በአውስትራሊያ አባትና ልጅ በአይሁዶች ላይ በፈጸሙት ጥቃት 15 ሰዎች ሲገደሉ 42 ጉዳት ደረሰባቸው

ተሰብስበው ሐዘናቸውን እየገለፁ ያሉ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በአውስትራሊያ የተፈጸመው ጥቃት በባሕር ዳርቻ የሃኑካህ በዓልን ሲያከብሩ የነበሩ አይሁዶችን ዒላማ እንዳደረገ ፖሊስ ገልጿል

በአውስትራሊያ ቦንዲ የባሕር ዳርቻ በዓል ሲያከብሩ በነበሩ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ 15 ሰዎች ሲገደሉ 42ቱ ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸው።

ከተፈፀመው ጥቃት ጀርባ አባት እና ልጅ እንዳሉበት የአገሪቱ ባለሥልጣናት ይፋ አድርገዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው በሒብሪው ቋንቋ 'ሃኑካህ' ወይም 'ቻኑካህ' በመባል የሚታወቀውን በዓል እያከበሩ በነበረበት ወቅት ነበር። ሃኑካህ የአይሁዶች 'የብርሃን በዓል' ነው።

በየዓመቱ የሚከበረው ሃኑካህ ብዙውን ጊዜ በኅዳር ወይም ታኅሳስ ወር ላይ የሚውል ሲሆን ለስምንት ቀናት ይቆያል።

ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅትም የመጀመሪያው ቀን ዝግጅት በቦንዲ ባሕር ዳርቻ ላይ እየተካሄደ ነበር።

እሑድ ዕለት በተፈፀመው በዚህ ጥቃት የ10 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ 15 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 42 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ ገልጿል።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ፖሊስ ኮሚሽነር ማል ላንዮን ሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት ታጣቂዎቹ የ50 ዓመት እና የ24 ዓመት እድሜ ያላቸው አባት እና ልጅ ናቸው።

የ50 ዓመቱ ግለሰብ መሣሪያ የመታጠቅ ፈቃድ ያላቸው ሲሆን ስድስት መሣሪያዎች በግለሰቡ ስም መመዝገባቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ሁሉም መሣሪያዎች በቦንዲ ባሕር ዳርቻው ጥቃት ጥቅም ላይ እንደዋሉም ይታመናል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒስ ጥቃቱን "ፀረ ሴማዊ ድርጊት . . . በባሕር ዳርቻችን ላይ የተፈፀመ ሽብር" ሲሉ ገልጸውታል።

ጥቃቱን የፈፀመው የ50 ዓመቱ ግለሰብ በፖሊስ በተተኮሰባቸው ጥይት የተገደሉ ሲሆን የ24 ዓመቱ ልጃቸው ደግሞ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

በአውስትራሊያ የጅምላ ጥቃት የተለመደ አይደለም።

በቦንዲ የባሕር ዳርቻ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በአውሮፓውያኑ 1996 በአርተር ወደብ ላይ ከተፈፀመው እና 35 ሰዎች ከተገደሉበት ጥቃት ወዲህ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ነው።

ፖሊስ ጥቃቱን "የሽብር ጥቃት" ሲል ፈርጆታል።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ፖሊስ በቦንዲ የባሕር ዳርቻ አርከር ፓርክ ተኩስ እንደተከፈተ ሪፖርት የተደረገለት እሁድ ረፋድ 4፡23 አካባቢ ነበር።

ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ነበር ፖሊስ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ራሳቸውን ለመደበቅ የሆነ ቦታ እንዲጠለሉ እና ሌሎች ደግሞ ወደ አካባቢው እንዳይሄዱ ማስጠንቀቂያ የሰጠው።

በቢቢሲ የተረጋገጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም የተኩስ ድምጽ እየተሰማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየጮሁ እና እየሮጡ ከባሕር ዳርቻው ሲወጡ አሳይተዋል።

አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ሁለት ታጣቂዎች ወደ ባሕር ዳርቻው በሚወስደው አነስተኛ ድልድይ ላይ ቆመው ሲተኩሱ ታይተዋል።

ሌላ ምስል ላይ ደግሞ በአካባቢው የነበሩ አንድ ግለሰብ አንደኛውን ታጣቂ መሣሪያውን በመንጠቅ ጥቃቱን እንዲያቆም ሲከላከሉ አሳይቷል።ከዚያም ታጣቂው ወደ ድልድዩ በማፈግፈግ ሌላ ጥቃት ከፍቷል።

ጥቃቱን ለመከላከል የሞከሩት የፍራፍሬ መሸጫ ሱቅ ያላቸው እና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አሕመድ አል አሕመድ የተባሉ ግለሰብ እንደሆኑ የተለዩ ሲሆን ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ሕክምና ላይ ይገኛሉ።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒስ ጥቃቱን "ሰይጣናዊ የሆነ ፀረ ሴማዊ ድርጊት" ብለውታል።

" አውስትራሊያውያን ሌሎችን ለመርዳት ሲሉ እራሳቸውን አደጋ ውስጥ ሲከቱ ተመልክተናል። እነዚህ አውስትራሊያን ጀግኖች ናቸው። ጀግንነታቸው ሕይወትን ታድጓል" ሲሉም ጥቃቱን ለመከላከል የሞከሩ ግለሰቦችን አወድሰዋል።

የእስራኤሉ ፕሬዚደንት አይዛክ ሄርዞግ በበኩላቸው ጥቃቱን "በአይሁዶች ላይ የተፈፀመ እጅግ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት" ብለውታል። የኮመንዌልዝ አገራት መሪ የሆኑት ኪንግ ቻርልስም በተፈፀመው 'ፀረ ሴማዊ' የሽብር ጥቃት እጅጉን ማዘናቸውን ገልጸዋል።