ጀርመን ውስጥ የአንዲት ኤርትራዊት እጆች ተቆርጠው መንገድ ላይ መገኘታቸው ድንጋጤ ፈጠረ

የጀርመን ፖሊስ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Polizei NRW Hagen

በጀርመን ጥገኝነት ጠይቃ ነዋሪ የሆነች ማንነቷ ለጊዜው ያልተገለጸ ኤርትራዊት ዌስትፋሊያ ከተማ ኤ45 ጎዳና ላይ ከቀሪው ሰውነቷ ተለይተው ሁለት እጆቿ ተቆርጠው ተገኙ።

ሰኞ ማለዳ ላይ እጆቿ በአንድ አሽከርካሪ በጎዳና ላይ ታይተው ለፖሊስ የተጠቆሙት የዚህች ኤርትራዊት የተቀረው አካሏ የት እንዳለ፣ እሷ በሕይወት ትኑር አትኑር እስካሁን ድረስ ምንም የታወቀ ነገር የለም።

የስደተኛዋ ኤርትራዊት ማንነት በፖሊስ የተለያው አንድ ዛፍ ስር ተቆርጦ ከተገኘው እጇ ላይ በተወሰደ አሻራ ምክንያት መሆኑንም ፖሊስ ተገልጿል።

በጀርመን ኮሎን የሚኖሩ የኤርትራዊያን ኮሚኒቲ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አቶ ወደብ ቴዎድሮስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ክስተቱ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ድንጋጤን የፈጠረ ሲሆን፣ "በየሰዓቱ ሚዲያዎች እየዘገቡት ነው" ብለዋል።

ይህ አሰቃቂ ዜና ከተሰማ በኋላ በጀርመን በሚገኙ የኤርትራ ማኅበረሰብ ዘንድም ከፍተኛ ሐዘን እና ድንጋጤን የፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።

የአንድ ልጅ እናት የሆነችው እና ሁለቱ እጆቿ ከቀሪው አካሏ ተለይተው የተገኙት የኤርትራዊቷ ስደተኛ ባል እስከአሁን የት እንሚገኝ እንዳልታወቀ የጀርመን ጋዜጦች ዘግበዋል።

ሰኞ ዕለት በወጡ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች የዚች 32 ዓመት ሴት፣ ልጅ ነው የተባለ የሦስት ወር ሕጻን እጆቿ ከተገኙበት ስፍራ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ገዳም ደጅ በሕጻን ጋሪ ላይ ብቻውን ተገኝቷል።

እጆቿ ተቆርጦ የተገኘችው ኤርትራዊት ጥገኝነት ለመጠየቅ ከኤርትራ የመጣች እንደሆነች እና በቦን ከተማ የጥገኝነት ጠያቂዎች መጠለያ ማዕከል ውስጥ ተመዝግባ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከእናቱ ተለይቶ የተገኘው ጨቅላ ልጇ በአሁኑ ጊዜ በልጆች ማቆያ ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገለት እንደሆነ ታውቋል።

የኤርትራዊቷ ሴት እጆች ወድቀው የተገኘነት ቦታ ትኖርበት ከነበረው አካባቢ ርቆ የሚገኝ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል።

ይህ ክስተት የተሰማው አንዲት ሴት እሑድ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ለሰኞ አጥቢያ ያልተለመደ ነገር መንገድ ላይ ተመለከትኩ ብላ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠቷ ነው።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ቦታው ሲደርሱ ሁለት የተቆረጡ እጆች ዋና መንገድ ዳር ተጥለው አግኝተዋል።

ጥቆማው የደረሳቸው የፖሊስ አባላት በኦልፔ-ሱድ እና በፍሩደንበርግ መገንጠያ መካከል እጆቿን ያገኙበትን ሥፍራ ለትራፊክ ዝግ አድርገውት ቆይተዋል።

በኋላ ላይ በወጡ ዘገባዎች መሠረት ሁለቱ የተቆረጡ እጆች የአንዲት ሴት ናቸው ሲሉ የጀርመን ጋዜጦች ዘግበዋል።

የግዛቱ ዐቃቤ ሕግ ምን ያህል የአካል ክፍሎች እንደተገኙ በትክክል ባይናገርም፣ የጣት አሻራ ምርመራው ግን የኤርትራዊት ሴት መሆኑን ማረጋገጡን የመገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል።

እጆቿ ብቻ እንዴት ተቆርጠው ሊገኙ ቻሉ የሚለው ገና አሁንም ድረስ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ቢሆንም፤ ነገር ግን ቅድመ ምርመራዎች እንደሚያሳዩት ክስተቱ በመኪና አደጋ ያጋጠመ ሊሆን እንደማይችል ነው።

በዚህ የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ ከኤርትራዊያን ቤተሰብ የተወለደ አንድ የ6 ዓመት ሕጻን ከትምህርት ቤት ለቀናት ጠፍቶ ከቆየ በኋላ በዊልበርግ አቅራቢያ በሚገኝ ወንዝ ውስጥ ሞቶ መገኘቱ ይታወሳል።

በ2024 የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳስታወቀው በተለያዩ አገራት ከ683 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ተመዝግበዋል።

ጀርመን ኤርትራውያን ስደተኞችን በመቀበል በአውሮፓ ቀዳሚ አገር ነች።

አብዛኞቹ እነዚህ ስደተኞች አገራቸውን ለቅቀው ወደ ጎረቤት አገራት ለመሻገር ከዚያም አደገኛውን የሰሃራ በረሃ እና የሜዲትራኒያን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመሄድ ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ።