ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዙሪያችን ያሉ ነገሮች ሁሉ ከኢንተርኔት ጋር ሲተሳሰሩ ዓለም ምን ትመስላለች?
ፍሪጅ ውስጥ ያስቀመጡት ወተት ሲያልቅ ፍሪጁ ቢነግርዎ፣ ዘራፊ አጥር ዘሎ ሲገባ በርዎ በስልክዎ ጥቆማ ቢያደርስዎ፣ በአካባቢዎ ያለውን የአየር ሁኔታ ከግምት አስገብቶ የቤትዎን ሙቀት እና ቅዝቃዜ የሚወስን መሣሪያ ቢገጥሙ፣ በየትኛው መንገድ ምን ያህል የትራፊክ መጨናነቅ እንዳለ ተረድቶ አማራጭ መንገድ መኪናዎ ቢያመለክትዎ. . .
እነዚህ ሁሉ ምናባዊ አይደሉም። በቴክኖሎጂ ታግዘው እውን ሆነዋል።
አሁን አጠገብዎ የሚያዩዋቸው ቁሶች መረጃ በኢንተርኔት እንዲቀባበሉ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ከተጠነሰሰ ቆይቷል።
ቁሶቹ አካባቢያቸውን በዕይታ፣ በድምጽ ወይም በእንቅስቃሴ ተረድተው ያገኙትን መረጃ ይለዋወጣሉ።
ይህም ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ (Internet of Things ወይም IoT) ይባላል። ኑሮን እና ሥራን ፈጣን እና ቀላል ያደርጋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ ምንድን ነው? እንዴት ይሠራል? ምንስ ይጠቅመናል? ስንል የአይኮግ ላብስ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ጌትነት አሰፋን ጠይቀናል።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) እንዲሁም ተያያዥ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ የሚሠራው ተቋም መሥራች የሆነው ጌትነት ማብራሪያውን የሚጀምረው በአካባቢያችን ያሉ ነገሮች መረጃ (Information) እንደሚሆኑ በመጥቀስ ነው።
“. . .የምናያቸው ነገሮች ሁሉ መረጃ ናቸው። እነዚህ መረጃዎች ማእከላዊ ወደሆነ የኢንተርኔት ቋት ማምጣት ከቻልን መረጃውን መቆጣጠርና ለጠቃሚ አገልግሎት ማዋልም እንችላለን።”
የመጀመሪያው ደረጃ፣ እንቅስቃሴን አንብበው የሚሠሩ (Sensors)፣ የበይነ መረብ ካርታ (GPS) ወይም ሌሎችም መረጃ ሰብሳቢዎችን ከቁሶች ጋር ማገናኘት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ፣ ከዚህ የምናገኘውን መረጃ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ወደ ኮምፒውተራችን እንወስዳለን።
ከዚህ ቀጥሎ ያለው በመረጃዎቹ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ ማሳለፍ ነው።
ነገሩን የበለጠ ለመረዳት ጌትነት ሁለት ዘርፎችን ምሳሌ ይሰጣል። ግብርና እና መጓጓዣ።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ግብዐቶች የሚሠራ ከተማ (Smart City) ተገነባ እንበል። በከተማው ያሉ መኪኖች፣ አሽከርካሪዎች፣ ተሳፋሪዎች፣ አምቡላንሶች ወይም ፖሊሶች በኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ መረጃ እንዲለዋወጡ ማድረግ እንችላለን።
