አደይ አበባ በኢትዮጵያ ብቻ ነው የሚበቅለው? ለምን በአዲስ ዓመት?

የፎቶው ባለመብት, Amensisa Ifa/BBC
የክረምቱ ወቅት ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ አንስቶ የዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ጋራና ሸንተረሩ አረንጓዴ ከመልበሱ ባሻገር የተለየ ሕብር የሚፈጥረው አደይ አበባ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት አብሳሪ ነው።
በበርካታ ኢትዮጵያውን ዘንድ አደይ አበባ የአዲስ ዓመት አብሳሪ የመስከረም ወር መለያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ለበርካቶች የመስከረም ወር፣ የመስቀል ደመራና አዲስ ዓመት ከአደይ አበባ ውበትና መዓዛ ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው።
እንዲያውም አደይ አበባ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ እፅዋት፣ የኢትዮጵያውያን ብቻ መለያ የሆነ ያህል ጠንካራ የስሜት ትስስር ተፈጥሯል።
በእርግጥ አደይ አበባ በኢትዮጵያ ብቻ ነው የሚበቅለው? ከሆነስ ለምን በአዲስ ዓመት? ሳይንሱ ምን ይላል?
አደይ አበባ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብዝሃ ሕይወት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው በአማርኛ አደይ አበባ ወይም የመስቀል አበባ፣ በኦሮምኛ 'ኬሎ'፣ በትግርኛ ደግሞ ገልገለ መስቀል ተብለው የሚጠሩት የእፅዋት ዓይነቶች በሳይንስ መጠሪያቸው 'ባይደንስ' እንደሚባሉ ያስረዳሉ።
ተመራማሪው እንደሚሉት በኢትዮጵያ ሃያ የሚሆኑ የባይደንስ ዝርያዎች አሉ።
ከእነዚህ መካከል 'ባይደንስ ማክሮፕተራ'፣ 'ባይደንስ ፕሬስቲናሪያ' እና 'ባይደንስ ፓክሎማ' የተባሉት ዝርያዎች ብርቅዬና ሰፊ ሥርጭት ያላቸው ወይም በብዛት የሚበቅሉ ናቸው።
እነዚህ ሦስት ዝርያዎች በቅርበት ካልታዩ ወይም በጥናት ካልተለዩ በስተቀር ለዕይታ የመመሳሰል ባህርይ አላቸው ይላሉ- ፕሮፌሰሩ።
እንደ ተመራማሪው ከሆነ 'ባይደንስ ማክሮፕተራ' የሚባለው ዝርያ የሚገኘው በኢትዮጵያ ብቻ ነው።
ይህ የአደይ አበባ ዝርያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይበቅላል። 'ማክሮፕተራ'ን መለየት የሚቻለው በአበባው እምብርት ላይ በሚገኘው ዘሩ አማካኝነት ነው። ዘሩ ትንሽ ክንፍ መሳይ ነገር አለው።
ሆኖም በኢትዮጵያ የሚገኘው ይህ ዝርያ ብቻ አይደለም። 'ባይደንስ ፕሬስትራኒያ' የተባለው ዝርያም ይገኛል።ነገር ግን ይህ የአደይ አበባ ዝርያ ሱዳን ውስጥ ስለሚበቅል በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ነው ማለት አይቻልም።
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ይህ ዝርያም ከሱዳን እና ኢትዮጵያ ውጭም አይበቅልም።
በመሆኑም 'ማክሮፕተራ' በኢትዮጵያ ብቻ ስለሚገኝ 'ብርቅዬ' ሲባል 'ፕሬስትናሪያ' ደግሞ በኢትዮጵያና በጎረቤት ሱዳን ስለሚገኝ 'የቅርብ ብርቅዬ' እንደሚባል ፕሮፌሰር ሰብስቤ ያስረዳሉ።
'ባይደንስ ፓክይሎማ' የተባለው ዝርያ ግን አፍሪካ ውስጥ በብዛት ይገኛል።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ [ባይደንስ ማክሮፕተራ] በዓለም ብርቅዬ እፅዋቶች መዝገብ ውስጥ ባይሰፍርም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀውና የመጤዎችንና አገር በቀል እፅዋቶችን መረጃ የያዘ ጥራዝ ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኝ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, GASHAW LENE
የሰይጣን መርፌ (ባይደንስ ፒሎሳ)
ሌላኛው በኢትዮጵያ የሚበቅለው ከሃያዎቹ የባይደንስ ዝርያዎች መካከል አንዱ የሆነው 'ባይደንስ ፒሎሳ' የተባለው ዘርያ ነው። ይህ የአደይ አበባ ዝርያ ቀለሙ ነጭ ነው። የሚበቅለው ግን ቢጫው አደይ አበባ በሚበቅልበት ወራት ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች በተለምዶ 'የሰይጣን መርፌ' ይባላል።
"የሰይጣን መርፌ የተባለው ጫፉ ላይ እሾህ መሳይ ነገር ስላለውና በቀላሉ ስለሚጣበቅ ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።
የሱፍ አበባ እና የአደይ አበባ ዝምድና አላቸው?
