ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሱዳን ሆስፒታል በተፈጸመ 'አሰቃቂ ጥቃት' በርካታ ህጻናት መገደላቸውን ዶ/ር ቴድሮስ ገለጹ
በሱዳን ሆስፒታል በተፈጸመ 'አሰቃቂ ጥቃት በአብዛኛው ህጻናትና የጤና ባለሙያዎች የሆኑ 40 ሰዎች መገደላቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ ገለጹ።
"በጤና ዘርፉ ላይ የሚደርሰው ጥቃት መቆም አለበት፤ ይህ ሊሰመርበት የሚገባ ነው" ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ኮርዶፋን በተሰኘችው ግዛት ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘው አል-ሙጅላድ ሆስፒታል ባለፈው ቅዳሜ ዕለት ነው ጥቃት የተፈጸመበት።
ሆስፒታሉ ሶስተኛ ዓመት በያዘው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተፋላሚ የሆኑት ጦሩ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሚፋለሙባቸው ግንባሮች መካከል በቅርበት ይገኛል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እንዲሁም ሁለት የሱዳን የሲቪል ድርጅቶች ጦሩን በሆስፒታሉ ላይ ጥቃት በመፈጸም ከሰውታል።
ጦሩ በቀረበበት ውንጀላ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።
ደም አፋሳሹ የእርስ በርስ ጦርነት በዓለም የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ያደረሰ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ ገልጿል።
በጦርነቱ፣ በዳርፉር የደረሰውን የዘር ማጥፋት ጨምሮ፣ በአገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ተገድለውበታል እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን አፈናቅሏል።
ሁለቱም ወገኖች በህክምና ተቋማት እና ሰራተኞች ላይ የጦር ወንጀል በመፈጸመም መከሰሳቸውን ቢቢሲ አረብኛ መረጃ አይቷል።
በሙግላድ የሚገኘው አል ሙጅላድ ሆስፒታል "በአካባቢው አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛው የጤና ተቋም ነበር" ሲል የሱዳን ዶክተሮች ኔትወርክ አስታውቋል።
በጥቃቱ ከተገደሉት ከ40 በላይ ሰዎች ውስጥ ስድስቱ ህጻናት እንዲሁም አምስቱ የጤና ባለሙያዎች መሆናቸውን በሱዳን የሚገኘው የአለም ጤና ድርጅት ጽህፈት ቤት እሁድ ዕለት ገልጿል።
በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን ጽህፈት ቤቱ አክሏል።
ሆሰፒታሉ ወሳኝ የሚባል የኩላሊት እጥበትን (ዲያሊሲስን)ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ይሰጥ እንደነበር በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የሚፈጸሙ ጥሰቶችን የሚመዘግበው የአደጋ ጊዜ የህግ ባለሙያዎች ቡድን ገልጿል።
የሱዳን ዶክተሮች ኔትወርክ እና የአደጋ ጊዜ የህግ ባለሙያዎች ቡድን ቅዳሜ ሆስፒታሉ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂው የሱዳን ጦር መሆኑን ገልጸዋል።
ኔትወርኩ ለጥቃቱ ምክንያት ጦሩ "በአል-ሙጅላድ ሆስፒታል" የሰፈሩ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተዋጊዎችን ለመግደል በሚል እንደሆነ ገልጿል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉም ሆስፒታሉ ላይ ተዋጊዎችን አስፍሯል ስለመባሉ የሰጠው ምላሽ የለም። የሱዳን ጦርም የዶክተሮች ኔትወርክ ባቀረበበት ክስ ላይ ያለው ነገር የለም።