የአሜሪካ ዕዳ 37 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል፤ቀሪውን ዓለም ሊያሳስብ ይገባል?

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ትልቅ ቆንጆ" ሲሉ በይፋ የሰየሙት ረቂቅ በጀታቸው በአገሪቱ በምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

የረቂቅ በጀቱ መጽደቁን ተከትሎም አሜሪካ ከተቀረው ዓለም በምትወስደው የብድር መጠን እና ዘላቂነቱ ላይ የሚነሱ ጥርጣሬዎች በአዲስ መልኩ መነጋገሪያ ሆነዋል።

ትራምፕ ያቀረቡት ግብርን የሚቀንሰው የበጀት ረቂቅ ቀድሞውኑ ሸክም በሆነው 37 ትሪሊዮን ዶላር የአገሪቷ ዕዳ ላይ ቢያንስ 3 ትሪሊዮን ዶላር በመጨመር የበለጠ እንደሚቆልለው ይጠበቃል።

ይህ የፕሬዚዳንቱ የበጀት ዕቅድ በብዙዎች ዘንድ ተተችቷል።

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የትራምፕ የቀድሞ አጋር ኤለን ማስክ "አጸያፊ ነውር" በሚል በጠንካራ ቃል ነው ዕቅዱን ሲተች የነበረው።

ከዓለማችን ኃያል አገራት መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካ የዕዳ መጠኗ እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎ የተቀረው ዓለም ለማበደር ገደብ አለው ወይ ብለው እንዲያጤኑ ያደርጋቸው ይሆን? የሚል ጥያቄን አጭሯል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሜሪካ የመገበያያ ገንዘብ ዶላር እየደከመ መምጣቱ መታየቱ እንዲሁም የአሜሪካ አበዳሪዎች ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ተመን እየጠየቁ ይገኛሉ።

አገሪቱ በየዓመቱ በገቢዋ እና በወጪዋ መካከል ያለውን ክፍተት ለማስተካከል ብድር መውሰድ ያስፈልጋታል።

ከጥር ወር ጀምሮ ባለው ጊዜ ዶላር ከዩናይትድ ኪንግደም ፓውንድ ጋር ሲነጻጻር 10 በመቶ እንዲሁም ከአውሮፓ ኅብረት ዩሮ ጋር ተነጻጽሮ 15 በመቶ ማሽቆልቆል አሳይቷል።

የአሜሪካ የብድር ወጪዎች በአጠቃላይ ቋሚ ቢሆኑም በረጅም ጊዜ በሚከፈል ብድር የወለድ ምጣኔ ተመን እና በአጭር ጊዜ በሚከፈል ብድር የወለድ ተመን ላይ ያለው ልዩነት ጭማሪ አሳይቷል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ አሜሪካ የምትወስዳቸው ብድሮች ላይ የረጅም ጊዜ ዘላቂነት ላይ ጥርጣሬዎን መፍጠሩ አልቀረም።

አሜሪካ የወለድ ምጣኔዋን መቀነሷን ተከትሎ ዶላሯን የበለጠ ጠንካራ ያደርገዋል የሚሉ ግምቶች ነበሩ። ምክንያቱም ባለሃብቶች ገንዘባቸውን በባንክ ተቀማጭ ሲያደርጉ ከፍተኛ ወለድ ሊያገኙ ስለሚችሉ ነው።

በዓለማችን ትልቁን የሄጅ (ኢንቨስትመንት) ፈንድ መሥራች የሆኑት ሬይ ዳሊዮ የአሜሪካ ብድር መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ብለው ያምናሉ።

አገሪቷ አሁን በያዘችው አካሄድ ከቀጠለች በቅርቡ በየዓመቱ 10 ትሪሊዮን ዶላር ብድር እና ወለድ ለመክፈል እንደምታወጣ ይገምታሉ።

"የአሜሪካ መንግሥት የፋይናንስ ሁኔታ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው፤ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ማስተካከል ካልተቻለ ዕዳዎቹ ጨምረው ከፍተኛ ዋጋ ሳይከፈል ማስተካከል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደረሳል" ይላሉ።

የሚከፈለው ከፍተኛ ዋጋ ምን ሊመስል ይችላል?

የመጀመሪያው አማራጭ የመንግሥትን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ፣ የግብር ከፍተኛ ጭማሪ ወይም ሁለቱንም ተግባራዊ ማድረግ ሊሆን ይችላል።

ሬይ ዳሊዮ እንደሚሉት አገሪቷ አሁን ያለባትን 6 በመቶ የበጀት ጉድለትን ወደ 3 በመቶ በቅርቡ ማውረድ ካልቻለች ለወደፊቱ ጣጣ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ጠቋሚ ነው።

የትራምፕ ረቂቅ በጀት የመንግሥትን ወጪ በተወሰነ መልኩ ቢቀንስም የበለጠ የቀነሰው ግን ግብርን በመሆኑ የፖለቲካ መንገዱ ሌላ አቅጣጫ መያዙን ያሳየ ነው።