አዲስ ዓመት ሲመጣ አደይ አበባ እና የሱፍ አበባ ለውበት እና ጌጣጌጥነት ጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላል።አንዳንዶች የአዲስ ዓመት ምልክት አደይ አበባ እንዲ የሱፍ አበባ አይደለም ሲሉ ትችታቸውን ይሰነዝራሉ። ለመሆኑ የእነዚህ ሁለት አበባዎች ዝምድና ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ሰብስቤ እንደሚሉት ኑግ፣ ሱፍና ግራዋ የአደይ አበባ ቤተሰብ አባላት ናቸው።
ሁሉም የሚገኙት 'አስትሬይሲያ' በሚባል የእፅዋት ቤተሰብ ውስጥ ነው። እነዚህ የቤተሰብ አባላት በብዛት የሚገኙትና የሚስፋፉት ብዛት ያላቸው ዘሮችን ስለሚያፈሩ ነው።
አደይ አበባ ለዕይታ የሚስበውም የተለያዩ ዝርያዎቹ ብዙ ዘሮች ኖሯቸው በአንድ ላይ ሲያብቡ ብዙ ስለሚሆኑ ነው።
ከዚህም ባሻገር የየአካባቢው ባህል እንዲሁም ሃይማኖታዊ በዓላት ይበልጥ እንዲጎሉ አድርጓቸዋል።
"እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ እፅዋት ቤተሰብ አለው" የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ እነዚህ ዝርያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ቁጥር እንዳላቸው ይናገራሉ። እንደ ተመራማሪው ከሆነ በቁጥር ምን አልባት የአተር ዝርያዎች ቢበልጧቸው ነው።
የአደይ አበባ ፋይዳ ውበት ብቻ አይደለም።ለአንዳንዶች የገቢ ምንጫቸውም ጭምር ነው
የአዲስ ዓመት ምልክት የሆነው አደይ አበባ በተለይ በከተሞች አካባቢ ምስሉ በቀሚስ እና በካናቴራ ላይ ታትሞ አሊያም ተጠልፎ ይቸበቸባል።
እናቶች፣ ወጣቶች ኑሯቸውን ለመደገፍ ከቄጠማ ጋር ቀላቅለው ይሸጡታል።
እድሜው ለወራት የሚዘልቀው አደይ አበባ በመስቀል በዓል ላይ ደመራውን ከሚያስውቡት አንዱ ነው። ጫፉ ላይ ከቄጠማ ጋር ይታሰራል። ከደመራው ሥርም ይጎዘጎዛል።
በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ በድምቀት በሚከበረው የኢሬቻ ክብረ በዓልም የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች ወደ በዓሉ ቦታ የሚያመሩት አደይ አበባ እና እርጥብ ሳር በእጃቸው ይዘው ነው።
በተፈጥሮ በለመለመው ሳርና በፈካው አበባ ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑበታል። ልምላሜንና በጎ ምኞታቸውንም ይገልጹበታል።
አደይ አበባ በምድር ገጽ ላይ መታየት የሚጀምረው በአንዳንድ አካባቢዎች ከነሐሴ ወር መገባደጃ ጀምሮ ነው።
መስከረም አንድ ብሎ ከጀመረ በኋላ እስከ ኅዳር ድረስ ግን መስኩ፣ ተራራው፣ ሜዳው በዚሁ አበባ ያሸበርቃል። የቆይታ እድሜው ግን ከሦስት ወራት አይዘልም።

የፎቶው ባለመብት, AFP
አደይ አበባ ለምን በእነዚህ ወራት ብቻ ታይቶ ይጠፋል?
