊያውያንን ለመጥራት የሚውል ቃል ነው።

በቦንዲ የባሕር ዳርቻ ላይ የተፈጸመው ጥቃት "በኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ርዕዮተ ዓለም" ምክንያት የተነሳሳ ይመስላል ሲሉ፤ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል።

አይኤስ የ15 ሰዎችን ሕይወት ለቀጠፈው ጥቃት ኃላፊነት አልወሰደም።

ሆኖም ግን ፖሊስ ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ በተገኘ ተሽከርካሪ ውስጥ "በቤት የተሠሩ" የአይኤስ ባንዲራዎች ከተቀጣጣይ ፈንጂዎች ጋር ተገኝተዋል ብሏል።

ጥቃቱን በመፈጸም የተጠረጠሩት አባት እና ልጅ ናቸው። አባትየው በጥቃቱ ወቅት በፖሊስ በጥይት ሲገድል ልጁ ክፉኛ ቆለሏል። በግድያ ክስ ተመሥርቶበታል።

በጥቃቱ 42 ሰዎች ተጎድተዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው አይሁዳውያን 'ሐኑካህ' ወይም 'ቻኑካህ' በመባል የሚታወቀውን በዓል እያከበሩ በነበረበት ወቅት ነበር። ሐኑካህ የአይሁዶች 'የብርሃን በዓል' ነው።

የተገደሉ ሰዎችን ለማሰብ የተቀመጡ አበባዎች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተገደሉ ሰዎችን ለመዘከር የተቀመጡ አበባዎች

የ43 ዓመቱ አሕመድ አል አሕመድ ከጥቃት አድራሹ መሣሪያ ለመቀማት ሲታገል አይተው የተገረሙ ብዙዎች ናቸው። በማኅበራዊ ሚዲያ የተዘዋወረውን ቪድዮ ያዩም 'የቦንዲ ጀግና' እያሉ አሞካሽተውታል።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው አሕመድ የሸቀጥ ሱቅ አለው። እጁ እና ክርኑ ላይ በጥይት በመመታቱ የሕክምና እርዳታ እያገኘ ነው።

ቢልየነበሩ ቢል አክሀምን ጨምሮ ከመላው ዓለም ከ43 ሺህ በላይ ሰዎች ገንዘብ አሰባስበዋል።

አሕመድ ገንዘቡን ምን ላይ እንደሚያውለው አልገለጸም።

በየዓመቱ የሚከበረው ሐኑካህ ብዙውን ጊዜ ኅዳር ወይም ታኅሣሥ ላይ የሚውል ሲሆን ለስምንት ቀናት ይቆያል። ጥቃቱ የተፈጸመው የመጀመሪያው ቀን ዝግጅት በቦንዲ ባሕር ዳርቻ ሲካሄድ ነበር።

በዚህ ጥቃት ከተገደሉት መካከል የ10 ዓመት ታዳጊ ትገኝበታለች።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ፖሊስ ኮሚሽነር ማል ላንዮን እንዳሉት ታጣቂዎቹ የ50 ዓመት እና የ24 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አባት እና ልጅ ናቸው።

የ50 ዓመቱ ግለሰብ መሣሪያ የመታጠቅ ፈቃድ ያላቸው ሲሆን ስድስት መሣሪያዎች በግለሰቡ ስም መመዝገባቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ሁሉም መሣሪያዎች በቦንዲ ባሕር ዳርቻ ጥቃት ጥቅም ላይ እንደዋሉም ይታመናል።

ፖሊስ ድርጊቱ የአይሁድ ማኅበረሰብ ላይ የተቃጣ የሽብር ድርጊት ነው ብሎታል።

አሕመድ ከጥቃት አድራሹ ታግሎ መሳሪያውን መንጠቅ ችሏል
የምስሉ መግለጫ, አሕመድ ከጥቃት አድራሹ ታግሎ መሣሪያውን መንጠቅ ችሏል

አሕመድ ከጥቃት አድራሹ ጋር ትግል ሲገጥም የሚታይበት ምሥል በማኅበራዊ ሚድያ ላይ በሰፊው ተጋርቷል።

ከጥቃቱ አድራሾቹ መካከል አንደኛው ከአንድ አነስተኛ የእግረኛ ድልድይ አጠገብ ከሚገኝ ዛፍ ሥር ሆኖ ሲተኩስ ይታያል።

ከቆመ መኪና ጀርባ ተደብቆ የነበረው አሕመድ ከጥቃት አድራሹ ጀርባ መጥቶ በመታገል የጦር መሣሪውን ከነጠቀው በኋላ ወደ መሬት ገፍትሮ ጥሎት መሣሪውን ይደግንበታል። ጥቃት አድራሹ በማፈግፈግ ወደ ድልድዩ ይሸሻል።

አሕመድ መሣሪውን ዝቅ ያደርግና እሱ ጥቃት አድራሽ አለመሆኑን ለመጠቆም አንድ እጁን ከፍ አድርጎ ለፖሊስ ጥቆማ ይሰጣል።

ይህ ጥቃት አድራሽ ወደ ድልድዩ ካፈገፈገ በኋላ ሌላ መሣሪያ አንስቶ የተሰበሰበው ሕዝብ ላይ ሲተኩስ ታይቷል። ሌላኛውም ጥቃት አድራሽ ከድልድዩ ላይ ሆኖ ሲተኩስ ነበር።

የአሕመድ ዘመድ የሆነው ሙስጠፋ "እሱ ጀግና ነው። መቶ በመቶ ጀግና" ሲል ነው የገለጸው።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ሀገረ ገዢ ክሪስ ሚንስ ለአሕመድ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

"ይህ ግለሰብ የሚገርም ጀግና ነው። በእሱ ጀግንነት ምክንያት በርካታ ሰዎች በሕይወት መትረፋቸው ግልጽ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አንተኒ አልባኒዝም "አውስትራሊያውን አደጋን ተጋፍጠው ሌሎች ለመርዳት ሲሯሯጡ ተመልክተናል። እነዚህ አውስትራሊያውን ጀግኖች ናቸው። የእነሱ ጀግንነት የብዙዎችን ሕይወት ታድጓል" ብለዋል።

የ43 ዓመቱ አሕመድ የተወለደው በደቡብ ምዕራብ ሶሪያ፣ ኢድሊብ ውስጥ ነው። ለሥራ ወደ አውስትራሊያ የሄደው ከ20 ዓመት በፊት ነበር።