ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"እናቴ መጠጊያዬ እና ኃያል ሰው ነበረች" ታዋቂዋ ደራሲ አሩንዳቲ ሮይ
በርካቶች 'ዘ ጋድ ኦፍ ስሞል ቲንግስ' በሚለው መጽሐፏ ያውቋታል ታዋቂዋን ሕንዳዊት ፀሐፊ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አሩንዳቲ ሮይ።
ይህ መጽሐፏ የሕንድን ማኅበረሰብ የተዋረድ መደብ (ካስት) አስከፊ ገጽታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
በተለይም በሕዝቡ ዘንድ "አይነኬ" ተብለው ከተፈረጁት ጋር የሚጀመር ፍቅር የሚያስከፍለው መስዋዕትነት ታይቶበታል።
ይህም ፍቅር፤ መደብ፣ ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ድንበሮችን ይዘላል የሚለውን መልዕክት ያስተላልፋል።
ታዋቂዋ ደራሲ እና ተሟጋች የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በዓለም ላይ ያደረሰውን ቀውስ፣ ድንበር የለሽ ኮርፖሬሽኖች ሰውን ምን ያህል ከሰብዓዊነት ማማ እንዳወረዱ በተለያዩ ጽሑፎቿ ትተቻለች።
የአገሯን የሕንድ መንግሥትንም በጽኑ ከሚተቹት አንዷ ናት።
ፍርሃት የሚባል አያውቃትም። የሕንድን የኒውክሌር ፕሮግራም፣ ታላላቅ ግድቦች የሚያስገብሩትን የሕይወት መስዋዕትነት ጽፋለች።
ሕንድ እና ፓኪስታን የሚወዛገቡባትን ካሽሚርን በተመለከተ ካሽሚር የሕንድ ግዛት ሆና አታውቅም የሚል አስተያየት ሰጥታ ውግዘት ደርሶባታል።
የሕንድ ባለሥልጣናት "የአገሯን ጥቅም አሳልፋ የሰጠች" በሚል ወቅሰዋታል።
መውቀስ ብቻም ሳይሆን ክስ ተመሥርቶባታል፤ መጽሐፏም ሕንድ በምታስተዳደራት ካሽሚር ግዛት እንዳይነበብ እግድ ተጥሎባታል።
ይህ የተከለከለው መጽሐፍ "አዛዲ" የተሰኘ ሲሆን፤ ሕንድ በካሽሚር ግዛት ስለገደለቻቸው እና ስለሰወረቻቸው ዜጎች የሚተርክ ነው።
ፀሐፊዋ ከሰሞኑ በእናቷ ላይ ያጠነጠነ ማስታወሻ ይዛ ብቅ ብላለች።
"በቅርቡ አንድ ሰው የእናቴ የተወችው ታላቅ ትሩፋት ምን እንደሆነ ጠየቀኝ፤ እኔም ጉልበተኝነት፣ ኃያልነት ብዬ መለስኩ" ስትል ከሰሞኑ ዴልሂ በነበረ አንድ ዝግጅት ላይ ተናግራለች።
የቡከር ሽልማት አሸናፊዋ እና የጭቁኖች ተሟጋች አሩንዳቲ "ማዘር ሜሪ ካምስ ቱ ሚ" የሚል እናቷን የሚዘክር መጽሐፍ አውጥታለች።
እናቷ ሜሪ መምህር፣ ላመነችበት ታጋይ፣ ፌሚኒስት፣ ኃያል (ጉልበተኛ)፣ አስፈሪ፣ ካመነችበት ነገር ወደ ኋላ የማትል፣ በርካቶችን ያነሳሳች ሰው ነበረች።
አሩንዳቲ ስትገልጻትም "መጠጊያዬ እና ማዕበል ነበረች" ትላታለች።
