ሩሲያ ኃይሏን ለማሳየት የላከቻቸው የጦር መርከቦች ከአሜሪካ አቅራቢያ ወደምትገኛው ኩባ ደረሱ

በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከምዕራቡ ዓለም ጋር ውጥረት ውስጥ የገባችው ሩሲያ በኑክሌር ኃይል የሚንቀሳቀስ የባሕር ሰርጓጅን ጨምሮ አራት መርከቦቿ ኩባ ደርሰዋል።

መርከቦቹ ከዩናይትድ ስቴትሷ ፍሎሪዳ ግዛት 145 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለው ሃቫና ቤይ የባሕር ዳርቻ ላይ መልህቃቸውን ጥለዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ከሆነ አድሚራል ጎርሽኮቭ የተባለው ሰርጓጅ መርከብ እና ካዛን የጦር መርከቦች ዚርኮን የተሰኘውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ጨምሮ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ተሸካሚዎች ናቸው። መርከቦቹ ቀደም ሲል በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚሳኤል ልምምዶችን አከናውነዋል።

የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ መርከቦቹ የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳልያዙ እና ለአምስት ቀናት የሚቆየው ጉብኝታቸው በአካባቢው ስጋት እንደማይፈጥር ተናግሯል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጉብኝቱን በቅርበት እየተከታተልነው ነው ብለዋል።

የአሜሪካ የባሕር ኃይል የሩሲያ መርከቦች ወደ ኩባ መቃረባቸውን ተከትሎ የባሕር ላይ ድሮኖችን በመጠቀም ጉብኝቱን ለመሸፈን መሞከራቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል።

የሩሲያ መርከቦች ማለዳ ላይ ወደ ሃቫና ቤይ ሲደርሱ በአነስተኛ መርከቦች ከመታጀባቸውም በላይ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ የመርከቦቹ ሠራተኞች እንዲያርፉ እና ከአካባቢው መስህቦች ጋር እንዲተዋወቁ እንጂ ጉብኝቱ ይፋዊ አይደለም ብሏል።

ሩሲያ ከዚህ ቀደም የጦር መርከቦቿን ወደ ኩባ በተደጋጋሚ የላከች ሲሆን፣ ሁለቱ አገራት ለረዥም ጊዜ የቆየ አጋርነት አላቸው። የአሁኑ ልምምድ ከዚህ ቀደሞቹ ይለያል ተብሏል።

እአአ በ2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ባካሄደችው ወረራ ምክንያት ከአሜሪካ ጋር ያላት ፍጥጫ እየጨመረ በመጣበት ወቅት መሆኑ፣ ሞስኮ ይህን እርምጃ የወሰደችው ፍርሃት ለማንገስ ያደረገችው ነው ተብሎ ተተርጉሟል።

አሜሪካ በጎረቤቷ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ነው ብለው ስለሚያስቡት ከክሬምሊን ወደ ዋሽንግተን የተላለፈ ግልጽ መልዕክትም ይመስላል።

ጉብኝቱ ለኩባ መንግሥት እና የሶሻሊስት አጋሯ ቬንዙዌላ ወሳኝ የድጋፍ ምልክት ነው ተብሏል። የጦር መርከቦቹ በሃቫና የሚኖራቸውን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ቬንዙዌላ ሊያቀኑ ይችላሉ።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጉብኝቱን እንደሚያውቁ ጠቁመው፣ ለአሜሪካ ስጋት እንደሆነ አድርገው እንደማይቆጥሩት ጠቁመዋል። ባላቸው መረጃ መሠረት በኑክሌር ኃይል የሚንቀሳቀሰው የባሕር ሰርጓጅ መርከብ የኑክሌር ጦር መሳሪያ አለመያዙንም ገልጸዋል።