ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፓኪስታን በኒውክሌር ጦር መሳሪያዋ ላይ የሚወስኑትን ከፍተኛ ባለሥልጣኖቿን ለስብሰባ ጠራች
ፓኪስታን በሕንድ የአየር መከላከያ ሥርዓት ላይ ጥቃት መፈጸሟን ካሳወቀች በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሯ የአገሪቱን ከፍተኛውን ወታደራዊ ውሳኔ የሚያሳልፈውን ቡድን ለስብሰባ ጠሩ።
ፓኪስታን ከሰዓታት በፊት እንዳስታወቀችው በተለያዩ የሕንድ ይዞታዎች ውስጥ የሚገኙ የአየር ኃይል ሰፈሮች ላይ እና የአየር ጥቃት መከላከያ ሥርዓት ላይ ጥቃት ፈጽማለች። በተጨማሪም የከባድ መሳሪያ መተኮሻዎች እና ማከማቻዎች መመታታቸውን የፓኪስታን ወታደራዊ ኃይል አስታውቋል።
ከቀናት በፊት ሕንድ በፓኪስታን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ሁለቱም አገራት የአጸፋ የአየር እና የሚሳዔል ጥቃቶች እየፈጸሙ መሆናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ዛሬ [ቅዳሜ] ማለዳ ሕንድ እና ፖኪስታን በሚዋሰኑበት የካሽሚር አካባቢዎች ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘገባዎች ያመለከቱ ሲሆን፣ የቢቢሲ ዘጋቢዎች ሕንድ በምታስተዳድረው ካሽሚር ውስጥ በሚገኙ ሁለት ከተሞች ፍንዳታዎች መሰማታቸውን አረጋግጠዋል።
ሌሎች መገናኛ ብዙኃንም ፓኪስታን ጥቃት ፈጸምኩባቸው ያለቻቸው የሕንድ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች በሚገኙባቸው የካሽሚር ክፍሎች ውስጥ የፍንዳታ መሰማታቸውን ዘግበዋል።
የሕንድ ጦር ሠራዊትም ፓኪስታን ድሮኖችን እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም በምዕራባዊ የሕንድ ድንበር አካባቢ ጥቃት መፈጸሟ "አደገኛ ሁኔታን የሚያስከትል ነው" ሲል አስጠንቅቋል።
የፓኪስታን ጦር በበኩሉ በሕንድ ይዞታዎች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ሕንድ በአየር ኃይል ሰፈሮቹ ላይ ለፈጸመችው የሚሳዔል ጥቃት አጸፋ መሁኑን ቢገልጽም፤ ሕንድ ግን ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ያለችው ነገር የለም።
ለዘመናት በፍጥጫ ውስጥ የቆዩት ሕንድ እና ፓኪስታን ኒውክሌየርን ጨምሮ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን የታጠቁ ሠራዊቶች ያሏቸው ሲሆን፣ ግጭቱ ተባብሶ ወደ ለየለት ጦርነት እንዳይገቡ ስጋት ተፈጥሯል።
ዛሬ ቅዳሜ ማለዳ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የፖኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሸሪፍ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ በአገሪቱ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚሰጠውን 'የብሔራዊ ዕዝ ባለሥልጣንን' ለስብሰባ ጠርተዋል።
ይህ ባለሥልጣን ከፍተኛ የሲቪል እና ወታደራዊ ባለሥልጣናትን ያካተተ ሲሆን ፓኪስታን ያሏትን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች በተመለከተ እና በሌሎች ወሳኝ የአገሪቱ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ በመምከር ለሠራዊቱ ትዕዛዝ የሚያስተላለፍ አካል ነው።እና
በሕንድ እና ