በአፋር የተከሰተው እሳተ ገሞራ የፈጠረው አመድ እስከ ሕንድ ደርሶ በረራዎችን አስተጓጎለ

ከኢትዮጵያ አፋር ክልል ከፈነዳው እሳተ ገሞራ የወጣ ጭስ ከቀይ ባሕር ተሻግሮ ከኦማን እና የመን ባሻገር ከሕንዷ ሙምባይ መደረሱን የሕንድ ሜቲዮሮሎጂካል መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

የሕንድ የአቪየሽን ባለሥልጣናት አመዱ በታየባቸው አካባቢ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ያዘዙ ሲሆን፣ በርካታ በረራዎች ተሰርዘዋል ወይም ዘግይተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዳዩ ዙሪያ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ የእሳተ ገሞራው አመድ እስካሁን ድረስ በሥራውን መስተጓጎል እንዳልፈጠረ አሳውቋል።

ሁኔታውን ከሚመለከታቸው የአቪዬሽን እና የሜትሮሎጂ ተቋማት ጋር በቅርበት እየገመገመ መሆኑን ገልጿል።

ለበርካታ ሺህ ዓመታት ሳይፈነዳ የቆየው የኢትዮጵያው ሃይሊ ጉቢ ተብሎ የተጠራው እሳተ ገሞራ መፈንዳት የጀመረው ባለፈው ዕሁድ ጠዋት ላይ ነበር። በፍንዳተው ግዙፍ የጭስ አምድ ወደ ሰማይ በመውጣት በአካባቢው ታይቷል።

በዚህ እሳተ ገሞራ የተነሳ የተፈጠረው አመድ በሕንድ ውስጥ የሚደረጉ በረራዎች እንዲሰረዙ፣ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ወይም እንዲዘገዩ ምክንያት ሆኗል።

የሕንድ አቪየሽን ባለሥልጣንም አየር መንገዶች ጭስ እና አመድ በታየባቸው አካባቢዎች በኩል ከመብረር እንዲቆጠቡ በጥብቅ አዝዟል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በእሳተ ገሞራው ምክንያት የተፈጠረው የአመድ ብክለት ምን ያህል እንደሆነ አስካሁን አልታወቀም። ነገር ግን ወትሮም በአየር ብክለት ችግር ውስጥ ያለቸውን የሕንድ ከተማን የዴልሂን አየር ጥራት እንደማያበላሸው ተነግሯል።

የእሳተ ገሞራ አመድ የሚያብለጨልጭ እና ደመናማ ጥቃቅን ብናኝ ያሉት ሲሆን፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታን ተከትሎ ወደ ከባቢ አየር ይረጫል። ይህም የአውሮፕላን ሞተርን ሊያበላሽ፣ አየር ማረፊያዎችን አየር ሊበክል እና ዕይታን በማገድ ለበረራ አደገኛ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል።

"በጭሱ የተበከለው የከባቢ አየር ክፍል ከባሕር ጠለል በላይ 8.5ኪሜ እና 15ኪሜ ከፍታ ላይ የሚገኝ ነው" ሲሉ የሕንድ ሜትሮሎጂ መሥሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር ምሩቲዩንጃይ ሞሃፓትራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ጭሱ ለጊዜው በረራዎችን እና የሳተላይቶችን ሥራ ሊያደናቅፍ ይችላል። ነገር ግን የአየር ሁኔታን እና የአየር ጥራት ላይ ችግር አይኖረውም። ሰኞ ምሽት ላይ ወደ ሰሜናዊ ሕንድ የደረሰ ሲሆን፣ ወደ ቻይና እያመራ ነው" ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በስካይሜት ዌዘር መረጃ መሠረት አመዱ ተበትኖ ለመጥፋት ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅበት ለማወቅ አዳጋች ነው፣ ነገር ግን የሕንድ ባለሥልጣናት እንደሚሉት አመዱ ከዴልሂ ሰማይ ማክሰኞ ምሽት ይበተናል።

በዚህ አመድ ምክንያት የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ የተስተጓጎለ ሲሆን፣ ኤር ኢንዲያ 11 በረራዎችን ሲሰርዝ፣ ኢንዲያጎ፣ አካሳ እና ኬኤልኤም ጫና እንዳሳረፈባቸው ገልጸዋል።

የሙምባይ አየር ማረፊያ ተሳፋሪዎች ወደ አየር ማረፊያው ከመሄዳቸው በፊት የበረራ ሁኔታቸውን ቀደም ብለው እንዲመለከቱ ተጠይቀዋል።

የሕንድ የሲቪል አቪዬሽን ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አብራሪዎች ሞተር ላይ ያልተለመዱ ነገሮች፣ ጭስ ወይም የአመድ ሽታን ጨምሮ ማንኛውንም አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥማቸው በፍጥነት ሪፖርት እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

አየር መንገዶች ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚበሩ አውሮፕላኖችን እንዲመረምሩ እና "ችግሩ በተባባሳባቸው አካባቢዎች አየር ማረፊያዎች ሥራቸውን እንዲያቆሙ ወይም እንዲያዘገዩ" አዝዟል።

አንድ አብራሪ ከፍተኛ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መብረር የሚችልባቸውን መመሪያ የያዘ ሦስት የእሳተ ገሞራ አመድ ብክለት ደረጃዎች አሉ - ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ተብለው ተለይተዋል።

አሁን ያለው የብክለት ደረጃ ግልጽ አይደለም።

"በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምክንያት የሚከሰትን ብክለት ለመለካት ብዙ ዝግጅት ይጠይቃል። መሣሪዎች አስቀድመው መሰማራት ይኖርባቸዋል። ይህን መሰሉ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ለዝግጅት ምንም ዕድል አልሰጠም። ስለዚህ የብክለት ደረጃው አይታወቅም" ሲሉ የስካይሜት ዌዘር ፕሬዝዳንት ጂፒ ሻርማ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእሳተ ገሞራው ፍንዳታ ለሺህ ዓመታት ሳይፈነዳ የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ድምጽ ቢኖረውም የመሬት መንቀጥቀጥ እንቅስቃሴ እንዳላስከተለ ተናግረዋል። የሃይሊ ጉቢ እሳተ ገሞራ በኤርታ አሌ አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን ይህም በንቁ እሳተ ገሞራው የሚታወቅ አካባቢ ነው።

የእሳተ ገሞራ አመድ መከሰቱ የተለመደ አይደለም። የአይስላንድ የኤጃፍጃላጆኩል እሳተ ገሞራ በ2010 ሲፈነዳ ዓለም አቀፍ የጉዞ መሰናክሎችን አስከትሏል።

በወቅቱም የዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ የአየር ክልል ተዘግቶ ወይም በከፊል ተዘግቶ ነበር። ይህም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እጅግ የከፋ የአየር ጉዞ መስተጓጎል ሆኖ ተመዝግቧል።