በትግራይ እና በኦሮሚያ ካጋጠመው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ጀርባ ያሉ ምክንያቶች

በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ፤ በተለይ በትግራይ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ የነበረው የባንክ አገልግሎት መጀመሩ ይታወሳል።
ሆኖም ሥራ ጀምረው የነበሩት ባንኮች በጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ሙሉ አግልገሎት እየሰጡ እንዳልሆነ የክልሉ ነዋሪዎች እና የባንክ ሠራተኞች ይገልጻሉ።
በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር በተያያዘ የፀጥታ ችግር ባለበት የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎችም አንዳንድ ባንኮች ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የተወሰኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ደንበኞች ማውጣት የሚችሉት የጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ገደብ ጥለዋል።
በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸው እንደሆነ በትግራይ እና የፀጥታ ችግር ባለባቸው የኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ለመሆኑ በትግራይ እና ምዕራብ ኦሮሚያ ያጋጠመው የጥሬ ገንዘብ እጥረት መነሻው ምንድን ነው?
“መድኃኒት መግዣ ብር ማውጣት ያልቻሉ ደንበኞች”
አቶ ክፍሎም የአብይ አዲ ነዋሪ ናቸው። ከተማዋ ከነዋሪዎች በተጨማሪ በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎችን አስጠልላለች።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ሌሎች የግል ባንኮች ሥራ ጀምረው ነበር። አሁን ግን ከሞላ ጎደል ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸው አቶ ክፍሎም ይናገራሉ።
“ቀደም ሲል በቀን እስከ 10 ሺህ ብር ማውጣት እንችል ነበር። ከዚያ የገንዘብ እጥረት አጋጥሟል በሚል ወደ 2 ሺህ ብር አወረዱት። አሁን ጭራሽ ብር የለንም ማለት ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል።”
በዚህ ምክንያት በጦርነቱ ለከፍተኛ ችግር የተዳረጉ ነዋሪዎች ችግራቸውን ለመፍታት የሚሆን ጥሬ ገንዘብ ማግኘት አልቻልንም ይላሉ።
አቶ ክፍሎም እንደሚሉት “በጣም የሚያሳዝነው ከገጠር የሚመጡ ሰዎች መረጃ ስለባንኮቹ አገለግሎት መረጃ ስለማይኖራቸው ገንዘብ እናገኛለን ብለው ያላቸውን ከፍለው በትራንስፖርት አንዳንዶች ደግሞ በእግር የሚመጡም አሉ።
“ሌሎች ደግሞ ከባንክ ገንዘብ አውጥተው መድኃኒት ለመግዛት የሚመጡም አሉ። ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ ባንኮች ጋር ሲደርሱ አገልግሎት የለም ይባላሉ።”
“ብር ላኩ አልተባልንም”
ባለፈው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከትግራይ ክልል አመራሮች ጋር ተገናኝተው ወደ ትግራይ አምስት ቢሊዮን ብር መላኩ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም በርካታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርጫፎች በራቸውን ከፍተው አገልግሎት መስጠት ጀምረው ነበር።
ሆኖም ባንኮቹ የተላከላቸው ብር ከአስር ቀናት በላይ እንዳላቆያቸው እና የገንዘብ እጥረት መልሶ ማጋጠሙን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በትግራይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲስትሪክት ኃላፊ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“አምስት ቢሊዮን ብር ነው የተላከው። ሦስት ቢሊዮን ለንግድ ባንክ፤ ለወጋገን እና ለአንበሳ ባንክ ደግሞ አንድ አንድ ቢሊዮን ብር አገኙ። ነገር ግን ወጪ እንጂ ገቢ አልነበረም። ለዚህ ነው እጥረት ያጋጠመው።”
የቀረበው ገንዘብ በማለቁ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲልክ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም “ብር ላኩ አልተባልንም” የሚል ምላሽ እንዳገኙ የሚናገሩት ኃላፊው፤ ባንኮች ከሦስት ሺህ ብር በላይ ለደንበኞቻቸው መስጠት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ።
“ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ እንዲልክልን ሦስት ጊዜ ጠይቀናል። ጉዳዩ ፖለቲካዊ ነው ብዬ አምናለሁ። በየቀኑ ከባንኩ ጋር እንነጋገራለን።”
ኃላፊው በተለይ መድኃኒት ለመግዛት ገንዘብ የሚሹ ደንበኞች የጥሬ ገንዘብ እጥረት እያንገላታቸው መሆኑን አንስተዋል።
“የስኳር፣ ካንሰር እና የሌሎች በሽታዎች ማስረጃ ይዘው የሚመጡ አሉ። አቅም በፈቀደ መጠን ትንሽ ጨምረው ለመስጠት ይሞክራሉ። ሆኖም አጥጋቢ አይደለም።”
በዚህ ጊዜ አንዳንድ ቅርንጫፎች የተወሰኑ ተቋሞች ገቢ ከሚያደርጉት ጥሬ ገንዘብ አገልግሎት ለመስጠት እየታገሉ እንደሚገኙ የሚገልጹት ኃላፊው፡ ቅርንጫፎቹ “ትንሽ ብር ሲሰበስቡ ይከፈታሉ፤ ብር ሲታጣ ይዘጋሉ” ይላሉ።
ከሰላም ስምምነቱ በፊት በትግራይ ክልል ባንኮች ከአገልግሎት ውጪ ሆነው ሳለ ከውጪ ወደ ትግራይ ገንዘብ ለማስተላለፍ ከሚላከው ገንዘብ እስከ 40 በመቶ ድረስ ለሚያስተላልፉት ግለሰቦች ይከፍሉ እንደነበር ይታወሳል።
