ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሙሉ ለሙሉ ‘አረንጓዴ ነዳጅ’ የሚጠቀመው የመጀመርያው አህጉር አቋራጭ በረራ ዛሬ ይከናወናል
የአየር ንብረትን የማይበክለውን አረንጓዴ የኃይል አማራጭን ብቻ በመጠቀም የሚደረገው የመጀመሪያው አትላንቲክን የሚያቋርጥ በረራ በዛሬው ዕለት ማክሰኞ ማለዳ እንደሚጀምር ተገለጸ።
አውሮፕላኑ ከእንግሊዝ፣ ለንደን ሂትሮው አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ አሜሪካ፣ ኒውዮርክ ጆን ኦፍ ኬኔዲ አየር ማረፊያም በረራውን ያደርጋል ተብሏል።
ይህ በመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ይህ በረራ አካባቢን በማይጎዳ መልኩ መብረር እንደሚቻል ያሳያል ተብሏል።
ነዳጅ የማይጠቀመው አውሮፕላን የአቅርቦት እጥረት ሊገጥመው ይችላል የተባለ ሲሆን፣ ሆኖም የታለመለትን የልቀት ደረጃ ለመድረስም ሌሎች የቴክኖሎጂዎች እገዛ እንደሚፈልግም ተጠቁሟል።
አውሮፕላኑ ዘላቂ ታዳሽ ኃይል (ዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጅ) የሚጠቀም ሲሆን ይህም ከሰብሎች፣ ከቤት ውስጥ ቆሻሻዎች እና እንደ ምግብ ዘይቶች ካሉት መሰራት ይቻላል። 50 ቶን አረንጓዴ ነዳጅ ለዚህ በረራ በተዘጋጀው ቦይንግ 787 ላይ ይሞላል።
ለነዳጁ ሁለት ዓይነት ግብዓቶች ጥቅም ላይ ውለዋል። 88 በመቶው ከቆሻሻ ስብ ሲሆን፣ የተቀረው ከአሜሪካ የበቆሎ ምርት የተገኘ ነው።
ከበርካታ ጥትናት እና ሙከራ በኋላ በረራው በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከዩናይትድ ኪንግደም ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ፈቃድ አግኝቷል። የሞተር አምራቹን ሮልስ ሮይስ እና በኢነርጂ ዘርፍ የተሰማራውን ቢፒን ጨምሮ በርካታ ኩባንያዎች በዚህ ፕሮጀክት ተሳታፊ ሆነዋል።
የአቪዬሽን ኢንደስትሪውን ከካርቦን ልቀት ማላቀቅ አስቸጋሪ ሆኖ ይታይ ነበረ ቢሆንም፣ አየር መንገዶች አረንጓዴ ነዳጅን ልቀቱን ወደ ዜሮ ለማውረድ ብቸኛው ውጤታማ መንገድ አድርገው ይመለከቱታል።
አውሮፕላኖች አረንጓዴ ነዳጅን ሲጠቀሙም ካርቦን ማመንጨታቸውን ቢቀጥሉም የእነዚህ ነዳጆች ልቀት እስከ 70 በመቶ ያነሰ ሊሆን እንደሚችል የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
አረንጓዴ ነዳጅ ከተለመደው የጄት ነዳጅ ጋር ተቀላቅሎ ጥቅም ላይ ይውላል። ይህ ግን በዓለም ዙሪያ ጥቅም ላይ ከሚውለው የአቪዬሽን ነዳጅ ከ0.1 በመቶ ያነሰ ያነሰ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ዋጋው ከናፍጣ የሚወደድ ሲሆን፣ የሚመረተውም በአንጻራዊነት በአነስተኛ መጠን ነው። አውሮፕላኖች አብዛኛውን ጊዜ እስከ 50 በመቶ የሚደርስ የተቀላቀለ ነዳጅ ብቻ እንዲጠቀሙ ይፈቀድላቸዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) አረንጓዴ ነዳጅን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሉም። ከዩኬ መንግሥት በድጋፍ የሚገኝን ገንዘብ ጨምሮ በአውሮፓውያኑ 2025 አምስት ፋብሪካዎችን የመገንባት ፍላጎት አለው።
አየር መንገዶች 100 በመቶ አረንጓዴ ነዳጅን በመጠቀም የሚደረገውን የመጀመሪያውን የረዥም ርቀት በረራ እንደ አንድ ትልቅ ምዕራፍ ተመልክተውታል። ባለሙያዎች ግን እንዲህ ያሉት ነዳጆች አስገራሚ የሚባል ለውጥ አያመጣም ይላሉ።
በክራንፊልድ ዩኒቨርሲቲ የአቪዬሽን እና የአካባቢ ጥበቃ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጋይ ግራተን “ግብዓቱ ስለሌለን አብዛኛውን የነዳጅ ፍላጎታችንን በዚህ መንገድ ማምረት አንችልም። ቢመረቱም ደግሞ ሙሉ በሙሉ አረንጓዴ አይደሉም” ብለዋል።
እያደገ የመጣው የዚህ ነዳጅ አጠቃቀም “ለወደፊቱ፣ እውነተኛ የተጣራ ቴክኖሎጂዎች ለመጠቀም እንደ አንድ እርምጃ” መታየት አለበት ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በ2030፣ 10 በመቶው የአቪዬሽን ነዳጅ በዚህ መልኩ የተዘጋጀ እንዲሆን ለመጠየቅ አቅዷል።
በዩናይትድ ኪንግደም የተመዘገቡ አየር መንገዶችን የሚወክለው ዩኬ አየር መንገድ እንዲህ ያለውን መስፈርት ለማሟላት በተመጣጣኝ ዋጋ ነዳጁን ማግኘት መቻል ያስፈልጋል ብሏል።
የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች እንደሚሉት የበካይ ጋዝ ልቀትን በፍጥነት ለመቀነስ ብቸኛው መንገድ የበረራ ቁጥርን መቀነስ ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት እና የኢንዱስትሪው ኃላፊዎች በ 2050 የተሳፋሪዎችን ቁጥር እየጨመሩ የካርበን “ልቀቱን ዜሮ” ማድረስ እንደሚቻል ያምናሉ።