ይህን ለማድረግ፣ ምን ያህል መኪና በዚህ መንገድ አልፏል? የሚለውን የሚቆጥር መሣሪያ መግጠም ይቻላል።
በተጨማሪም ካሜራ ማስቀመጥ ወይም እያንዳንዱ መኪና ውስጥ ጂፒኤስ መግጠም ይቻላል።
የመንገዱን ቁልቁለትና ዳገት እንዲሁም ጉድጓዶች ወይም የተበላሹ መንገዶች የሚለይ መሣሪያ መግጠም ሌላው አማራጭ ነው።
“. . .እነዚህ ሴንሰሮች የሚሰበስቧቸው መረጃዎች ወደ ማእከላዊ ቋት የሚላኩና የሚከማቹ ናቸው። እነዚህ ትንንሽ ሀርድዌሮች ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ ይባላሉ። እነዚህን ወደ መረጃ በመለወጥ ከዚያም ኮምፒውተራችን ላይ በማድረግ ወደ ጠቃሚ መረጃ በመለወጥ ሁነቶችን መቆጣጠር ይቻላል” ሲል ጌትነት ያስረዳል።
ሁለተኛው ምሳሌ ግብርና ነው።
ሰው አልባ አውሮፕላን (Drone) ላይ ሴንሰር በመግጠም መረጃ መሰብሰብ ይቻላል። ሙቀት ተጠቅሞ ምሥል የሚያወጣ ካሜራ በመግጠም ወይም የሰብልን ምርታማነት የሚፈትሽ መሣሪያ በመግጠም መረጃ ይሰበሳል።
በተጨማሪም መሬት ውስጥ የሚቀበሩ ሴንሰሮች፣ የአፈር እርጥበትን ወይም የማዕድን ይዘትን እየለኩ ወደ ኮምፒውተር መረጃ ይልካሉ።
“. . .በሺዎች፣ በሚሊዮኖችና በትሪሊየኖች የሚቆጠሩ ኤሌክትሮኒክ ሀርድዌሮች የሚሰበስቡትን መረጃ በአንድ ኮምፒውተር ላይ አስቀምጦ ያንን ወደ ጠቃሚ መረጃ መቀየር ማለት ነው” ይላል ባለሙያው።
‘ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ’
ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ፣ በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ምሳሌ እንዳየነው የትራፊክ ፍሰትን ለመቆጣጠር እንዲሁም ግብርናን ለማሳለጥ ይረዳል።
በእርግጥ በሌሎች ዘርፎችም እየተተገበረ ነው።
በዙርያችን የምናያቸው ነገሮች ባጠቃላይ ከኢንተርኔት ጋር ተሳስረው የምናይበት ዘመን እየቀረበ ይመስላል።
አሁንም ራሱ አብላጫው የዓለም ሕዝብ (ቢያንስ የኢንተርኔት ተደራሽነት ባለባቸው አካባቢዎች) አብዛኛውን ጊዜ የሚያጠፋው ኤሌክትሮኒክስ ላይ ነው። ማንኛውንም ነገር ወደ መረጃ መለወጥ የሚቻለውም ለዚህ ነው።
በሥነ ሕይወት እና በኬሚስትሪ ያሉ ሳይቀሩ ወደ መረጃነት እየተለወጡ እንደሆነ ጌትነት ያነሳል።
“አተም፣ ሚኒራል፣ ዲኤንኤ፣ ኒውሮዳታ እና ሰዎችም ሳይቀሩ ወደ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተቀይረዋል። በስተመጨረሻ የሚቀረው ነገር መረጃ ይሆናል” ይላል።
ድምጽ፣ ምሥልና እንቅስቃሴ የሚያብላሉ ሴንሰሮች በመጠቀም የሰው ልጅ አካባቢውን ወደ መረጃ ክምችት እንደሚቀይር ይጠበቃል።
ጤና፣ ትምህርት፣ ንግድ ወይም መዝናኛ አሁን እንደምናውቀው ሆኖ አይቀጥልም። በጣም ይራቀቃል። ዛሬ እንደ ቅንጦት የምናያቸው ነገሮች ለወደፊት የሁሉም ሰው ንብረት ይሆናሉ።
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የተንቀሳቃሽ ስልክ ዘመን ባለ ገመድ ስልክን በእጥፍ ማስናቁ ነው። አሁን እጁ ላይ ስልክ የሌለ ሰው ስንት ነው?
