በአሜሪካ የፊልም ባለሙያዎች ሽልማት ላይ ታድመው የነበሩ ታዋቂ ሰዎች በኮቪድ ተያዙ

በጎልደን ግሎብ የፊልም ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ከታደሙት ታዋቂ ሰዎች መካከል በርካቶቹ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ ተረጋገጠ።

ኮሊን ፋረል፣ ብሬንዳን ግሊሰን፣ ጄሚ ሊ ከርቲስ እና ሚሸል ፊፈርን ጨምሮ ሌሎችም የፊልም ከዋክብት በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከታደሙ ከቀናት በኋላ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

በዚህም ሳቢያ ባለፈው እሁድ በቴሌቪዥን የተላለፈው በሃያሲያን ምርጫ በሚሰጠው ሽልማት “ዘ ክሪቲክስ ቾይዝ አዋርድ” ላይ ከተጋበዙት ሰዎች ቁጥር ዝርዝር ውስጥ የሚቀሩ ሰዎች በመበርከታቸው፣ ታዳሚዎች የኮቪድ ምርመራ እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል።

በርካቶችም ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሳይገኙ የቀሩ ሲሆን፣ የተወሰኑ ታዋቂ ሰዎች ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

ሚሸል ፊፈር በኢንስታግራም ገጿ ላይ “በኮቪድ በመያዜ ምክንያት የሃያስያን ምርጫ ሽልማትን ባለመታደሜ አዝኛለሁ” ስትል አስፍራለች።

ፊፈር በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለአንድ ተዋናይ ሽልማት እንድታበረክት ፕሮግራሙ ውስጥ ተካትታ የነበረ ሲሆን እሷ ባለመገኘቷ በጆን ጉድማን እንዲሰጥ ተደርጓል።

ሚሸል ፊፈር በሃያስያን ምርጫ ሽልማት ላይ እንዳትገኝ ምክንያት የሆናት በጎልደን ግሎብ ሽልማት ላይ ከተሳተፈች በኋላ በኮቪድ በመያዟ መሆኑን ገልጻለች።

ለፊልም እና ለሙዚቃ ባለሙያዎች ሽልማት በሚበረከትበት በዚህ ወቅት በሥነ ሥርዓቶች ላይ የሚታደሙ ሰዎች ከኮሮናቫይረስ አንጻር ምርመራ፣ ክትባት እና ማስክ የማድረግ ጥንቃቄዎች ወጥ እንዳልሆኑ ተዘግቧል።

አንዳንድ ታዳሚዎች በአካል በሚገኙባቸው ሥነ ሥርዓቶች ምንም አይነት የጥንቃቄ እርምጃ የሚጠየቅባቸው አይደሉም። ነገር ግን ጎልደን ግሎብ እና ክሪቲክስ ቾይዝ አዋርድን የመሳሰሉት ደግሞ የምርመራ ውጤት፣ የክትባት ማስረጃ ወይም ሁለቱንም ሲጠይቁ ነበር።

የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች በሆሊዉድ የሽልማት ሥነ ሥርዓቶች ላይ የታደሙ ታዋቂ ሰዎች በኮቪድ መያዛቸውን በተመለከተ እምብዛም እንዳልተደነቁ ተናግረዋል።

“ይህ የማይጠበቅ አይደለም” ያሉት ዶ/ር ጆን ብራውንስታይን “ጉንፋንን የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ቫይረሶች በሚበዙበት በዚህ ወቅት ማስክ ሳያደርጉ በቤት ውስጥ በቅርበት መሰባሰብ በቫይረስ የመያዝ ከፍተኛ አጋጣሚ ይኖረዋል” ብለዋል።

በአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል መረጃ መሠረት ባለፉት ስድስት ሳምንታት፣ በየሳምንቱ 400 ሺህ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሪፖርት ቢደረግም ለኮቪድ ያለው ፍርሃት እና የሚደረገው ጥንቃቄ እየጠፋ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚከሰተው ሞትም እየጨመረ ወደ 3,907 መድረሱን ባለፈው ሳምንት የወጣው የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከሉ መረጃ አመልክቷል።