ሁለተኛው አማራጭ እንደ ቀደሙት የምጣኔ ሃብት ቀውሶች የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ብዙ ገንዘብ በማተም የመንግሥትን ዕዳ ለመግዛት ሊጠቀምበት ይችላል። ይህም ከአውሮፓውያኑ 2008 ታላቅ የፋይናንስ ቀውስ በኋላ ታይቷል።

በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንዲሁም ቤቶች እና አክሲዮኖችን የመሳሰሉ ንብረቶች ባለቤቶች በደመወዝ (በጉልበታቸው) ከሚተዳደሩ በበለጠ የተሻሉ በማድረግ ልዩነቶችን ይፈጥራል።

ሌላኛው እና ሦስተኛው ሊሆን የሚችለው ብድር መክፈል አለመቻል (ዲፎልት) ነው። መክፈል አልችልም ስለዚህ አልከፍልም የሚለው ነው።

ሆኖም የአሜሪካ ግምጃ ቤት "ብድር እና ሙሉ እምነት" የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት መሠረት በመሆኑ ታላቁን የፋይናንስ ቀውስ እንደ ሽርሽር የቀለለ ያስመስለዋል።

እነዚህ ሁኔታዎች የመፈጠር ዕድላቸው ምን ያህል ነው? መልሱ በአሁኑ ወቅት ኢምንት ሊባል ይችላል። ነገር ግን ብዙ የሚያጽናና አይደለም።

ሆኖም እውነታው ወደድንም ጠላንም ዓለም ከዶላር የበለጠ የመገበያያ አማራጮች ያሏት ጥቂት ናቸው።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው እና በተለያዩ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኃላፊነት ያገለገሉት መሐመድ ኤል ኢርያን በርካቶች የዶላርን ምጣኔ ለማውረድ እየሞከሩ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ዶላር ከሚገባው በላይ ዋጋ ያለው ነው፤ ይህንንም ዓለም ያውቀዋል፤ ለዚያም ነው የወርቅ ገበያ ያንሰራራው። እንዲሁም የዩሮ እና የፓውንድ መገበያያ ገንዘቦች መናርን ያየነው። ነገር ግን አሁን ባለው አካሄድ ችግሩን ለመፍታት ከባድ ስለሆነ አማራጮቹን አነስተኛ ያደርጋቸዋል" ይላሉ።

በሌላ ቋንቋ "ዶላር ማለት ልክ በጣም ከቆሸሹ ሸሚዝዎችዎት ሻል ያለው ቆሻሻ እንደማለት ነው። ያንን ከመልበስ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም" ይላሉ።

ነገር ግን የዶላር የወደፊት ዕጣ ፈንታ እና የዓለም የንብረቶች መለኪያ የሆነው የአሜሪካ የመንግሥት ቦንድ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ዘንድ ለውይይት ቀርቧል።

የባንክ ኦፍ ኢንግላንድ ገዥ በቅርቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአሜሪካ የብድር መጠን እና የዶላር ሁኔታ "በአሜሪካ የግምጃ ቤት ፀሐፊ ቤሴንት በዋነኝነት የሚያስብበት ነው። በአሁኑ ወቅት ዶላር በመሠረቱ ስጋት ላይ ያለ አይመስለኝም፤ ነገር ግን ስለእነዚህ ጉዳዮች ጠንቅቆ ያውቃል። እሱም የሚያቃልለው አይመስለኝም" ብለዋል።

37 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳ ሊደረስበት (ሊታሰብ) የማይችል አሃዝ ነው። በሰውኛ ስናሰላው በየቀኑ አንድ ሚሊዮን ዶላር ቢያጠራቅሙ እዚህ ላይ ለመድረስ መቶ ሺህ ዓመታት ይፈጅብዎታል።

የአንድን አገር ዕዳ ለመመልከት ትርጉም ሰጪው መንገድ የአገሪቱን ገቢ በመቶኛ በማየት ነው።

የአሜሪካ ምጣኔ ሃብት በዓመት 25 ትሪሊዮን ዶላር ያስገባል።

ከገቢ አንጻር ሲሰላ ያላት ዕዳ ከብዙ አገራት እጅግ ከፍ ያለ ቢሆንም እንደ ጃፓን ወይም ጣሊያን ከፍ ያለ አይደለም።

ከዚህ በተጨማሪ የአገሪቷ ምጣኔ ሃብት በዓለማችን ካሉ ሃብት ፈጣሪ እንዲሁም ፈጠራ የተሞላበት መሆኑ ጥቅም አለው።

ዊልያም ኤፍ ሪከነባከር 'ዴዝ ኦፍ ዘ ዶላር ' (የዶላር ሞት) በሚለው መጽሐፋቸው ዶላር የዓለም መጠባበቂያ ምንዛሪ መሆኑ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ አስጠንቅቀዋል።

መጽሐፉ የተጻፈው በአውሮፓውያኑ 1968 ነው።

ዶላር ኃያልነቱን ይዞ እስካሁን ቢቀጥልም ደረጃው እና እሴቱ መለኮታዊ ነው ማለት አይደለም።