ሩሲያ ነዳጇ ከተቀመጠለት የዋጋ ጣሪያ በላይ እንዳይሸጥ ለተስማሙ አገራት የነዳጅ ሽያጭን አገደች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩሲያ ምዕራባውያን አገራት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የተስማሙበትን የዋጋ ጣሪያ ለሚጠቀሙ አገራትና ኩባንያዎች የነዳጅ ሽያጭን አገደች።
የዋጋ ገደቡ በቡድን 7 አገራት፣ አውስትራሊያ እና አውሮፓ ኅብረት ተግባራዊ መሆን የጀመረው በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።
የዋጋ ገደቡ አገራት የሩሲያን ነዳጅ በበርሜል ከ60 ዶላር በላይ እንዳይገዙ ይከለክላል።
ሩሲያ አሁን ላይ የዋጋ ገደብ ለጣሉ አገራትና ኩባንያዎች ነዳጇ እና የነዳጅ ውጤቷ እንደማይሸጥ አስታውቃለች።
ይህ ፕሬዝዳንታዊ አዋጅ እንደሚለው እገዳው ከፈረንጆቹ የካቲት መጀመሪያ ጀምሮ ለአምስት ወራት ተግባራዊ ይሆናል።
በእገዳው ለተካተቱ አገራት ነዳጅ ለማቅረብ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ልዩ ፈቃድ ሊሰጡ አንደሚችሉ አዋጁ ጨምሮ አመልክቷል።
የቡድን 7 አገራት፣ ሞስኮ ከነዳጅ የምታገኘው ገቢ በዩክሬን የምታካሂደውን ጦርነት ለመደገፍ እንዳይውል በሚል የነዳጅ ዋጋ ገደብ የማስቀመጥ ሃሳቡን ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረቡት መስከረም ወር ላይ ነበር።
ምንም እንኳን ከወረራው በኋላ የምዕራባውያኑ የሩሲያ ነዳጅ ፍላጎት የቀነሰ ቢሆንም የነዳጅ ዋጋ በመናሩና በሕንድና በቻይና ጭምር ነዳጇ ተፈላጊ በመሆኑ የሩሲያ ገቢ ከፍተኛ ሆኖ ቆይቷል።
የአውሮፓ ኅብረት የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ በባህር በኩል እንዳይገባ የሚከለክለው እቀባ አሁንም ተግባራዊ እየተደረገ ነው። ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና ሌሎች አገራትም በተመሳሳይ ቃል ገብተዋል።
የነዳጅ ዋጋ ገደቡን የማስቀመጡ ዓላማ ሩሲያ ከነዳጅ የምታገኘውን ገቢ እንዲቀንስ ማድረግ ነው።
ይህም ከ60 ዶላር በላይ የሚሸጥ ማንኛውም የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ቡድን 7 እና የአውሮፓ ሕብረት ታንከሮችን፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን እና የብድር ተቋማትን በመጠቀም እንዳይላክ ያግዳል።
ዋና ዋናዎቹ ዓለም አቀፍ የመርከብ ድርጅቶች እና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተቀማጭነታቸው በቡድን 7 አገራት ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ የዋጋ ገደቡን "የሩሲያን ኢኮኖሚ ለማውደም በቂ ያልሆነ ደካማ ሃሳብ" ሲሉ አጣጥለውታል።
የሩሲያ የገንዘብ ሚኒስትር አንቶን ሲሉያኖቭ ማክሰኞ ዕለት የነዳጅ ዋጋ ገደቡ ከውጭ ንግድ የሚገኘውን ገቢ በመቀነሱ የሩሲያ የበጀት እጥረት በ2023 ከታቀደው ጂዲፒ 2 በመቶ በላይ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
አሁን ላይ አንድ በርሜል ነዳጅ በ80 ዶላር እየተሸጠ ሲሆን መጋቢት እና ሰኔ ላይ ከፍተኛ ሆኖ ከተመዘገበው 120 ዶላር ዝቅ ብሏል።












