ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አውስትራሊያዊቷ የወደቀባትን ስልክ ለማንሳት ስትሞክር በአለት ስንጥቅ መካከል ተቀረቀረች
በአውስትራሊያ በአለቶች መካከል የወደቀባትን ስልክ ለማውጣት የሞከረች ሴት ተንሸራትታ በመውደቅ ለሰዓታት በግዙፉ ድንጋይ ውስጥ ተቀርቅራ መቆየቷ ተሰማ።
ማቲልዳ ካምቤል የተባለችው አውስትራሊያዊት በኒው ሳውዝ ዌልስ ሀንተር ቫሊ በእግሯ እየተንሸራሸረች ሳለ ሦስት ሜትር ክፍተት ባለው የአለት ስንጥቅ መካከል በጭንቅላቷ ተዘቅዝቃ ወድቃለች።
የነፍስ አድን ሠራተኞች ማቲልዳን ለማትረፍ ለሰባት ሰዓት ያህል የጣሩ ሲሆን፣ በርካታ አለቶችን ማንፏቀቅ አስፈልጓቸው ነበር ተብሏል።
500 ኪሎ ግራም የሚመዝን አለትን ካንፏቀቁ በኋላም ማቲልዳን ጎብጣ ከተቀረቀረችበት ለማውጣት አዳጋች ሆኖ እንደነበር ተነግሯል።
ፒተር ዋትስ የተባለ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ “በነፍስ አድን የሕክምና ሠራተኛነት ባሳለፍኩበት 10 ዓመታት ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ነገር ገጥሞኝ አያውቅም። በጣም ፈታኝ የነበረ ቢሆንም መጨረሻው ግን የበለጠ አስደሳች ሆኗል።”
ማቲልዳ የነፍስ አድን ሠራተኞች ከመድረሳቸው በፊት ለአንድ ሰዓት ያህል በአለቱ ስንጥቃት መካከል ተዘቅዝቃ ቆይታለች፤ ከዚያ በፊት ጓደኞቿ ሊያወጧት ሞክረው ሳይችሉ መቅረታቸው ተዘግቧል።
በአምቡላንስ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቱ የተለቀቁት ምሥሎች ማቲልዳ በአለቶች መካከል በተፈጠረ ስንጥቅ ተቀርቅራ ይታያል።
ከዚህ በተጨማሪ የነፍስ አድን ሠራተኞች እርሷን ነጻ ለማውጣት በሚረባረቡበት ወቅት በአካባቢው ያሉ ሌሎች አለቶች ሳይናጉ እንዲቆዩ የተደረገውን ጥረትንም ፎቶዎቹ ያሳያሉ።
ዋት እንደገለጸው ማቲልዳ “ወታደር” እንደሆነች ከአንድ ቴሌቪዥን ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ ላይ ገልጻለች።
አክሎም “ሁላችንም እዚያ እንዴት ልትገቢ ቻልሽ፤ ከዚህ እንዴት ነው የምናወጣሽ?” ስንል ነበር የጠየቅነው።
የአምቡላንስ ድርጅቱ በማይታመን መልኩ ማቲልዳ ከትንሽ ጭረት እና መበለዝ ውጪ ምንም የደረሰባት ጉዳት እንደሌለ ገልጿል።
ያም ሆኖ ግን ስልኳን ማትረፍ አልቻለችም።
“ሕይወቴን ላተረፋችሁልኝ ሁሉ አመሰግናለሁ፤ እውነተኛ የሕይወት አድን ሠራተኞች ናችሁ” ስትል በማኅበራዊ ድረ ገጿ ላይ የምስጋና መልዕክት አስፍራለች።
“ወይኔ ስልኬን” ስትል ስልኳን ማትረፍ ባለመቻሏ መቆጨቷንም ገልጻለች።