ስፖርተኞች ከኦሊምፒክ ውድድር በኋላ በድባቴ የሚጠቁት ለምንድነው?

“ለቀናት ቁጭ ብዬ እተክዝ ነበር። ስሜት አልባ ነበርኩ። ምንድን ነው የሆነው? እያልኩ እጠይቃለሁ።”

የኦሊምፒክ አትሌቷ ሚሪያም ግሌዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ውድድር ተሳትፋ ስትመለስ የተፈጠረባት ስሜት ነው።

“ድንገት ከእውነታው ጋር መጋፈጥ አለብኝ። በፊት የተለመዱ የሚመስሉ ነገሮችን እንደ አዲስ መልመድ ግዴታ ይሆናል።”

የስፖርቱ ዓለም ትልቁ ውድድር በሚባለው ኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች ውድድሮቹ ከተጠናቀቁ በኋላ አእምሯቸው ይዝላል። ይህ ጉዳይ በእንግሊዝኛው ‘ፖስት-ኦሊምፒክ ብሉዝ’ ይባላል። የድኅረ ኦሊምፒክ ድብታ እንደማለት ነው።

አርቲስቲክ ዋና በተሰኘው ስፖርት የምትወዳደረው ሚሪያም ከኦሊምፒክ ጨዋታዎች በኋላ ለወትሮው የምታደርገውን ከባድ ልምምድ እንዳቋረጠች ትናገራለች።

የኦሊምፒክ ተወዳዳሪዋ የብቸኝነት ስሜትም ይጫጫናት ነበር። በሲድኒ ኦሊምፒክ የሚካሄደውን ጨዋታ ለመመልከት ከፈረንሳይ የመጡት ቤተሰቦቿ በዚያው ሽርሽር ሲወጡ እሷ ግን ከውድድሩ በኋላ ብቻዋን ወደ ቤቷ ተመለሰች።

ፓሪስ በሚገኘው የውሃ ዋና ሥልጠና ቦታ ለወትሮው የምታገኛቸው አሠልጣኞችም ከውድድሩ በኋላ እረፈት ወጥተው ነበር።

“ማንም ከጎንሽ ነኝ የሚለኝ አልነበረም” ትላለች።

ይህ የሚሪያም ስሜት በርካታ አትሌቶች የሚጋሩት ነው።

ዶ/ር ካረን ሀዌልስ በካርዲፍ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሥነ ልቦና መምህር ናቸው። ስለድኅረ ኦሊምፒክ ድባቴ ጥናት ያደረጉት ካረን እንደሚሉት ወደ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች መሄድ ለአትሌቶች በጣም ከባድ ነገር ነው።

“በኦሊምፒክ መንደር የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ይቀርብላቸዋል። ነገር ግን ውድድሩ ሲጠናቀቅ ይህ ሁሉ ነገር በአንድ ሌሊት ይጠፋል” ይላሉ።

“ጥናታችን እንደሚጠቁመው የሚደርግላቸው እንክብካቤ ታዋቂ ሰዎች የሚደርግላቸው ዓይነት ነው። ይህ ሁሉ ነው በአንድ ጊዜ የሚቆመው።”

“ከጋብቻ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። መተጫጨት አለ። ከዚያ ሰርግ ለመደገስ መዘጋጀት አለ። ይህ ሁሉ ነገር ስናልመው የነበረ ነው። የምንወደውን ሰው ነው የምናገባው። ነገር ግን በሚቀጥለው ቀን ስትነሳ ምንም የተለወጠ ነገር የለም።”

አትሌቶቹም ስፖርት ላይ አተኩረው ሲጫወቱ ከቆዩ በኋላ እንዲህ ያለ ስሜት ቢሰማቸው የሚገርም አይደለም።

“ገና የስድስት ዓመት ሕፃን ሳለሁ ነው አርቲስቲክ ዋና የጀመርኩት” ትላለች ሚሪያም።

“እያንዳንዱ የምወስነው ውሳኔ፤ እያንዳንዷ እርምጃ ስፖርት ላይ ያጠነጠነች ናት። 14 ዓመት ሲሞላኝ ልምምድ ለማድረግ ወደ ፓሪስ ሄድኩ።”

ዶ/ር ካረን በዚህ ይስማማሉ። አትሌቶች ሕይወታቸውን ሙሉ እዚህ ቦታ እደርሳለሁ ብለው ነው ልምምድ የሚያደርጉት ይላሉ።

አትሌቶቹ ድብርት የሚያጠቃቸው የፈለጉትን መብላት እና መጠጣት በሚፈቅዳለቸው ወቅት ነው። አንዳንድ አትሌቶች ለዓመታት በጣም ቁጥብ የሆነ ነገር እየበሉ ነው ለዚህ የሚበቁት።

