ማንቸስተር ዩናይትድ ሲሸነፍ ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ ጣለ

 ኖቲንግሃም ፎረስት ከ30 ዓመት በኋላ ኦልድትራፎርድ ላይ አሸንፏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው በኖቲንግሃም ፎረስት ሲሸነፍ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ነጥብ ለመጋራት ተገዷል።

በቅርቡ ማንቸስተር ዩናይትድን ማሠልጠን የጀመረው ሩበን አሞሪም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፏል።

አሠልጣኙ ከፊቱ ከባድ ሥራ እንደሚጠብቀው የሚያሳይ ውጤት ነው ተብሏል።

ኒኮላ ሚሌንኮቪች ለፎረስት በግንባሩ ገጭቶ ግብ ሲያስቆጥር ራስመስ ሆይሉንድ ለማንቸስተር ዩናይትድ ኳስ እና መረብ አገናኝቷል። በዚህም ሁለቱ ቡድኖች በአቻ ውጤት ለእረፍት ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና ስህተት ፎረስት በሞርጋን ጊብስ-ዋይት በድጋሚ መምራት ቻለ።

ከደቂቃዎች በኋላ እንግዳው ቡድን ሦስተኛ ግብ ሲያስቆጥር ማንቸስተር እንድ ግብ አክሏል። ግቡን ዘንድሮ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ክሪስ ዉድ አስቆጥሯል። ለማንቸስተር ደግሞ አምበሉ ቡርኖ ፈርናንዴስ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

በዚህም ጨዋታው 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

አሞሪም ከ2023 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳቸው ሽንፈት አስተናግደዋል።

"ይሄ ረዥም ጉዞ ነው . . . በአንዳንድ አካባቢዎች መሻሻሎችን አሳይተናል" ሲሉ ከጨዋታው በኋላ ተናግረዋል።

በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ማንቸስትር ሲቲ በሳምንቱ አጋማሽ ማሸነፍ ቢችልም በድጋሚ ነጥብ ለመጣል ተገዷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከክሪስታል ፓላስ ጋር በነበረው ጨዋታ 2 አቻ በመለያየት ለዋንጫ የሚያደርገው ጉዞ ሌላ እንቅፋት ገጥሞታል።

ውጤቱን ይበልጥ አሳሳቢ ያደረገው ደግሞ ፓላስ ሁለት ጊዜ መምራት መቻሉ ነው።

ሲቲ በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አንድ ጨዋታው ከሚቀረው እና ሊጉን ከሚመራው ሊቨርፑል ከወዲሁ በስምንት ነጥብ ርቋል።

ሲቲ ሦስት ነጥብ ማግኘት ቢችል ደረጃውን የሚያሻሽልበት ዕድል ይኖረው ነበር።

ፓላስ በዳንኤል ሙኖዝ ግብ ሲመራ ኧርሊንግ ሃላንድ ሲቲን አቻ ማድረግ ችሏል።

በ56ኛው ደቂቃ ማክሲንስ ላክሮክስ ፓላስን በድጋሚ ወደ መሪነት ቢመልስም ሪኮ ዊሊያምስ ሲቲ በድጋሚ አቻ አደረገ።

ዊሊያምስ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ በ84ኛው ደቂቃ ከሜዳ ተባሯል።

"በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ቡድኔን እወደዋለሁ። ቡድኑ ውስጥ በርካታ ችግሮች አሉብን። የምንችለውን ያህል ታግለን አንድ ነጥብ አግኝተናል። ዘንድሮ በእያንዳንዱ ጨዋታ ነጥብ በመሰብሰብ መጓዝ አለብን" ሲል አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ተናግሯል።

በስምንት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ሁለት ጨዋታዎችን በተከታታይ በማሸንፍ ከማንቸስትር ሲቲ በሁለት ነጥብ ብቻ ርቆ ለመቀመጥ ችሏል።

ጆን ዱራን በ24ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ቡድኑ ሳውዝሃምፕተንን ለማሸነፍ ችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኒውካስል ከሜዳው ውጪ በብሬንትፎርድ 4 ለ2 ተሸንፏል።

ብሪያን ምቡሞ ብሬንትፎርድን ቀዳሚ ሲያድርግ አሌክሳንደር አይዛክ ኒውከሳልን አቻ ለማድረግ ችሏል።

ዮአን ዊሳ ቡድኑን ወደ መሪነት ቢመልስም ሃርቪ ባርነስ በድጋሚ ኒውካስልን አቻ አድርጓል።

ናታን ኮሊንስ እና ኬቪን ሼድ በተከታታይ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ብሬንትፎርድን አሸናፊ አድርገዋል።

በመርሲ ሳይድ ደርቢ ኤቨርተን እና ሊቨርፑል እንዲያከናውኑት ቀጠሮ የተያዘለት ጨዋታ በአየር ንብረት ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላለፏል።