ኢትዮጵያ፡ በህገወጥ የወርቅና ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ከ90 በላይ የውጭ ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Federal Police
ፈቃድ ሳይኖራቸው በወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ ከ90 በላይ የውጭ ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጸጥታ ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታወቀ።
በህገወጥ መንገድ በማዕድን ፍለጋ ተሰማርተዋል የተባሉት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉት በጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ትናንት መጋቢት 28/2015 ዓ.ም በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
ከየት አገር እንደመጡ በመግለጫው ያልተጠቁሱት የውጭ አገር ዜጎች በማዕድን በበለጸጉት ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በህገወጥ መንገድ ከመሰማራታቸው በተጨማሪ ወደ አገሪቱ የገቡትም አስፈላጊ ሰነዶችን ሳያሟሉ እንደሆነ ተጠቅሷል።
“የመግቢያ ቪዛ፣ የጸና ሰነድ እንዲሁም የመኖሪያ ፈቃድ” የላቸውም የተባሉ 45 የውጭ ዜጎችና ሶስት ኢትዮጵያውያን በጋምቤላ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እንደተከፈተባቸው ተገልጿል።
በተመሳሳይም ኢትዮጵያ ለውጭ ዜጎች የምትጠይቀውን አስፈላጊ ሰነዶች አላሟሉም የተባሉ 47 የውጭ ዜጎች፣ ዘጠኝ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማህበራት እንዲሁም ሰባት ኢትዮጵያውን በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ መከፈቱንም የጋራ ግብረ ኃይሉ በትናንት መግለጫ አስታውቋል።
በህገወጥ መንገድ የማዕድን ፍለጋ ላይ ተሰማርተው ነበሩ የተባሉ የውጭ ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው የተባሉት ኢትዮጵያውያን እና ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማህበራት በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት በአካካቢው ኅብረተሰብ ጥቆማ መነሻ እንደሆነ መግለጫው ጠቅሷል።
ይህንንም ተከትሎ ግብረ ኃይሉ ባደረገው ክትትልና ዘመቻ መሆኑም ተገልጿል።
“አገሪቱ ከማዕድን ዘርፉ ተጠቃሚ እንዳትሆን በሕገ-ወጥ መንገድ ማዕድናትን በማውጣት በኮንትሮባንድ ከሀገር እንደሚያወጡ ደርሸበታለሁ” ብሏል ግብረ- ኃይሉ በመግለጫው
በጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ በህገወጥ መንገድ በማዕድን ፍለጋ ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ የውጭ ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር መዋል ጅማሮ እንደሆነና በነዚህ ክልሎችም ተወስኖ እንደማይቀርም ነው የጋራ ግብረ ኃይሉ ያሳሰበው።
በቅርቡ በጋምቤላ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በህገወጥ መንገድ ማዕድናትን ከኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገራት እያስተላለፉ ነበር የተባሉ 83 የውጭ ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ መናገራቸው ተዘግቧል።
ምክትል ኮሚሽነሩ ከሰሞኑ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በህገወጥ መንገድ በማዕድናት ቁፋሮ ተሰማርተዋል የተባሉት የውጭ ዜጎች በየአገራቸው በተለያዩ ወንጀሎች የሚፈለጉ ግለሰቦች ናቸው ሲሉ መናገራቸውም ተገልጿል።
በህገወጥ መንገድ ተሰማሩ የተባሉት የውጭ ዜጎች “የማዕድን ዝርፊያ ሲፈጽሙ” ነበር የተባለው ከኢትዮጵያውያን ጋር በመተበባር ሲሆን ከአገር ሊወጡ ሲሉም በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል። በዚሁ ማብራሪያ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከማዕድን ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በየአመቱ አገኛለሁ የሚል ዕቅድ እንደነበረውም ተጠቅሷል።












