የአፍሪካ ዋንጫ፡ የግብፅ ድራማዊ ትዕይንት፣ የጋና እና አይቮሪ ኮስት አጣብቂኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በርካታ ትዕይንቶችን ባስተናገደው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሁለት ጨዋታ ግብጽ ከኬፕ ቨርዴ 2 አቻ በመለያየት ጥሎ ማለፉን ተቀላቀለች።
ግብፅ በተቆጠሩባት ሁለት ጎሎች ሰማያዊ ሻርኮቹን እና ጋናን ተከትላ ምድቡን ሦስተኛ ሆና የምታጠናቅቅ መስላ ነበር።
የፈርኦኖቹ አጥቂ ሙስጠፋ መሐመድ በ93ኛው ደቂቃ ቡድኑን አሸናፊ ያደረገ የሚመስል ኳስ ከመረብ ለማሳረፍ ችሏል።
ኬፕ ቨርዴ ከስድስት ደቂቃ በኋላ አቻ ለመሆን ችላለች።
በምድቡ ሌላ ጨዋታ 2 ለ 0 ስትመራ የቆየችው ጋና የማታ የማታ በሞዛምቢክ በተቆጠሩባት ሁለት ጎሎች አቻ በመለያየቷ ፈርኦኖቹ የምድቡን ሁለተኛ ደረጃ ለመያዝ ችለዋል።
በጉዳት ሞሐመድ ሳላህን ማሰለፍ ያልቻለችው ግብፅ ቤንቺሞል ባስቆጠራት ጎል ብትመራም ተቀይሮ የገባው ትሬዝጌ አቻ አድርጓታል።
ሦስት ነጥብ ማግኘት ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሳልፋቸው ፈርኦኖቹ በሞሐመድ ጎል 2 ለ 1 መምራት ችለው ነበር።
ብሪያን ቴክሴራ ባለቀ ሰዓት ያስቆጠራት ጎል ቡድኑን አቻ ሲያደርግ ግብፅ ከምድቡ የማለፍ ዕድሏን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶት ነበር።
ሆኖም 2 ለ 0 ስትመራ የቆየችው ጋና በ91ኛው እና በ94ኛው ደቂቃ ላይ በሞዛምቢክ በተቆጠሩባት ጎሎች አቻ በመለያየቷ ሦስቱንም ምድብ ጨዋታዎች አቻ የተለያየችው ግብፅ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።
ጋና በጆርዳን አይው ሁለት የፍጹም ቅጣት ምት ግቦች ነበር ለመምራት የቻለችው።
ሲፕሪያኖ ሳታሞ በፍጹም ቅጣት ምት እና ኢስናርድ ማንዳቫ ለሞዛምቢክ ኳስና መረብን አገናኝተዋል።
ኬፕ ቨርዴ ምድቡን በሰባት ነጥብ በመምራት ወደ ቀጣዩ ዘር አልፋለች።
ሁለት ነጥብ ብቻ ያላት ጋና ሦስተኛ ደረጃን ስትይዝ ሞዛምቢክ አራተኛ ሆናለች።
በምድብ አንድ በተደረጉ ጨዋታዎች አስተናጋጇ ኮትዲቯር አስደንጋጭ ሽንፈት ከማስተናገድ ባለፈ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሏ ተመናምኗል።
ዝሆኖቹ በደጋፊዎቻቸው ፊት 4 ለምንም በሆነ ሰፊ ውጤት በኢኳቶሪያል ጊኒ ተሸንፈዋል።
ለኢኳቶሪያል ጊኒ ኤሚሊዮ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጠር ቀሪዎቹን ጎሎች ፓብሎ ጌኔት እና ያኒክ ቡይላ ከመረብ አሳርፈዋል።
በምድቡ ሌላ ጨዋታ ናይጄሪያ ጊኒ ባሳዎን አንድ ለምንም ማሸነፍ ችላለች።
ናይጄሪያ ሦስቱን ነጥብ ማሳካት የቻለችው ኦፓ ሳንጋንቴ በራሱ ላይ ባስቆጠራት ግብ ነው።
ምድብ አንድን ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ናይጄሪያ በእኩል ሰባት ነጥብ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው አጠናቀዋል።
አይቮሪ ኮስት በሦስት ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዛለች።
ጊኒ ቢሳዎ ያለምንም ነጥብ በጊዜ ከውድድሩ መሰናበቷን አረጋግጣለች።
አይቮሪ ኮስት ጥሩ ሦስተኛ በመሆን ወደ ጥሎ ማለፉ ለመግባት ዕድል ስላለት የሌሎች ምድቦችን ውጤት ለመጠባበቅ ተገዳለች።