አሩንዳቲ ወደ ደራሲነት ሕይወት ከመግባቷ በፊት አርክቴክት፣ ተዋናይት፣ ፀሐፌ ተውኔት እና ፕሮዳክሽን ዲዛይን ነበረች።
የመጀመሪያ ድርሰቷ 'ዘ ጋድ ኦፍ ስሞል ቲንግስ' በአውሮፓውያኑ 1997 ታዋቂውን የቡከር ሽልማት ማሸነፍ ችሏል።
በ36 ዓመቷም ከከፍተኛ የዕውቅና ስፍራ ላይ አስቀምጧታል።
የመጽሐፉ ስድስት ሚሊዮን ቅጂዎች በመሸጡም ደራሲዋን ሃብታም አድርጓታል።
ሽልማቱም "በነጻነት የመኖር እና በራሴ ፍላጎት የመጻፍ ነጻነቷን" እንደሰጣት ተናግራለች።
ከዚያም በኋላ ለ20 ዓመታት ያህል በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፍትሕ፣ የዓለም ሥርዓት ላይ የሚያተኩሩ ትንታኔዎችን የያዙ ጽሑፎችን አውጥታለች።
እነዚህ ጽሑፎች ከፍተኛ ከበሬታን እንዲሁም ነቀፌታን አትርፈውላታል።
ከዓመታት በፊት ሌላ ልብወልድ መጽሐፏን ያሳተመችው አሩንዳቲ በቅርቡ ደግሞ እናቷን በሚዘክር የመጀመሪያ ማስታወሻዋ ብቅ ብላለች።
ይህ መጽሐፍ እናቷን በጥሩ (በቅድስና) መሳል ሳይሆን እውነታውን እንደወረደ የያዘ እንደሆነ የምትናገረው አሩንዳቲ "በእናት እና ልጅ መካከል ያለውን ትስስር የሚያሳይ፤ በሁለት ኃያላን ሴቶች መካከል ያለውን አክብሮት የተሞላበት ግንኙነት የሚያሳይ ነው" ትላለች።
የእናቷ ሜሪ ሮይ ታሪክ በራሱ የሚያስደንቅ ነው።
ጋብቻዋን ጥላ ወጥታ ዲግሪ እንኳን ሳይኖራት የራስዋን ትምህርት ቤት አቋቋመች።
ትምህርት ቤቷ የተቋቋመው ኬራላ ኮታያማ በተሰኘው የሕንድ ግዛት በአውሮፓውያኑ 1967 ነበር።
ሜሪ የክርስቲያን ሴቶችን የውርስ መብት ለማሰከበር ባደረገችው እልህ አስጨራሽ ክርክር በጠቅላይ ፍርድ ቤት ረትታለች።
የከፋ የአስም ሕመምተኛ ነበረች።
ለአስም ሕመምተኞች ለመተንፈስ የሚረዳትን 'ኢንሄለር' "ይዘው የሚከተሏት ትንንሽ ረዳቶች ነበሯት።"
በኮረብታዋማ ስፍራ ከመሠረተችው ትምህርት ቤት አገልግሎቷን ካቆመች ከአስር ዓመት በኋላ በ88 ዓመቷ በአውሮፓውያኑ 2022 ሕይወቷ አልፏል።
"አንዲት ልጅ በእናቷ ሞት ከምታዝነው በላይ እንደ ፀሐፊ በጣም አስደናቂ የሆነችውን ሴት ማጣቴ የበለጠ ያሳዝነኛል" ስትል አሩንዳቲ ስለእናቷ በመጽሐፏ ማስታወሻ ላይ አስፍራለች።
አሩንዳቲ ያደገችው 'ዘ ጋድ ኦፍ ስሞል ቲንግስ' መቼቱን ባደረገበት አይመነም በተሰኘች ኬራላ ውስጥ በምትገኝ በወንዝ በተከከበች መንደር ነው።
እሷ እና ወንድሟ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ነበር።
መንደሯ "አስገራሚ ሕይወት ባላቸው፣ ከተሜዎች፣ ዓለምን በተረዱ እና ኑሮ ባሸነፋቸው ነዋሪዎች የተሞላች ናት።"