“በየቀኑ ፓርቲ ያደርጉ እንደነበር፣ ብዙ ይጠጡ እንደነበር አትሌቶች ነግረውናል። ይህ ደግሞ ስሜታቸውን ከፍ ከማድረግ ይልቅ የበለጡ የማይወጡት ነገር ውስጥ ነው የሚከታቸው” ይላሉ አጥኚዋ።

ይህ ስሜት የወርቅ ሜዳሊያ ያመጡ አትሌቶችም ሆኑ ያሰቡት ያልተሳካላቸው አትሌቶች ላይ የሚንፀባረቅ እንደሆነ ነው ዶ/ር ካረን የሚናገሩት።

ብሪታኒያዊው ዋናተኛ አዳም ፒቲ በሦስት የኦሊምፒክ ውድድሮች ሦስት የወርቅ ሜዳሊያ እና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችሏል። አዳም ስለአእምሮ ጤናው በግልፅ በመናገር ነው የሚታወቀው።

በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ-መጠይቅ “ወርቅ ሜዳሊያ ማምጣት ሁሉን ችግሬን ይቀርፍልኛል ብለህ ታስብ ይሆናል። ግን ላይሆን ይችላል።”

ዶ/ር ሀዌል በጥናታቸው እንዳገኙት የድኅረ ኦሊምፒክ ድብርት አትሌቶች ላይ የሚያመጣው ጫና ከሚታሰበው በላይ ከባድ ሊሆን ይችላል።

“በጣም የከበደ ሲሆን ወደ ድባቴ [ዲፕረሽን] ሊያድግ ይችላል። በጣም የከፍ ሲሆን ደግሞ ራስን የማጥፋት ስሜት ሊመጣ ይችላል” ይላሉ።

ምንም እንኳ ይህ ጉዳይ በደንብ ተጠንቶ ችግሩ ምን ያህል ከባድ ነው የሚለውን ለማወቅ እስካሁን ባይቻልም፤ አትሌቶች ከታላላቅ ውድድሮች በኋላ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ግፊት መፈጠር ጀምሯል።

ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ከ76 የተለያዩ አገራት 148 ባለሙያዎችን አሠልጥኖ በተለይ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለአትሌቶች የተሻለ እንክብካቤ ለማድረግ ሞክሯል።

የኦሊምፒክ ኮሚቲው ሴፍ ስፖርት ዩኒት ኃላፊ የሆኑት ክሪስቲ በሮውስ በተለይ ከውድድሩ በኋላ ለአትሌቶች የሚደረገው ድጋፍ እንዲቀጥል መደረጉን አስታውቀዋል።

ከፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ በኋላ 24 ሰዓት የሚያገለግል አትሌቶች ደውለው ድጋፍ የሚያገኙበት መስመር የተዘጋጀ ሲሆን በ70 ቋንቋዎች የሚያገለግለው መስመር ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ይቀጥላል።

ሚሪያም ከዋና ስፖርት ራሷን ካገለለች በኋላ በቢዝነስ እና ስፖርት አድሚኒስትሬሽን ዘርፍ ተሰማርታ ነበር። አሁን ግን አትሌትስ ሶል የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት አላት።

በቀድሞው የስፖርቱ ሰዎች የሚመራው ድርጅት አትሌቶች ከስፖርቱ ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ጡረታ ሲወጡ የሚገጥማቸውን እክል ለማገዝ የተቋቋመ ነው።

ምንም እንኳ በርካታ አትሌቶች የስፖርት ሥነ ልቦና ባለሙያ ድጋፍ ቢያገኙም የውስጣቸውን አውጥተው መናገር የማይፈልጉት ባለሙያዎቹ የሚዘጋጁት በአገራቱ ኦሊምፒክ ኮሚቲ በመሆኑ ነው ይላሉ ዶ/ር ካረን።

እርዳታ መጠየቅ የስንፍና አሊያም የደካማነት ምልክት ተደርጎ ስለሚቆጠር ለኦሊምፒክ ጨዋታ ላንመረጥ እንችላለን የሚል ስጋት ያድርባቸዋል።

አጥኚዋ እንደሚሉት ለአትሌቶቹ ትክክለኛው ምክር እና እርዳታ ሊገኝ የሚችለው አሁን ጡረታ ከወጡ የቀድሞ አትሌቶች ነው።

“ድጋፍ ያስፈልጋል። ከኦሊምፒክ ጨዋታዎች በፊት ስላለው ሁኔታ እና ከውድድሩ በኋላ ስለሚመጣው ነገር ለአትሌቶች ድጋፍ ሊደረግ ይገባል።”