ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬን በማዕከላዊ ኪዬቭ የራሷን ድሮን መትታ ጣለች
የዩክሬን አየር ኃይል በማዕከላዊ ኪዬቭ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል ያለውን የራሱን ድሮን (ሰው አልባ አውሮፕላን) መትቶ ጣለ።
የአየር መከላከያ ኃይሉ ሐሙስ ምሽት በፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት አቅራቢያ ድሮኑን መትቶ ለመጣል ሲሞክር ከ15 እስከ 20 ደቂቃ የቆዩ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንታዊ የሥራ ኃላፊ አንደሬይ ኢርማርክ መጀመሪያ ላይ ተመትቶ የተጣለው የጠላት ድሮን ነው ብለው ነበር።
ሆኖም በኋላ ላይ አየር ኃይሉ የዩክሬን ድሮን መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ተመትቶ የተጣለው “አላስፈላጊ ሁኔታዎችን” ለማስወገድ ነው ብሏል።
አየር ኃይሉ በመግለጫው እንዳለው ባራክታር ቲቢ2 ዩኤቪ (ሰው አልባ የአየር ላይ በራሪ ድሮን) በኪዬቭ ግዛት ውስጥ በታቀደለት በረራ ላይ መቆጣጣር ተስኖት ነበር።
በመሆኑም በዋና መዲናዋ ድሮኑ ከቁጥጥር ውጭ በመገኘቱ ሌላ ያልተጠበቀ ጉዳት ያስከትላል በሚል መትቶ ለመጣል ውሳኔ ላይ መደረሱንም ገልጿል።
በወደቀው ድሮን ምክንያትም የጠፋ የሰው ሕይወትም ሆነ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል መግለጫው።
“የሚያሳዝን ነው፤ ግን ቴክኖሎጂ ነው እንዲህ ዓይነት ክስተቶች ያጋጥማሉ” ያለው መግለጫው ድሮኑን መቆጣጠር ያልተቻለው ምናልባት በቴክኒክ ብልሽት ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
ድሮኑን መትቶ ለመጣል ሲደረግ የነበረውን ጥረት የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተጋርተዋል።
ድሮኑ በመጨረሻም ሲወድቅ የደስታ ጩኸት ተሰምቷል።
የከተማዋ ጦር አስተዳዳር ኃላፊ ስርሂይ ፖፕኮ፣ ድሮኑ በወደቀበት በከተማዋ የምዕራብ አካባቢ ሶሎምያንስኪይ በተባለው ስፍራ በነበረ ሕንጻ ላይ ሲወድቅ የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተናግረዋል።
ከስተቱ ያጋጠመው ረቡዕ ዕለት ዩክሬን በክሬሚሊን የድሮን ጥቃት ፈፅማለች ስትል ሩሲያ ከከሰሰች በኋላ ነው።
ሐሙስ ዕለት የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፣ ያለ ምንም ጥርጥር አሜሪካ ከጥቃቱ ጀርባ አለችበት ብለዋል። ሆኖም ቃለ አቀባዩ ለዚህ ንግግራቸው ያቀረቡት ማስረጃ የለም።
ዩክሬን በበኩሏ በክሬሚሊን በተፈፀመው ጥቃት እጇ እንደሌለበት ገልጻ፣ ሩሲያ ጦርነቱን ለማባባስ ራሷ የፈፀመችው ነው ስትል ከሳለች ።