ፕሮፌሰር ሰብስቤ የአደይ አበባንና የመስከረምን ቀጠሮ የሚያመሳስሉት ከሰዓት ጋር ነው።
"ማታ ተኝተን ጠዋት እንድንነቃ ሰዓት እንሞላለን፤ ልክ እንደዚያው እፅዋት የራሳቸው ጉዳዮች ከተሳካላቸው፣ የሚፈልጉትን ያህል ዝናብና ፀሐይ ካገኙ 'አሁን ነው የምታብቡት' በሚል ውስጣዊ ግፊት ያብባሉ" ይላሉ።
ይህም 'ባዮሎጂካል ክሎክ' [ተፈጥሯዊ ሰዓት] ይባላል።
አበቦቹ ምንም እንኳን ማበቢያ ጊዜያቸው አዲስ ዓመትን ተንተርሶ ቢሆንም እንዲያብቡ የሚያደርጋቸው ግን ውስጣዊ ባህርያቸው እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።
"ግንዳቸው ጠንከር ያላሉት የአደይ አበባ ዝርያ ዓይነቶች ለማበብና ለማፍራት ባላቸው ተፈጥሯዊ ሒደት አንድ ዓመት ይቆያሉ" ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።
ከዚያ በኋላ እነዚህ አበቦች ለውስን ጊዜያት አብበው ይሞታሉ።
"ይሞታሉ ሲባል ይጠፋሉ ማለት ሳይሆን ዘራቸው መሬት ውስጥ ይገባል ማለት ነው"
ፕሮፌሰር ሰብስቤ እንደሚሉት አደይ አበባ መሃል ላይ ያለው ዘሩ የእሾህነት ባህርይ ስላለውና በብዛትም ስለሚመረት በቀላሉ መሬት ውስጥ ለመግባት ያስችለዋል።
መሬት ውስጥ ሲቆይ ልክ ጉንዳን ለክረምት ምግብ እንደሚሰበስበው ሁሉ አደይ አበባም ለዘር የሚያበቃውን ምግብ ይዞ ይቆያል።
"አመቺ ሁኔታ ሲያገኝ፣ ዝናብ ሲዘንብ፣ ከዚያም ፀሐይ ሲወጣ፤ 'አሁን ነው ማበብ ያለብህ' የሚል የተፈጥሮ ግፊት ይገፋፋዋል። ይህ የተፈጥሮ ባህርያቸው ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።
አደይ አበባ ዓመቱን ሁሉ ማበብ ይችላል የሚሉት ተመራማሪው፤ የመስከረም ወር ግን ለእነዚህ ዝርያዎች ይበልጥ አመቺ ነው ይላሉ።
አደይ አበባን ልዩ የሚያደርገውም ከኢትዮጵያ አዲስ ዓመት እና ተከታትለው ከሚመጡ በዓላት ጋር መገናኘቱ ነው።
ሆኖም "አደይ አበባ እና የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ መገጣጠም አጋጣሚ ነው" ብለዋል ተመራማሪው።

በኢትዮጵያ አደይ አበባ የማይበቅልበት ቦታ አለ?
ተመራማሪው እንደሚሉት አደይ አበባ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ይበቅላል።
ይሁን እንጂ በመሬት አቀማመጥ ከፍታና ዝቅታ መጠኑና ቆይታው ሊለያይ ይችላል።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው 'ባይደንስ ማክሮፕተራ' በብዛት የሚገኘው ከመሬት ወለል በላይ ከ2000 እስከ 3600 ሜትር ከፍታ ባሉ ደጋማ አካባቢዎች እንደሆነ ተመራማሪው አስረድተዋል። ከ1750 ሜትር በታች ባሉ አካባቢዎች ግን አይበቅልም።
የእፅዋት ሥርጭት ከመሬት ወለል በላይ ባለ ከፍታ ይወሰናል የሚሉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ አደይ አበባ በትግራይ፣ በአዲስ አበባ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሐረር፣ ደሴ፣ ወለጋ፣ ነቀምት፣ ጂግጂጋ እና ሌሎች ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ይበቅላል ይላሉ።
"ለምሳሌ አፋር ውስጥ ከፍተኛ ተራራ ላይ ሊገኝ ይችላል። ወደ ዳሎል ወረድ ሲባል ግን ሊገኝ አይችልም" ሲሉም ያስረዳሉ።
አደይ አበባ ከውበትና ከድምቀት ሌላ . . .
አደይ አበባ ውበቱ፣ ለሥነ ምኅዳሩ፣ ለሐይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት ያለው አስተዋፅኦ ራሱን የቻለ እሴት ነው።
ከዚህ ባሻገር ግን የመድኃኒትነት ባህርይ ያላቸው የአደይ አበባ ዝርያዎች እንዳሉ ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።
በተለምዶ 'የሰይጣን መርፌ' ተብሎ የሚጠራው የአደይ አበባ ዓይነት በባሌ አካባቢ ሰው በእባብ ሲነድፍ በባህላዊ እውቀት ለመድኃኒትነት እንደሚጠቀሙበት በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። ይህ ግን በሳይንስ የተረጋገጠ አይደለም።
"ምንም እንኳን በተፈጥሮ የተሰጠን ፀጋ እና በረከት በገንዘብና በአገልግሎት መመዘን ብቻ ተገቢ ባይሆንም፤ቀለሙ ቢመረመር ማቅለም የሚችል ይመስለኛል" ብለዋል።
ሆኖም በኬሚካላዊ ባህርያቸው ላይ የተሰራ ምርምር አለመኖሩን ፕሮፌሰር ሰብስቤ ይገልጻሉ።
አንዳንድ ጥናቶችም አደይ አበባ ለስኳር በሽታ እና ለጭንቅላት ካንሰር ሕክምና መዋል እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ኢኮኦፒያ የተባለ በኢትዮጵያ ያለ ድርጅትም ከአደይ አበባ የተሠራ የውበት መጠበቂያ ክሬም ለገበያ እንዳበቃ ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ እንደ አደይ አበባ መጠሪያዋ የሆኑ ብርቅዬ እፅዋቶች እንዳሏት የሚናገሩት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፣ ልክ እንደ ብርቅዬ እንስሳት ሁሉ እነዚህን እፅዋት ለመጠበቅና ለማክበር አንዱ ዝርያ ተመርጦ 'አገራዊ አበባ' ቢደረግ ሲሉ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
*ይህ ዘገባ ከዚህ ቀደም በቢቢሲ አማርኛ ገጽ ላይ የቀረበ ነው።















