ሩሲያ በፕሬዝዳንቷ ላይ የእስር ማዘዣ ያወጡትን ዐቃቤ ሕግ ‘በወንጀል እፈልጋቸዋለሁ’ አለች

ዋናው ዐቃቤ ሕግ ካሪም ካህን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ የእስር ትዕዛዝ እንሲያወጣ ያደረጉት ዋናው ዐቃቤ ሕግ ካሪም ካህን

በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ያወጡትን የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ዋና ዐቃቤ ሕግን ሩሲያ በወንጀል ከምትፈልጋቸው ሰዎች ዝርዝሯ ውስጥ አስገባች።

ይህ የሩሲያ እርምጃ የተገለጸው ፍርድ ቤቱ በዩክሬን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ይፋ ካደረገ ከሁለት ወራት በኋላ ነው።

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ቅዳሜ ዕለት በሰጠው ምላሽ፣ ዋና ዐቃቤ ሕጉን ሩሲያ በተፈላጊ ወንጀለኞች ዝርዝር ውስጥ ማስገባቷ ፍርድ ቤቱን ከጀመረው ሂደት “የማይገታው” መሆኑን አሳውቋል።

ፍርድ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ የሩሲያ እርምጃ “ከተፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች አንጻር በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዳይወጣ” ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ ነው ብሎታል።

የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) አባል ያልሆነችው ሩሲያ፣ በፕሬዝዳንቷ ላይ የወጣውን የእስር ማዘዣ ተቀባይነት የሌለው “ውድቅ” ነው በማለት ገልጻዋለች።

ባለፈው መጋቢት ወር የወጣውን የእስር ማዘዣ ያዘጋጁት ብሪታኒያዊ ዜግነት ያላቸው ጠበቃ ካሪም ካህን ናቸው። በእስር ማዘዣው ላይ ፕሬዝዳንት ፑቲን በሕገወጥ መንገድ ልጆችን ከዩክሬን ወደ ሩሲያ አግዘዋል በሚለው ላይ በማተኮር በጦር ወንጀል ተከሰዋል።

ከፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ የሩሲያ የህጻናት መብቶች ኮሚሽነር የሆኑት ማሪያ ልቮቫ-ቤሎቫም ተመሳሳይ ክስ በፍርድ ቤቱ ቀርቦባቸዋል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሩሲያ ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ከ16,000 በላይ ልጆች በኃይል ወደ ሩሲያ ተወስደዋል።

ለዚህም አይሲሲ ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ኮሚሽነር ልቮቫ-ቤሎቫ ምክንያታዊ በሆነ መነሻ በግለሰብ ደረጃ ለወንጀሉ ተጠያቂ ናቸው ብሎ በማመኑ ነው የእስር መዘዣ እንዲወጣባቸው ያደረገው።

የሩሲያ መንግሥት በበኩሉ ያቋቋመው የምርመራ ኮሚቴ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዋና ዐቃቤ ሕግ ካሪም ካህን “ንጹህ በሆነ ግለሰብ ላይ የወንጀል ክስ በመመሥረት” ምርመራ እንደሚጀምር በዚህ ሳምንት አስታውቋል።

ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ ውስጥ የሚገኘው ፍርድ ቤቱ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ “በአይሲሲ ዐቃቤ ሕግ ላይ ሕገወጥ እና ተቀባይነት የሌለው ጫናን ለማሳደር በሚል እየተወሰደ ያለው እርምጃ በጽኑ እንዳሳሰበው” አመልከቷል።

የሩሲያ ውሳኔ “ተቀባይነት የሌለው” እንደሆነ የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፣ ይህም “የተሰጠውን ኃላፊነት በነጻነት ከመወጣት” እንደማያግደው ገልጿል።

በሩሲያ የተፈላጊዎች ዝርዝር ውስጥ ስማቸው የሰፈረው የፍርድ ቤቱ ዋና ዐቃቤ ሕግ ካሪም ካህን በሩሲያ ውሳኔ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ የህጻናት እና የግጭት ጉዳዮች ተወካይ የሆኑት ቨርጂኒያ ጋምባ ሞስኮ ውስጥ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው የሩሲያ የህጻናት ኮሚሽነር ልቮቫ-ቤሎቫ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል በሚል ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።

ኮሚሽነሯ ከተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን ጋር ተገናኝተው መወያየት ሳይሆን ዘ ሄግ ፍርድ ቤት ነው መቅረብ ያለባቸው በማለት የመብት ተቆርቋሪ ቡድኖች ጉዳዩ እንዲጣራ ጠይቀዋል።