ስለ ኬንያ ፕሬዚዳንት ልጅ የህይወት ታሪክ የጻፈው ደራሲ ተከሰሰ

ደራሲ ዌብስተር ኦቾራ ኤላይጃህ

የፎቶው ባለመብት, Francis Odee

የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ሴት ልጅን አስመልክቶ የህይወት ታሪኳን የጻፈው ደራሲ ተከሰሰ።

ግለሰቡ የፕሬዚዳንቱን ሴት ልጅ ፍቃድ ሳያገኝ እሷን የሚመለከት መጽሃፍ ጽፏል በሚል መከሰሱን ተከትሎ የኬንያ የህግ ባለሙያዎች እና ተሟጋቾች ሁኔታውን አውግዘዋል።

የፕሬዚዳንቱ ልጅ ቻርሊን ሩቶ ደራሲውን ዌብስተር ኦቾራ ኤላይጃህ ከሷ ፍቃድ ሳያገኝ በመጻፉ "ስሜን ያላግባብ ተጠቅሟል" ስትል ነው የከሰሰችው።

ደራሲው "ከስም ባሻገር፤ ቻርሊን ሩቶ እና የወጣቶች መነሳት" (Beyond the Name: Charlene Ruto and the Youth Uprising) በሚል ርዕስ ባወጣው መጽሐፉ ምክንያት ማክሰኞ ዕለት ክስ ተመስርቶበታል። ግለሰቡ ጥፋተኛ እንዳልሆነ ለፍርድ ቤት ቃሉን ከሰጠ በኋላ የዋስ መብቱ ተከብሮ ወጥቷል።

ክሱን የመሰረተችው ቻርሊን ጉዳዩን አስመልክቶ ለፖሊስ እንዳመለከተች እና ህጋዊ አሰራር መከተሏን ለጋዜጠኞች ተናግራለች።

ተከሳሹ መጽሐፉን ግንቦት 14/ 2017 ዓ.ም ወይም ከዚያ በፊት ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን ማሳተሙ የማጭበርበር አላማ ያለው ነው የሚል ክሱ ላይ ተካቶበታል።

ከተከሳሹ ጋር መጽሃፍ ያሳተሙት ግለሰቦች ክስ እንዳልተመሰረተባቸው ተገልጿል።

የፕሬዚዳንቱ ልጅ መጽሃፉ ያለ ፈቃዷ ስለመጻፉ እንጂ በይዘቱ ላይ ቅሬታ አላቀረበችም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ተቺዎች ግን ይህ አሰራር ህገወጥ አይደለም ይላሉ።

ፖለቲከኛው እና የህግ ባለሙያ የሆኑት ዊልስ ኦቶኖ "ደራሲነትን ለመወንጀል" የመንግሥትን ስልጣን ያለ አግባብ እየተጠቀሙበት ነው እላሉ።

የስነ ጽሑፍ ሃያሲው ምቡጉዋ ንጉንጂሪ በበኩላቸው ደራሲው ምንም ያጠፋው ጥፋት የለም ይላሉ።

ሐያሲው ለዚህም ዋቢ የሚያደርጉት በአውሮፓውያኑ 2014 የታተመው፣ በቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው እና ፍቃድ ያልተጠየቀበትን መጽሓፍ ነው።

"ሚሊዮን ጸሐፊዎች 'የሷን መጽሐፍ' መጻፍ ይችላሉ ይህም ህጋዊ ነው። ቻርሊን ክስ መመስረት የምትችለው ደራሲው በምንም መልኩ እሷን በተሳሳተ መንገድ ከገለጸ ብቻ ነው" ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።

የፕሬዚዳንት ሩቶ ልጅ በኬንያ "የሰዎችን ስም ያለ አግባብ የምንጠቀምበት እና የምናጠፋበት መጥፎ ባህል አለ" ስትል ለጋዜጠኞች ተናግራ፤ "ይህ ትክክል አይደለም" ብላለች።

ቻርሊን ለደራሲው ፈቃዷን እንዳልሰጠች እና መጽሃፉ "አዎንታዊ" ቢሆንም ለውጥ አያመጣም ብላለች።

ብዙም በማይታወቀው በ25 ዓመቱ ደራሲ የታተመው ይህ መጽሐፍ በሰፊው አልተሰራጨም፤ ይዘቱንም አስመልክቶ መረጃ ብዙም የለም።

በበይነ መረብም መጽሐፉ የለም።

ደራሲውን የወከሉት የህግ ባለሙያዎች ወንጀል እንዳልሆነ ተከራክረዋል።

ኬኔዲ ሞንጋሬ የተባሉት ጠበቃ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ደንበኛቸው ቀደም ሲል በታዋቂው ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የተመለከተ መጽሃፍ መጻፉን ነው።

ቻርሊን ሩቶ በኬንያ ውስጥ ታዋቂ ስትሆን ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ጋርም የሚያመሳስሏት አልታጡም።

በህዝባዊ ዝግጅቶች ላይ በእንግድነት በተደጋጋሚ የምትቀርብ ሲሆን፤ የተለያዩ አገራት መሪዎችን በማግኘት እንዲሁም አለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ትታወቃለች።

በአውሮፓውያኑ 2022 "የቀዳማዊት ሴት ልጅ" ብላ ለጠራችው ቢሮ የህዝብ ገንዘብ ውሏል መባሉን አስተባብላለች።