አንዳንዶቹም በዚሁ ልብወለድ ውስጥ በገጸ ባህርይነት ተካትተዋል።
አሩንዳቲ በ18 ዓመቷ ከቤት ወጥታ ወደ ዴልሂ የሥነ ሕንጻ (አርክቴክቸር) ዩኒቨርስቲ አቀናች።
ለሦስት ቀናት በባቡር ተጉዛም ነበር በዩኒቨርስቲው የደረሰችው።
በቀጣዩ ዓመታትም እናቷን ጎብኝታም ሆነ ተነጋግረው አያውቁም ነበር።
"እናቴ ለምን ከቤት እንደወጣሁ አልጠየቀችኝም። አስፈላጊ አልነበረም። ሁለታችንም እናውቃለን። ጥሩ በሆነ የውሸት ምክንያት ተስማማን። ነገርኳት፤ በጣም ስለምትወደኝም እንድሄድ ፈቀደችልኝ" ብላለች።
አሩንዳቲ አባቷ በጽሑፏ ላይ የሳለችው እንደ "ሙት መንፈስ" ዓይነት ነው።
"ምሥጢራዊ እንግዳ ነበር፤ ሜሪ በቁም ሳጥኗ ከቆለፈችው እና አልፎ አልፎ እንድናየው በተፈቀደልን አልበም ቆንጆ መሆኑን አይተናል" ስትል አስፍራለች።
አባቷ በኮልካታ ስመ ጥር ከሆኑ ቤተሰብ የተወለደ ነበር።
ሆኖም ከቤተሰቡ ተራርቆ ወጥቶ የአልኮል ሱሰኛ እና ዘመድ አልባ ሆነ።
ሚስቱ እንደምትገልጸው "ምንም ሳይሠራ ተጎልቶ የሚውል ሰው ነበር። አያነብም፣ አያወራም፣ አያስብም" ትለዋለች።
መጨረሻም ኑሮውን በጎዳና ላይ እንዲሁም ለችግረኞች በተቋቋመ መጠለያ እና አሳም በተሰኘ የሻይ ፋብሪካ ሠርቷል።
ሜሪ ቁጣዋን ወደ ወንድ ልጇ አዞረች።
እህቱ በትምህርቷ ጎበዝ ሆና እሱ "አማካይ" ውጤት በማምጣቱ ማስመሪያ እስኪሰበር ድረስ ደብድባዋለች።
ወንድሟ ላሊት ኩመር ክርስቶፈር ሮይ በአሁኑ ወቅት የተሳካለት የባሕር ላይ ምግቦች የመላክ ንግድ ላይ የተሰማራ እንዲሁም ሙዚቀኛ ነው።
ሁኔታውን በበሩ የቁልፍ ክፍተት በኩል የተመለከተችው አሩንዳቲ አንድ ትምህርት ወሰደች።
"ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲሳካልኝ መጥፎ ነገር ይከተላል የሚል ስሜት አደረብኝ። ሲጨበጨብልኝ፣ ስደነቅ ሁልጊዜም ሌላ ዝምተኛ ሰው [ወንድሟ] በሌላ ክፍል ውስጥ አየተደበደበ እንደሆነ ይሰማኛል" ትላለች።
"እናቴ በአደባባይ ስትናደደብኝ፤ ሽምቅቅ ብዬ እጠፋለሁ" ስትል ታስረዳለች ኃያል ስለሆነችው እናቷ።
ሆኖም የእናቷ ሜሪም ሆነ የቤተሰቧ የቁጣ፣ የንዴት ታሪክ ብቻ አይደለም። "በአስቂኝ ቀልዶች የተዋዛ እንዲሁም የሚያስደንቅ ታሪክ ነው" የመንደሯም ታሪክ እንዲሁም።
ታዳጊ እያለች ጥርሷን ያስተካከለላት የጥርስ ሐኪም ይታወሳታል። "ከዚያ በኋላ ለዓመታት ልክ አንደ ከብት ባለቤት ወይም እንደ ፈረስ ገዥ ጥርሴን በአደባባይ፣ በማኅበራዊ ዝግጅቶች ላይ ክፈቺው ብሎ ይመረምር ነበር" ትላለች።
አንዳንድ አስገራሚ እና አስደንጋጭም ሁነቶች ገጥመዋታል።
