ኬንያ ውስጥ ቁጣን የቀሰቀሰው የቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም
ኬንያ ውስጥ ቁጣን የቀሰቀሰው የቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም
ባለፈው ዓመት የኬንያ መንግሥት ተግባራዊ ሊያደርገው የነበረውን የግብር ሕግ በመቃወም አደባባይ በወጡ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ግድያ መፈጸማቸውን የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ቢቢሲ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ቁጣ ተቀስቅሷል።
ቢቢሲ ከአምስት ሺህ በላይ ምሥሎችን በመፈተሽ ባካሄደው ምርመራ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች አደገኛ ያልነበሩ ተቃዋሚዎች ላይ ቀጥታ በመተኮስ ግድያ መፈጸማቸውን የሚያጋልጡ ማስረጃዎችን አቅርቧል።
በቢቢሲ አፍሪካ የዩቲዩብ ገጽ ላይ ሰኞ ዕለት የተለቀቀው ዘጋቢ ፊልም በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዕይታን ያገኘ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ኬንያውያን መንግሥታቸውን ተጠያቂ እያደረጉ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ዘጋቢ ፊልሙ በአንድ አዳራሽ እንዳይታይ ጫና የተደረገበት ሲሆን፣ አንድ የአገሪቱ ምክር ቤት አባል ደግሞ ዘገባው የአገሪቱን መረጋጋት "የሚያናጋ" በመሆኑ መንግሥት ቢቢሲን እንዲያግድ ጥሪ አቅርበዋል።
ሌላ የምክር ቤት አባል ደግሞ ፊልሙ ምንም ዓይነት ውሸት ስለሌለበት በዜጎች ላይ የተፈጸመው ግድያ እውነት ወጥቶ ተጠያቂነት መኖር አለበት ሲሉ ተከራክረዋል።



