በመጠጥ ውሃ ውስጥ ስለሚገኘው እና የጥርስ መቦርቦርን ስለሚከላከለው ፍሎራይድ ምን እናውቃለን?

የአሜሪካዋ ዩታህ የመጠጥ ውሃ ውስጥ የሚገኘውን ፍሎራይድ በመከልከል የመጀመሪያዋ ግዛት ሆናለች።

የሕክምና ባለሙያዎች በልጆች እና በጎልማሶች ጥርስ ላይ ያለውን አስከፊ መዘዝ የሚናገሩትን ችላ በማለት ነው ውሳኔውን ያሳለፈችው።

ተመሳሳይ እርምጃዎች ሪፐብሊካን በሚቆጣጠሯቸው ግዛቶች ይቀጥላሉ የሚል ስጋት በሕዝብ ጤና ባለስልጣናት ዘንድ ተፈጥሯል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ፍሎራይድ ከአፈር ወይም ከድንጋይ በተፈጥሯዊ መንገድ ወደ ውሃው ይገባል።

በዓለም ዙሪያ ከ 20 በሚበልጡ አገሮች ደግሞ ለብዙ አሥርተ ዓመታት በመደበኛነት ፍሎራይድ ለሕዝብ በሚቀርብ ውሃ ውስጥ ሲጨመር ቆይቷል።

ሰዎች ብዙ ስኳር በሚጠቀሙባቸው ነገር ግን የጥርስ ሕክምና ማግኘት በማይችሉባቸው አካባቢዎች፣ ፍሎራይድ መጨመር የጥርስ መቦርቦርን እና መበስበስን ለመከላከል የሚረዳ ዘዴ በመሆኑ ውጤታማ የጤና ፖሊሲ ነው።

በሚመከረው ልክ መጠጥ ውሃ ውስጥ ሲጨመር በሰዎች ላይ ጉዳት ስለማድረሱ የሚያሳይ ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም።

ክትባቶችን ጨምሮ በጤና ላይ ባላቸው አወዛጋቢ አስተያየቶቻቸው የሚታወቁት በዶናልድ ትራምፕ የተሾሙት የጤና ሚኒስትሩ ኬኔዲ፤ በመጠጥ ውሃ ላይ ፍሎራይድ እንዳይጨምር ለረጅም ጊዜ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ኬኔዲ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) በአገር አቀፍ ደረጃ ፍሎራይድ መጠቀም መምከሩን እንዲያቆም ለመንገር ማቀዳቸውን ከቀናት በፊት አስታውቀው ነበር።

የዩታህ ባለስልጣናትም "አሜሪካን እንደገና ጤናማ ለማድረግ መሪ ሆነዋል" ሲሉ አወድሰዋቸዋል።

እነዚህ እርምጃዎች በፍሎራይድ ላይ ያለውን አለመተማመን የበለጠ በመጨመር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት በጤና ባለሙያዎች ዘንድ ፈጥሯል ።

የጥርስ ሐኪሞች ፍሎራይድን ለምን ይመክራሉ?

የቀድሞው የዩታህ የጥርስ ሐኪም ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ብሬንት ላርሰን ግዛቲቱ ፍሎራይድ በመጠጥ ውሃው ውስጥ መጨመር ከጀመረችበት ከ2003 በፊት ነበር የጥርስ ሕክምናን የተማሩት።

"ቀደም ሲል ልጆች አራት፣ ስድስት እና ስምንት የተቦረቦረ ጥርስ ያጋጥማቸው ነበር። ፍሎራይድ መጨመር ከተጀመረ በኋላ ግን ችግሩ ጠፋ" ብለዋል።