በአንድ ወቅት በአውቶብስ ጉዞ ላይ ያገኘችው ወጣት የባንክ ሠራተኛ ከፍ ዝቅ አድርጎ ካያት በኋላ "በጣም ቆንጆ ነሽ [እንደ ጃፓኑ] የቦንሳይ ተክል። ላግባሽ" ያላት ከሚያስገርሟት ነገሮች አንዱ ነው።
ሙዚቀኞቹ ጆ ኮከር፣ ጂሚ ሄንድሪክስ፣ ጃኒስ ጆፕሊን፣ ዘ ቢትልስ ኤንድ እና ጂሰስ ክራይስ ሱፐር ስታር ትልቅ ስፍራ አላቸው።
በሥነ ሕንጻ ኮሌጅ መመረቂያ ሥራዋን ስትሠራ የሮሊንግ ስቶን ባንድ "ጊቭ ሚ ሼልተር" የሚለው ሙዚቃ ነበር ያለማቋረጥ የሚጫወተው።
ከቤት ለመውጣት እያሰላሰለች በነበረበት ወቅት ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም የሮክ ባንድ ዘ ቢትልስ "ሺ ኢዝ ሊቪንግ ሆም"ን እያጫወተች ነበር።
ዘፈኑም ከሕይወቷ ጋር ተገጣጠመ።
"ይህ ሙዚቃ ፈገግ አስባለኝ፤ ውስጤንም ነካኝ" ትላለች አሩንዳቲ ስለ ትዝታ፣ ፖለቲካ እና ሙዚቃ ምልከታዋን ለቢቢሲ ባጫወተችበት ወቅት።
ይህ የእናቷ ማስታወሻ የተለመደ የሕይወት ታሪክ አይደለም "ከእናቴ ጋር ያለኝን ግንኙነት እንዲሁም እንዲህ ዓይነት ፀሐፊ እንዳደረገችኝ የሚፈትሽ ነው" ትላለች።
ይህንን ማስታወሻ ለመጻፍ ሁለት ዓመት ወስዶባታል እናም መጻፍ በሕይወት ለመኖር ምክንያቷ እንደሆነ ታስረዳለች።
"ባልጽፍ ኖሮ ምን እንደምሆን አስባችሁታል? ይገለኝ ነበር" ትላለች።
አሩንዳቲ ፍርድ ቤት በመዳፈር አንዲት ምሽት እስር ቤት አሳልፋለች። እንዲሁም በ"ፀረ-አርበኝነት" ተከሳለች።
ትላልቅ ግድቦች፣ ካሽሚር፣ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ፣ የሕንድ የማኅበረሰብ ተዋረድ ሥርዓት፣ የፍትሕ ጥያቄ ሌሎችንም ለዓመታት ከመጻፏ አንጻር በዓለማችን ላይ ለውጥ አለመኖሩ ተስፋ ያስቆርጣት ይሆን?
"እኔ ከሽንፈት ጋር የምኖር ሰው ነኝ። ስለ እኔ ግን አይደለም። ዋናው ስላጻፍኳቸው ጉዳዮች ነው። በርካታ ጊዜ ተደፍጥጠዋል፤ ተመትተዋል። ስለዚህ ለውጥ ስላልመጣ ዝም እንበል? አይሆንም፤ በምንችለው መቀጠል አለብን" ትላለች።
"ማሸነፍ አለብን፤ ባይሆንም ትግላችን ሊቀጥል ይገባል።"
በዚህ ሳምንት መጽሐፏ በትውልድ ስፍራዋ ኬራላ፣ ኮቺ አዳራሽ ምረቃ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታድመው ነበር። አዳራሹ አልበቃ ብሎ ውጭ በተተከለ ስክሪን በርካቶች ምረቃውን እየተከታተሉ ነበር።
የመክፈቻ ዝግጅቱ የአሩንዳቲ ወንድም የዘ ቢትልስ ሙዚቃ በሆነው "ሌት ኢት ቢ" ነበር የተጀመረው።
በዚህም ኃይለኛ፣ የማትበገር የነበረችውን እናታቸው ሜሪን ዘክረዋል።