በአፍጋኒስታን ርዕደ መሬት የሟቾች ቁጥር 800 ተሻገረ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በአፍጋኒስታን የመሬት መንቀጥቀጥ የሟቾች ቁጥር 800 የደረሰ ሲሆን፤ የሕይወት አድን ስራው እንደቀጠለ ነው።
የአብዛኞቹ ሰዎች ሕይወት ያለፈው እሁድ ዕለት በሬክተር ስኬል 6.0 የተለካው የመሬት መንቀጥቀጥ መሀል ላይ በናጠው በኩናር ተራራማ ግዛት ነው።
በአደጋው መንደሮች መውደማቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የሟቾች ቁጥር ከዚህም ከፍ እንደሚል አስጠንቅቀዋል።
እስካሁን በርካታ አገራት እርዳታ ለማድረስ ቃል የገቡ ሲሆን አንዳንድ አካባቢዎች ለመድረስ አስቸጋሪ በመሆናቸው የአካባቢው የጤና ባለሙያዎች እርዳታ ለማቅረብ ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸዋል።
ይህ አደጋ የደረሰው አፍጋኒስታን በከባድ ድርቅ፣ በእርዳታ አቅርቦት መቋረጥ እና የዓለም የምግብ መርሃ-ግብር ያልተጠበቀ ባለው የረሃብ ቀውስ እየተፈተነች ባለችበት ወቅት ነው።
የመሬት መንቀጥቀጡ እሁድ ዕለት በአገሪቱ አምስተኛ ግዙፍ ከተማ በሆነችው ጃላላባድ ከተማ 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የደረሰ ነው።
ኩናር የተባለው አነስተኛ እርሻ መሬት ያለው ተራራማ ግዛት በጣም ከፍተኛውን ጉዳት ያስተናገደ አካባቢ ነው።
አካባቢው ባለፉት ቀናት ከፍተኛ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የደረሰበት በመሆኑም አብዛኞቹ ነዋሪዎች አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓል።
መንገዶች በመዘጋታቸው መንግሥት የሕይወት አድን ሥራውን በአየር ለማድረግ የተገደደ ሲሆን፤ ሂሊኮፕተሮች ጉዳት በደረሰበት አካባቢ መድረስ የቻሉት ሰኞ ጠዋት ነበር።
"ሙሉ መንገዶች ተጠርገዋል። በተራሮች ውስጥ ያሉ መንገዶች እስካሁን እንደተዘጉ ናቸው። ስለዚህ አሁን እኛ ለተጎዱ ሰዎች ከመድረስ ይልቅ ቅድሚያ የምንሰጠው በፍርስራሾች ውስጥ የሞቱትን መፈለግ ላይ ነው" ሲሉ በኩናር ግዛት አንድ የታሊባን ባለሥልጣን ተናግረዋል።
በፍርስራሾች ውስጥ ለሰዓታት የሕይወት አድን ሠራተኞችን ሲጠብቁ ከቆዩ በኋላ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች በርካታ መሆናቸው ተዘግቧል።
በሕይወት አድን ጥረቱ እየተሳተፈ ያለው ሳይድ ራሂም ምንም እንኳ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት መታደግ ቢቻልም በርካቶች በፍርስራሾች ውስጥ ታፍነዋል ተብሎ እንደሚታመን ተናግሯል።
የቀይ መስቀል ቃል አቀባይ ጆይ ሲንጋል ለአልጀዚራ በሕይወት የተረፉ ሰዎች ተጨማሪ መንቀጥቀጥ ይከሰታል ብለው በመስጋታቸው ወደ ቤታቸው ለመሄድ እንደፈሩ ገልጸው በአካባቢው ያለው ድንኳን በቂ አይደለም ብለዋል።
ቻይና፣ ሕንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሲውዘርላንድን ጨምሮ በርካታ አገራት እርዳት ለማቅረብ ቃል ገብተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ "በጣም በተጎዱ አካባቢዎች አጋሮቻችን ወሳኝ የሕክምና እና የአደጋ ጊዜ ግብዓቶን እንዲያደርሱ እናግዛለን" ብለዋል።
አፍጋኒስታን ለመሬት መንቀጥቀጥ እንግዳ አገር አይደለችም።
እ.አ.አ በ2022 እና በ2023 ህራት እና ፓኪታካ በተባሉ ግዛቶች በደረሰ ርዕደ መሬት ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
እሁድ ዕለት የደረሰው የመሬት መንቀጥቀት ክፉኛ አውዳሚ የሆነው ጥልቀት የሌለው በመሆኑ ሲሆን ንዝረቱ ከካቡል በ140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እና በጎረቤት አገር ፓኪስታን ድረስ ሰምቷል።
እ.አ.አ ነሐሴ 2021 ጀምሮ አፍጋኒስታን በሩሲያ ብቻ እውቅና በተሰጠው የታሊባን መንግሥት ቁጥጥር ስር ገብታለች።
በርካታ የረድኤት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አክራሪ እስላማዊ የሆነው ታሊባን ሥልጣን ሲጨብጥ አፍጋኒስታን ለቀው ወጥተዋል።















