ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአውሮፓውያኑ አዲሱ ዓመት በመላው ዓለም በድምቀት ተከበረ
አዲሱ የአውሮፓውያኑ ዓመት 2026 በመላው ዓለም በድምቀት ተከብሯል።
ከኬንያ መዲና ናይሮቢ እስከ አሜሪካዋ ግዙፏ ከተማ ኒው ዮርክ እንዲሁም ለንደን እና ሲድኒ አዲሱን ዓመት እኩል ለሊት ጠብቀው በድምቀት ተቀብለዋል።
2026ን ቀድመው ከተቀበሉ ክፍለ ዓለማት መካከል የፓሲፊክ ውቅያኖስ ሀገራት እንዲሁም ኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ ይጠቀሳሉ።
በለንደን ቢግ ቤን የተሰኘው ታዋቂ ደወል አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ሲቃጭል ተሰምቷል። በቴምስ ወንዝ ዙሪያ ደግሞ 12 ሺህ ገደማ ርችቶች ተተኩሰዋል።
በስኮትላንድ ዋና ከተማ ኤደንብራም እንዲሁ በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች በተገኙበት ደማቅ ርችት ተተኩሷል።
የጀርመኗ በርሊን፣ የስፔኗ ባርሴሎና፣ የፈረንሷይዋ ፓሪስ ሌሎች አዲሱን ዓመት በድምቀት የተቀበሉ ከተማዎች ናቸው።
ግሪንላንድ፣ ብራዚል እና ኒው ዮርክ ከተቀረው ዓለም ዘግይተው አዲሱን ዓመት ተቀብለዋል።
በኒው ዮርክ ከተማ ታይምስ ስኩዌር በተባለው ግዙፍ አደባባይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በተሰበሰቡበት ነው አዲሱ ዓመት የተከበረው።
በሪዮ ዲ ጄኔይሮ በርካታ ሺዎች በተገኙበት ኮፓካባና የባሕር ዳርቻ የአዲስ ዓመት ዋዜማ የተከበረ ሲሆን እኩል ሌሊት ላይ የተተኩሰው ርችት የከተማዋ ድምቀት ሆኖ አምሽቷል።
ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን እና ቻይና ከአውሮፓው ቀድሞው አዲሱን ዓመት ከተቀበሉ የእስያ ሀገራት መካከል ናቸው።
በዓለማችን በቁመት ትልቁ የዱባዩ ቡርጅ ኻሊፋ ሕንፃም በርችት መብራት ሲደምቅ ታይቷል።
በአዲስ አበባ ከተማም የአውሮፓውያኑን አዲስ ዓመት በማስመልከት ትናንት ሌሊት በሸራተን አዲስ ሆቴል ርችት መተኮሱን የሚያሳዩ ምስሎች የከተማዋ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በፌስቡክ ገጹ አጋርቷል።
ከሁሉም ቀድሞ በጎርጎሪዮሳውያን አቆጣጠር 2026ን የተቀበለችው ስፍራ ኪሪቲማቲ ትባላለች።
ክሪስማስ ደሴት በተሰኘ ቅፅል ስሟ የምትታወቀው የፓሲፊኳ ኪሪባቲ ክፍል ናት። የሕዝብ ቁጥሯ 7 ሺህ ገደማ ሲሆን ውብ የባሕር ጠረፎቿ የቱሪስት ማዕከል ናቸው።
ኪሪቲማቲ ግሪንዊች ሜን ታይም በተሰኘው የሰዓት አቆጣጠር +14 ላይ ትገኛለች። ይህ ማለት ከኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 11 ሰዓታት ትቀድማለች ማለት ነው።
ኒው ዚላንድ ከቀሪው ክፍለ ዓለም ቀድማ አዲሱን ዓመት የተቀበለች ሌላኛዋ ሀገር ናት። በዋና ከተማዋ ኦክላንድ አዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት 2026 በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በደሴቲቱ ፊጂ አቆጣጠር አዲሱ ዓመት ተጀምሯል። የፊጂ ነዋሪዎች እኩለ ሌሊትን ጠብቀው 2026ን ተቀብለዋል።