ደጋፊዎች የዘረኝነት ጥቃት ከሰነዘሩ ቡድናቸው በፎርፌ እንዲቀጣ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ደጋፊዎች የዘረኝነት ጥቃት ከፈጸሙ ጨዋታው ተቋርጦ ቡድናቸው በፎርፌ እንዲቀጣ ጠየቁ።
ኢንፋንቲኖ ይህንን የጠየቁት ቅዳሜ ዕለት የዩዲኒዜ እና የሼፊልድ ዌንስዴይ ደጋፊዎች የተጋጣሚዎቻቸውን ጥቁር ተጫዋቾች ዘረኛ በሆነ ስድብ ካጠቁ በኋላ ነው።
ኤሲ ሚላን ዩዲኒዜን ባሸነፈበት ጨዋታ፤ የተሸናፊው ቡድን ደጋፊዎች የሚላኑ ግብ ጠባቂ ማይክ ማግናን ላይ ያደረሱትን የዘረኝነት ጥቃት ተከትሎ ጨዋታው ለአጭር ጊዜ ተቋርጦ ነበር።
በተመሳሳይ ሼፊልድ ዌንስዴይ ከኮቨንተሪ ሲቲ ጋር በነበራቸው ጨዋታ የኮቨንተሪው ካሴይ ፓልመር በደጋፊዎች የዘረኝነት ጥቃት እንደደረሰበት ተናግሯል።
ኢንፋንቲኖ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ የቆዳ ቀለምን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በሚሰነዝሩ ደጋፊዎች ክለብ ላይ ከባድ ቅጣቶች ሊተላለፉ ይገባል ብለዋል።
“ከሦስቱ እርምጃዎች (ጨዋታ ከማስቆም፣ ጨዋታው በድጋሚ ከማስቆም እና ጨዋታው ከማቋረጥ) በተጨማሪ የዘረኝነት ጥቃት ምክንያት የሆነው ቡድን ‘ፎርፌ’ እንዲሰጥበት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የስታዲየም እግድ መጣል እና በዘረኞች ላይ ደግሞ የወንጀል ክስ መመስረት አለብን" ብለዋል።
"ፊፋ እና እግር ኳስ ለዘረኝነት እና ለማንኛውም ዓይነት መድልዎ ተጠቂዎች ሙሉ በሙሉ አጋርነታቸውን ያሳያሉ። ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘረኝነት ይቁም! ምንም ዓይነት መድልዎ ይቁም!”
"ቅዳሜ በዩዲኒዜ እና ሼፊልድ የተፈጠሩት ድርጊቶች ፍጹም አጸያፊ እና ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው። በቅዳሜው ክስተቶች ጥቃት ለደረሰባቸው ተጫዋቾች ሙሉ ድጋፍ አለኝ።” ብለዋል ኢንፋንቲኖ።
ፈረንሳዊው ግብ ጠባቂ ማግናን በስታዲዮ ፍሪዩሊ ደጋፊዎች የዝንጀሮ ድምጽ መስማቱን ከገለጸ በኋላ የኤሲ ሚላን ተጫዋቾች ከሜዳው ወጥተዋል። ተጫዋቾቹ በመጨረሻ ተመልሰው ተጫውተው ሚላን 3 ለ 2 አሸንፏል።
የ28 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ለሚላን ቴሌቭዥን "ይህ በእግር ኳስ ዓለም ውስጥ መኖር የለበትም። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ለብዙ ዓመታት የታየ ድግግሞሽ ነው" በማለት ተናግሯል።
"ሁሉም ካሜራዎች በተገኙበት እና ማዕቀብ በሚጣልበት ወቅት ነገሮችን ለመለወጥ አንድ ነገር መደረግ አለበት።”
"ምላሽ መስጠት አለብን። አንድ ነገር ማድረግ አለብን ካልሆነ እንደዚህ መጫወት አንችልም።”
የሚላን እና የከተማ ተቀናቃኙ ኢንተር በይፋ ማይገናን ደግፈዋል። ሴሪ አው "ሁሉንም ዓይነት ዘረኝነት ያወግዛል" ብሏል።
ፈረንሳዊ አጥቂ ክሊያን ምባፔ ደግሞ "በቃ" ብሏል።
የቀድሞ የእንግሊዝ እና የአርሰናል አጥቂ ኢያን ራይት በሚላን በኩል ያለውን “አንድነት” አድንቆ ቡድኖቹ የሚደርስባቸውን ጥቃት ሲሰሙ “ከሜዳ እንዲወጡ” እና ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል።

የፎቶው ባለመብት, Rex Features
በእንግሊዝ ሻምፒየንሺፕ ከፓልመር ጋር የተያያዘው ክስተት የተፈጠረው ኮቨንተሪ ሼፊልድ ዩናይትድን 2 ለ 1 ባሸነፈበት ወቅት ነው። ጨዋታው ለበርካታ ደቂቃዎች እንዲቆም ተድርጎ የጨዋታው ዳኞች ሁለቱንም አሰልጣኞች ሲያነጋግሩ ታይተዋል።
የደቡብ ዮርክሻየር ፖሊስ ምርመራ የጀመረ ሲሆን "ሁኔታዎቹን ለመረዳት እና የተሳተፉትን ለመለየት ከክለቦች እና ከዌስት ሚድላንድስ ፖሊስ ጋር በጋራ እንሠራለን" ብሏል።
ሼፊልድ ማንኛውም ሰው "ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ጠንካራ የሆኑ እገዳዎች" እንደሚጠብቁት አረጋግጧል።
ፓልመር ግን ሁኔታዎች ይለወጣሉ ብሎ ለማመን ጥርጣሬ እንዳደረበት ተናግሯል። ኤክስ ላይም “ዘረኝነት አሳፋሪ ነው... እኔ ጥቁር እና ኩሩ ነኝ ሦስት ልጆቼንም እንደዚሁ እያሳደግኳቸው ነው" ብሏል።
"[አንድ] ሁለት ደጋፊዎች የዝንጀሮ ድምጽ ማሰማታቸው ሁሉንም ደጋፊዎች አይገልጹም። ስለሰጣችሁኝ ፍቅር እና ድጋፍ ሁሉ አደንቃለሁ።”
ጸረ መድሎ ላይ የሚሠራው ኪክ ኢት አውት የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት ለፓልመር እና ማይግናን ድጋፉን ሰጥቷል።
"ተጠያቂዎችን መቅጣት የባለሥልጣናት እና ክለቦች ጉዳይ ነው። ክለቦች ይህ እንዳይሆን መከላከል ካልቻሉ እነሱም ቅጣት ሊገጥማቸው ይገባል" ብሏል በመግለጫው።
"በፊፋ እንደተገለጸው ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ቅጣት እንጠብቃለን።” ብሏል።












