ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራይ ሲኖዶስ አክሱምን "ቅድስት ከተማ" ብሎ መሰየሙን እና ይህንኑ የሚያሳዩ "ሕጎችን እያወጣ" መሆኑን አስታወቀ
የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክስርስቲያን ሲኖዶስ ባደረገው ጉባኤ፤ የጥንታዊቷ አክሱም መጠሪያ "ቅድስት አክሱም ጽዮን ከተማ" እንዲሆን መወሰኑን አስታወቀ።
ቤተ ክርስቲያኗ፤ ይህንን ውሳኔ ተከትሎ በከተማዋ እንደ "መጠጥ እና ጫት" ሽያጭ ያሉ ተግባራት ላይ ክልከላ እንዲጣል እንደምትፈልግ እንዲሁም "የቅድስና ምልክት እንድታሳይ የሚያደርጉ ሕጎችን" እያወጣች መሆኑን ገልጻለች።
ውሳኔው ይፋ ከተደረገበት ሚያዝያ 28/2018 ዓ. ም. አንስቶ ከተማዋ በአጠቃላይ ቅድስት ተብላ እንደምትጠራ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክሱም ከዚህ ቀደም ያላት ክብር እንዳለ ሆኖ በጠቅላላው ቅድስት ከተማ እንድትባል የሚያስችል ጥናት ቀርቦ ውሳኔው እንደተላለፈ ገልጸዋል።
አክሱም ከተማ "ቅድስት ከተማ" በሚል በተለምዶ ትጠራ እንደነበር ጠቅሰው የአሁኑ ውሳኔ መጠሪያውን "ሕጋዊ" እንደሚያደርገው አስረድተዋል።
አክሱም "ሕገ ልቦና፣ ሕገ ኦሪት፣ ሕገ ወንጌል ጠብቃ የኖረች የረዥም ዓመት የክርስትና ደሴት" ስለሆነች "ቅድስት" መሆኗን ብፁዕ አቡነ አረጋዊ አስረድተዋል።
"ብዙ መንበረ ታቦተ ጽዮናት፣ መንበረ ጽላት፣ መንበረ ሳምራ፣ መንበረ ብዙ ቅዱሳን ስለሆነች ያላት ክብር እንዳለ ሆኖ ከአሁን በኋላ ደግሞ ከተማዋን ጠቅላላ ቅድስት የሚያስብላት ተጠንቶ ያለው ግብዓት ቀርቧል" በማለትም አብራርተዋል።
"ከተማዋ በዚህ ዘመን ያላትን ቅድስና ቀጣዩ ትውልድ ይዞ እንዲሄድ" በሚል አጠቃላይ ከተማዋ ቅድስት ተብላ እንድትጠራ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን አክለዋል።
የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በተለዩት አባቶች የተመሠረተው የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክስርስቲያን ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ እንደተናገሩት፤ አክሱም በአጠቃላይ ቅድስት ከተማ እንድትባል በመወሰኑ ምክንያት መጠጥ እና ጫትን የመሳሰሉት ላይ ሙሉ በሙሉ ክልከላ ለመጣል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር እያደረጉ ነው።
"ለሆቴሎችም ሥርዓት የሚወጣበት ሕግ እያወጣን ነው. . . ከተማይቷ ቅድስት ከተባለች የቅድስና ሥራ ሊሠራ ይገባል። ጠቅላላ ከተማዋ የቅድስና ምልክት እንድታሳይ የሚያደርጉ ሕጎች እያወጣን ነው" ብለዋል።
የከተማዋን "ጥንታዊ ታሪክ፣ ማንነቷን፣ ክብሯን ዓለም እንዲያውቀው" ማድረግም ዓላማቸው መሆኑን አክለዋል።
አሁን ላይ ከተማዋ "ለቅድስና የሚበቁ ነገሮች ማድረግ ስላለባት" ቤተ ክርስቲያኒቷን፣ ሕዝቧን እና ምዕመኗንም "በደንብ እንደሚያስተምሩ" ተናግረዋል።
የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አክሱም "ቅድስት ከተማ" እንድትባል ውሳኔ ያሳለፈው በከተማዋ የሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ጋር የተያያዘ ውዝግብ በድጋሚ በተስተዋለበት ወቅት ነው። በከተማዋ የሚገኙ መስጊዶች ከሚያዝያ መጀመሪያ አንስቶ የስግደት ሥነ ሥርዓታቸው መስተጓጎሉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሚያዝያ 7/2028 ባወጣው መግለጫ፤ በአክሱም ከተማ የሚገኙ ሙስሊሞች "ድብደባ እንደተፈጸመበባቸው" እና የመስጊድ ንብረቶች "በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ ጉዳት" እንደደረሰባቸው አስታውቆ ነበር።
ከዚህ ቀደምም በከተማዋ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የመስጊድ ግንባታ እና የሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሃይማኖታዊ አለባበስ ጋር በተያያዙ ውዝግቦች ተስተውለው ነበር።
