ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዓለም በዕድሜ ትልቋ ተብለው የተመዘገቡት ፈረንሳያዊት መነኩሴ በ118 ዓመታቸው አረፉ
በዓለም በዕድሜ ትልቋ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፈረንሳያዊቷ መነኩሴ ሉሲል ራንዶን በ118 ዓመታቸው አረፉ።
በ1944 (እአአ) ሲስተር አንድሬ በሚል ስም ምንኩስናን የተቀበሉት ራንዶን ፈረንሳይ ቱሎን ውስጥ በሚገኝ የአዛውንቶች መንከባከቢያ ውስጥ በእንቅልፍ ላይ ሳሉ ነው ያረፉት።
መነኩሲቷ በ1904 ደቡባዊ ፈረንሳይ ውስጥ ተወልደው ሁለት የዓለም ጦርነቶችን ያሳለፉ ሲሆን፣ መላ ሕይወታቸውን ለካቶሊክ እምነት የሰጡ ነበሩ።
ቀደም ሲል በጋዜጠኞች ስለዕድሜያቸው መርዘም ምስጢር ተጠየረቀው “ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው” በማለት መልሰው ነበር።
ሲስተር አንድሬ በዕድሜ ዘመናቸው 27 የፈረንሳይ መሪዎችን ለማየት በቅተዋል።
የእንክብካቤው ማዕከል ቃል አቀባይ ዜና እረፍታቸውን ይፋ ባደረገበት ጊዜ መነኩሲቷ “በሞት የተለያቸውን የሚወዱትን ወንድማቸውን ለመከተል ፍላጎት ነበራቸው” በማለት እረፍታቸው “ነጻነታቸው ነው” ብሏል።
ሲስተር አንድሬ በመጨረሻ ዕድሜያቸው ማየት ተስኗቸው በተሽከርካሪ ወንበር ይንቀሳቀሱ የነበሩ ቢሆንም፣ ከእሳቸው በዕድሜ ያነሱትን ሳይቀር ለሌሎች እንክብካቤ ያደርጉ ነበር።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ከኤኤፍፒ ዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “አንዳንድ ሰዎች ሥራ ይገድላል ይላሉ፤ ለእኔ በሕይወት የቆየሁት በሥራ ምክንያት ነው” በማለት አስከ 108 ዓመታቸው ድረስ ሲሰሩ እንደነበር ተናግረዋል።
ጨምረውም ወደ መንግሥተ ሠማያት መሄድ እንደሚፈልጉ የተናገሩ ሲሆን፣ በምድር ላይ በነበራቸው ቆይታ ቸኮሌት መመገብ እና በየቀኑ አንድ ብርጭቆ ወይን መጠጣት እንደሚያስደስታቸው ተናግረዋል።
ሲስተር አንድሬ ለተወሰነ ጊዜ የአውሮፓ በእድሜ ትልቋ ሆነው ከቆዩ በኋላ፣ ጃፓናዊዋ ካኔ ታናካ ባለፈው ዓመት በ119 ዓመታቸው ሲያርፉ እሳቸውን ተከትለው በጊነስ የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ በሕይወት ያሉ በእድሜ የገፉ ሴት ሆነው ተመዝግበዋል።
በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 2021 በኮቪድ ተይዘው ሲያገግሙ የመጀመሪያዋ ከበሽታው የዳኑ በእድሜ የገፉ ሰው ሆነው ተመዝግበዋል።
ሲስተር አንድሬ ለመጨረሻ ጊዜ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ “ሰዎች ከመጠላላት ይልቅ እርስ በርስ መደጋገፍ እና መዋደድ አለባቸው። ያሉንን ነገሮች ከተካፈልን፣ ነገሮች የበለጠ የታሸለ ይሆናሉ” ብለዋል።