አሁን ባንኮች አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ይህ ሕገ-ወጥ ክፍያ ይቀራል ተብሎ ተስፋ ቢጣልበትም ከባንክ አካውንት ወደ አካውንት የሚላላኩ ሰዎች አሁንም በኮሚሽን እንደሚሰሩ ቢቢሲ ተረድቷል።
አንድ ባንክ ጥሬ ገንዘብ ያለው ሰው ለሌላ ሰው ሲያስተላልፍ 7 በመቶ ጭማሪ ኮሚሽን እንደሚጥል ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ከ5 እስከ 7 በመቶ እየከፈልክ ነው ከባንክ አካውንት የምታስተላልፈው። ጥሬ ገንዘብ ለመቀበል ከአካውንትህ እስከ ሰባት በመቶ ጨምረህ ትከፍላለህ” ይላሉ አቶ ክፍሎም።

“ለባንክ ቅርበት ያለው የፈለገውን ያወጣል”
የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ ከባንክ ወጪ የሚደረግ የገንዘብ መጠን ገደብ፣ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የባንኮች አገልግሎት አለመኖር በምዕራብ ኦሮሚያ የብዙ ነዋሪዎች ምሬት ከሆነ ሰነባብቷል።
የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ኤቢሳ መርጋ በሚኖርባት የደንቢ ዶሎ ከተማ የቤት ኪራይ ለመክፈል የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከባንክ ለማውጣት መቸገሩን ይናገራል።
“2500 ብር የቤት ኪራይ፤ እሱንም መንግሥት የሚከፍልልኝን ለማውጣት ሄጄ ሊሰጡኝ አልቻሉም። ከ1000 ብር በላይ ማውጣት አይቻልም ብለው መለሱን።”
ሌላኛው የደንቢ ዶሎ ከተማ ነዋሪ ደግሞ የጥሬ ገንዘብ እጥረት በከተማዋ እንደሰፈነ ጠቅሶ፤ ይህ ጉዳይ ለብልሹ አሠራር መንገድ ከፍቷል ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
“የባንክ ማናጀር አሊያም ከባንኮች ጋር ቀረቤታ ያለው ሰው የፈለገውን ያክል ገንዘብ ማውጣት ይችላል። ተጠቃሚው ሰልፍ እየጠበቀ ከባንኩ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያለው ሰው ያሻውን ያህል ገንዘብ አውጥቶ ሲሄድ አይቻለሁ።”
ከምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ያናገርናቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ወደ ባንክ ሲያቀኑ የቅርንጫፍ ባለሙያዎች ‘ሞባይል ባንኪንግ’ በመጠቀም እርስ በርስ ገንዘብ ተላላኩ ይሏቸዋል።
የጥሬ ገንዘብ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች ያሉ ሰዎች ብር ሲፈልጉ ወደሚያውቋቸው ነጋዴዎች በመሄድ በሞባይል አማካይነት የሚፈልጉትን የብር መጠን ልከው ጥሬ ገንዘብ ይቀበላሉ።
ነገር ግን ይህን ልውውጥ ለማካሄድ ሁለቱ ሰዎች የሚተዋወቁ አሊያም የሚግባቡ ሊሆን ይገባል።
የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ኤቢሳ እንደሚለው፣ በደንቢ ዶሎ ከተማ ከባንክ ገንዘብ ለማውጣት የሚሰልፉ በርካታ ሰዎችን ማየት በጣም የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የተለያዩ ሥፍራዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል በሚያጋጥም ግጭት ምክንያት ባንኮችን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥራ ለማቆም ይገደዳሉ።
በቄለም ወለጋ እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ይህ ችግር በጣም የከፋ በመሆኑ ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ከተሞች በመሄድ ነው ገንዘብ የሚያወጡት።
የሙጊ እና ጊዳሚ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች እና ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ባለማግኘታቸው ወደ ደንቢ ዶሎ ከተማ በመምጣት ለከፋ ችግር እንደሚጋለጡ መምህሩ ይናገራል።
ደንቢ ዶሎ አካባቢ ካሉ ወረዳዎች የሚመጡ ነዋሪዎች ብዙ መንገድ ተጉዘው የሚፈልጉትን ገንዘብ በአንድ ቀን ማውጣት ስለማይችሉ በከተማዋ ለቀናት መቆየት ግድ ይላቸዋል። ይህ ደግሞ ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋቸዋል።
በምዕራብ ወላጋ ዞን፤ ገንጂ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አንዲት እናት እንደሚሉት በወረዳው የነበሩ ሁለት ባንኮች ‘በፀጥታ ችግር ምክንያት’ ከተዘጉ ስድስት ወራት አልፏቸዋል።
እኚህ እናት እንደሚሉት ነዋሪዎች ገንዘብ ከባንክ ማውጣት በሚፈልጉ ጊዜ ጊምቢ እና ዩብዶ ወደሚባሉ ከተሞች አቅንተው አገልግሎት እንደሚያገኙ ይናገራሉ።
ቢቢሲ፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ባገኘው መረጃ መሠረት በምዕራብ ኦሮሚያ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት በአካባቢው ያሉ ቅርንጫፎች ጥሬ ገንዘብ ይዘው ማቆየት ስለማይችሉ ይህም ለጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ሆኗል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አልሰን አሰፋ፤ ባንካቸው በዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንደማይሻ እና ይህን ምላሽ መስጠት የሚችለው ብሔራዊ ባንክ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ፤ ከብሔራዊ ባንክ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።