ይህንን ተከትሎ፤ ከተማዋን ቅድስት ብሎ መሰየም በሙስሊም ነዋሪዎች ዘንድ ሊፈጥር የሚችለው ቅሬታ አልያም ቅራኔ ስለመኖሩ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ተጠይቀዋል።
ዋና ፀሐፊው፤ "ከአክሱም ኅብረተሰብ ጋር በሰላም በፍቅር የሚኖሩ ወንድማማቾች ናቸው። የተለየ ሐሳብ ይኖራቸዋል ብዬ በግሌ አላምንም" ሲሉ መልሰዋል።
አክሱም "ቅድስትነቷን፣ ታላቅነቷን፣ ጥንታዊነቷን እና ቅርስነቷን" በማመን የሁለቱ ሃይማኖት ተከታዮች ማኅበራዊ መስተጋብር እንዳላቸው ጠቅሰው "ቅድስት በመባሏ የተለየ ድጋፍ ይሰጣሉ እንጂ የሚቃወሙት ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም። ካለ ግን ከሙስሊም ኅብረተሰቡ ጋር መነጋገር ይቻላል" በማለትም አስረድተዋል።
ከአንደኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ እስከ 9ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የአክሱም ሥርወ መንግሥት ዋና ከተማ የነበረችው ጥንታዊቷ አክሱም፤ የአክሱም ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መገኛ ናት።
በ4ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ኢዛና ዘመን እንደተመሠረተች ታሪክ የሚመሰክርላት የአክሱም ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን ታቦት መገኛ መሆኗም ይታመናል።
አክሱም ከተማ ከ1700 ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸው የሚነገርላቸው የአክሱም ሐውልቶች መገኛም ናት።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል የአክሱም ሐውልት ተጠቃሽ ነው።
የአክሱም ሰው ሠራሽ አርኪዮሎጂ ሥፍራም በዚህ መዝገብ ውስጥ ተካትቷል። ይህ ሥፍራ የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት፣ እንዲሁም ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍን የሚወክል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ጥንታዊ መዲና አክሱም፤ የኃያል መንግሥት ዋና ከተማ፣ የሃይማኖት ማዕከል እንዲሁም ጥንታዊ ሃይማኖታዊ መንግሥትን በአፍሪካ ውስጥ የመሠረተች ተብላ በተመራማሪዎች ትጠቀሳለች።
የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ አክሱምን ቅድስት ከተማ ብሎ ከመሰየም በተጨማሪ ዐፄ ዮሐንስ የክብር ሰማዕትነት እንዲሰጣቸው መወሰኑን ዋና ፀሐፊው ተናግረዋል።
ዐፄ ዮሐንስ "ለአገራቸው አንድነት" እንዲሁም "አብያተ ክርስቲያናት በማሠራት" ለአገሪቱ ትልቅ ውለታ መዋላቸውን የሚገልጹት ዋና ፀሐፊው፤ "በሰማዕትነት ስላረፉ ቤተ ክርስቲያን ልታስባቸው፣ ልትዘክራቸው ይገባል" ብለዋል።
"ለአገርም፣ ለቤተ ክርስቲያንም የሠሩት ውለታ ትልቅ ነው፤ እንዲህ ያሉ ደጋግ ሰዎችን አለማስታወስ ንፉግነት ነው" ያሉት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፤ ዐፄ ዮሐንስ ሰማዕት ተብለው እንዲጠሩ መወሰኑን አስረድተዋል።
የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፋቸው አጠቃላይ ውሳኔዎች 12 ሲሆኑ፤ በኢየሩሳሌም ገዳማት የሚያገለግሉ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ መነኮሳት ጉዳይም በዚህ ከተካተቱት አንደኛው እንደሆነ ተናግረዋል።
"የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከደመወዛቸው፣ ከሚቀድሱበት አገልግሎታቸው ለስድስት ዓመታት ታግደዋል" ያሉት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ለዚህ መፍትሔ እንዲሰጥ አሳስበዋል።