የጥርስ መበስበስን መከላከል እና የተቦረቦሩ ጥርሶችን ለመሙላት ዩታህ ውስጥ ከ100 እስከ 1000 ዶላር ያስከፍላል።

ይህ ደግሞ ብዙ ቤተሰቦች ሊከፍሉት የማይችሉት ወጪ ነው ሲሉ አክለዋል።

እአአ በ2015 ደግሞ የኒው ዮርኳ ቡፋሎ ባለስልጣናት ለህዝቡ ሳያሳውቁ ፍሎራይድ በከተማው ውሃ ላይ እንዳይጨመር አደረጉ።

የጥርስ ችግሮች በጣም በመጨመራቸው ወላጆች ከተማዋን በመክሰስ ከ2024 ጀምሮ ፍሎራይድ ውሃ ውስጥ መጨመሩ በድጋሚ ቀጠለ።

ከ2017 እስከ 2020 ከዩናይትድ ኪንግደም የተገኘ መረጃ እንዳሳየው ከሆነ 20 በመቶ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ማኅበረሰቦች ፍሎራይድ ውሃ ውስጥ በመጨመሩ የጥርስ መበስበስ ዕድላቸው በ 25 በመቶ ዝቅ ያለ ነበር።

ከፍሎራይድ ጋር የተያያዘው መሠረተ ቢስ ታሪክ

ፍሎራይድ ከመጀመሪያው ጀምሮ በተሳሳተ መረጃ የተተበተበ ነበር።

የሚቺጋን ግዛቷ ግራንድ ራፒድስ እአአ በ1945 የውሃ አቅርቦቷን በፍሎራይድ ያበለፀገች የመጀመሪያዋ ከተማ ሆናለች።

የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ጤና አገልግሎት ባካሄደው ጥና ከ11 ዓመታት በኋላ በከተማዋ ሕጻናት ላይ የሚያጋጥመው የጥርስ መቦርቦር 60 በመቶ ቀንሷል።

ይህም የዊስኮንሲን የጥርስ ጤና ቢሮም በግዛቲቱ ፍሎራይድ ያለበትን ውሃ ለነዋሪዎች እንዲቀርብ እንዲጠይቅ አድርጎታል።

በስቲቨንስ ፖይንት ከተማ ፍሎራይድ ውሃ ውስጥ እንዲጨመር የተደረሰው ውሳኔ በ1949 በተካሄደ ዘመቻ እንዲቀር ተደረገ።

አንዳንዶች ፍሎራይድ መርዝ እና የአካባቢ ብክለት ምንጭ መሆኑን ሲገልጹ፣ በመላ አገሪቱ የሚገኙ የአካባቢ እና ፀረ-ክትባት ቡድኖችን ድጋፍ አግኝተዋል።

የግለሰብ ፍላጎት አለመከበሩን እና የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ ሳይንቲስቶች ፍሎራይድ ውሃ ውስጥ የሚጨምሩበትን ዓላማ በማንሳት የሴራ ትንተና አድርገዋል።

እነዚህ ሃሳቦች አሁንም ድረስ ዘልቀዋል።

ፍሎራይድ ውሃ ውስጥ መጨመሩን የሚቃወሙት የሕዝብ ጤና ጣልቃገብነትን የሚቃወሙ ቡድኖች ዋነኛ ነጥብ ነው።

ለዘንድሮው ዕገዳ ምክንያቱ ምን ይሆን?

ኬኔዲ ከጤና እና ከሳይንስ ጋር የተያያዙ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማስፋፋት ይጠቀሳሉ።

ክትባቶችን ከኦቲዝም ጋር ማገናኘትን እና ኤድስን ከኤችአይቪ ይልቅ ከመርዛማ እና ከአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀም ጋር የተቆራኙ በማደረግ በማቅረባቸው ይታወቃሉ።

ከወራት በፊት ኬኔዲ ለ 5.5 ሚሊዮን የኤክስ ተከታዮቻቸው "ፍሎራይድ ከአርትራይተስ፣ ከአጥንት ስብራት፣ ከአጥንት ካንሰር፣ ከአይኪው መቀነስ፣ ከኒውሮን ዕድገት ዝግመት እና ከታይሮይድ በሽታ ጋር የተያያዘ የኢንዱስትሪ ቆሻሻ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።

በርካታ ጥናቶችን በማጣቀስ ነበር ይህንን በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት።