ይህ ስልክ በዙርያችን ካሉ ቁሶች ጋር መረጃ ወደመለዋወጥም ይሻገራል።
ጌትነት ለወደፊት የሚጠብቅን ዓለም እንዲህ ነው የሚገልጸው።
“. . .የኢንተርኔት፣ የመረጃ እና የዕውቀት ዘመንነቱ ሁሉንም ይቀይራል። አሁን የዕውቀት እጥረት የለብንም። ዕውቀትን ወደ ሀብት መቀየር ነው የቀረን። ይህም ለወደፊት ይሆናል። በጣም የተሻለና ብሩሕ የወደፊት ዓለም እየተገነባ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ።”
‘ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ’ የሚፈጥረው ዓለም
የ21ኛው ክፍለ ዘመን ጉልህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከሚባሉት አንዱ ነው።
እስካሁን ከሰባት ቢሊዮን በላይ ቁሳቁሶች በኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ መተሳሰራቸው ሲገለጽ፣ እአአ በ2025 እስከ 22 ቢሊዮን እንደሚደርሱም ይጠበቃል።
ከቁሶች ባሻገር ከሰዎችና ከእንስሳት ጋርም ማገናኘት ይቻላል። የልብ ሕሙማን የጤና ሁኔታቸውን የሚቆጣጠር መሣሪያ ሲገጠምላቸው ያንን መሣሪያ ከሌሎች መሣሪያዎች ጋር ማገናኘት ይቻላል።
እንስሳት ሲንቀሳቀሱ የሚከታተል መሣሪያ ተገጥሞላቸው መረጃ መሰብሰብም ይቻላል።
ፍሪጅ፣ መኪና፣ በር እና ሁሉንም ቁስ ከኢንተርኔት ጋር ማገናኘት ተቻለ ማለት በሰዎች፣ በቁሳቁሶች እና በሂደት መካከልም ትስስር ተፈጠረ ማለት ነው።
እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩት ቁሶች መረጃ ይሰበስባሉ፤ መረጃውንም ይለዋወጣሉ። ቁሳዊው ዓለምና የበይነ መረቡ ዲጂታል ዓለም አንድ ሆኑ ማለት ነው።
ሐሳቡ ከተጠነሰሰ ቢቆይም ቁሶች መረጃ የሚሰበስቡበት ሴንሰር በቀላሉ የሚሠራና የሚገኝ መሆኑ ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስን ስኬታማ አድርጓል።
የኢንተርኔት ትስስር መስፋፋት፣ የክላውድ ኮምፒውቲንግ መራቀቅ፣ የማሽን ለርኒንግ እና አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ወደላቀ ደረጃ መሸጋገርም አወንታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።
መሣሪያዎችን በኔትወርክ ማስተሳሰር ሥራን ለማቀላጠፍ እየዋለ ነው። ጊዜ ለመቆጠብና የተሻለ ኑሮ ለመግፋት ሚና እንዳለውም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከዚህ በተቃራኒው፣ ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ በማንኛውም ጊዜ በብዛት መረጃ መሰብሰቡ ከመረጃ ደኅንነት አንጻር የሚያሳስባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ትችት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
አንዳች አሳሪ መርሕ ሳይኖር፣ መሸሸግ የምንፈልጋቸውን መረጃዎች ሳይቀር መሰብሰቡ፣ ሰብስቦም ከሌሎች መሣሪያዎች ጋር መለዋወጡ ተተችቷል።
በመሣሪያዎች መካከል ሁሉም መረጃ በኢንተርኔት አማካይነት የሚዘዋወር ከሆነ መረጃ ሰርሳሪዎች በቀላሉ የግለሰቦችን፣ የተቋማትን እና የአገራትን መረጃ ሊመዘብሩም ይችላሉ።
ሁሉም መሣሪያ በኢንተርኔት ተሳስሮ የአንዱ መሣሪያ መሥራት ለሌላው ውጤታማነት አስፈላጊ እየሆነ ሲሄድ፣ አንድ መሣሪያ እንኳን ቢበላሽ አጠቃላይ ሥራ ይቃወሳል የሚለው ሌላው ስጋት ነው።
መቼ እንደርስበታለን?
በቴክኖሎጂ ልህቀት የምዕራቡ እና የምሥራቁ ዓለም ከደቡቡ ዓለም ቀደም ማለቱን መነሻ አድርገን ለጌትነት አንድ ጥያቄ አንስተናል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የተቀረው የደቡብ ዓለም ከተቀረው ዓለም እኩል በኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ ይተሳሰራል?
መልሱ “አፍሪካ በየትኛው አህጉር ተሞክሮ ልሂድ የሚለወ ብዙ አማራጭ አላት” የሚል ነው።
“. . .እነሱ መቶ ዓመታት የፈጀባቸውን ጉዞ እኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማንደርስበት ምንም ምክንያት የለም። እሱን ዘለን ሌላ የምጣኔ ሀብት ደረጃ ላይ የምንደርስበትም ዕድል እንዳለ ነው” ሲል ያክላል።
ይህን የሚለው ያለ ምክንያት አይደለም። የቴክኖሎጂን አካሄድ እንደ ማስረጃ ይጠቅሳል።
ቴክኖሎጂ አገርና አህጉራት ላይ ከተመሠረተው የድንበር ክፍፍል ይዘላል።
“ቴክኖሎጂ የቦታ ገደብን አልፎ የሚሄድ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ፣ ክሪፕቶከረንሲ እና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች አገር ሳይሆን ቦታ (Location) መጠየቃቸው አካላዊው ድንበር ለቴክኖሎጂ እንደማይሰራ ማሳያ ነው” ሲል ያስረዳል።
ቢዘገይም በኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ ከሚፈጠረው ዓለም የሚቀር ያለ አይመስልም።