በካርዲፍ ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ጤና አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኢቮር ቼስትኑት ግን ትንተናው ድኩም መሆኑን ገልጸው፤ ጥናቶቹ የተከናወኑት በተፈጥሮ ከፍተኛ የፍሎራይድ መጠን ባለባቸው አካባቢዎች መሆኑን እና ይህም ለሕዝብ በሚቀርበው ውሃ ላይ ከሚጨመረው በላይ ፍሎራይድ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ከአሜሪካ ጋር ተመሳሳይ ፍሎራይድ ባለባቸው በስዊድን እና በዴንማርክ የተደረጉ ጥናቶች ከዝቅተኛ አይኪው ጋር ስላለው ግንኙነት ምንም አላገኙም።

የአሜሪካ የካንሰር ማሕበርን ጨምሮ ሌሎችም ውሃ ውስጥ በሚገኝ ፍሎራይድ እና በካንሰር መካከል ስላለው ግንኙነት ጠንካራ ማስረጃ አለመኖሩ ገልጸዋል።

የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) በበኩሉ ባለሙያዎች ውሃ ውስጥ የሚገኝ ፍሎራይድ ከጤና ጉዳት ጋር የሚያገናኝ "አሳማኝ ሳይንሳዊ ማስረጃ አላገኙም" ብሏል።

የዩታህ ሕግ አውጪዎች በጤና ዙሪያ ለግለሰብ ምርጫ ቅድሚያ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

ፍሎራይድ በመጠጥ ውሃ ውስጥ ከመጨመር የፍሎራይድ ታብሌቶችን በፋርማሲዎች እንዲሸጡ ሃሳብ አቅርበዋል።

ፕሮፌሰር ቼስትነት ግን ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ፍሎራይድ ስለማግኘታቸው ይጠራጠራሉ።

"የፍሎራይድ ታብሌቶችን የሚገዛው ማነው? ጥሩ ገቢ ያላቸው ወላጆች ናቸው የሚገዙት።"

የዩታህ የጥርስ ሐኪሞች ማህበር አባሉ ዶ/ር ላርሰንም በዚህ ይስማማሉ። መድሃኒቶቹን ለመግዛት በዓመት ከ300 እስከ 400 ዶላር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች ከባድ መሆኑን ጠቁመዋል።

በግል ምርጫ ዙሪያ የሚደረገው ክርክር በትራምፕ ዘመን ለአሜሪካ መራጮች ትልቁ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል።

ኬኔዲ ቀደም ሲል እንደተናገሩት ከሆነ የኩፍኝ ክትባትን መውሰድ "የግል ምርጫ" መሆን አለበት።

ይህን ያሉት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በቴክሳስ ተከስቶ በነበረው የኩፍኝ በሽታ ምክንያት 2015 በኋላ ለመጀመሪያው ጊዜ አንድ ህጻን ከሞተ በኋላ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት የትብብር ማዕከል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ላውረንስ ጎስቲን በበኩላቸው "የሕዝብ ጤና አጠቃላይ ሕዝቡን ለመጠበቅ ነው" ብለዋል።

"የግል የሕክምና ውሳኔ አይደለም፣ ነገር ግን የሰፊውን ሕዝብ ጤና እና ደህንነት ለመጠበቅ የተነደፈ ፖሊሲ ነው።"

ከፍሎራይድ በተያያዘ የሚሰራጨው የተሳሳተ መረጃ በእስያ፣ በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ እየጨመረ ይገኛል።

በሪዮ ዲ ጄኔሮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ጤና ፕሮፌሰር የሆኑት የጥርስ ሐኪም ብራንካ ኦሊቬራ እንዳሉት ከሆነ "በክልሉ ያለው የፍሎራይድ ፕሮግራሞች ውጤታማነት የማይካድ ቢሆንም፤" በሺህዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው ብራዚላውያን የጥርስ ሐኪሞች የፀረ-ፍሎራይድ ጉዳዮችን በመደገፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የኬኔዲ አስተያየት ሲያጋሩ እየተመለከቱ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅቱ ፕሮፌሰር ጎስቲን በበኩላቸው የዩታህ እገዳ "ለሕዝቡ ግራ አጋቢ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ" እና "በብዙ የዓለም ክፍሎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል" ብለው ያምናሉ።

"ይህ አደገኛ ነው ምክንያቱም ለኅብረተሰብ ጤና መተማመን አስፈላጊ ነው" ሲሉ አክለዋል።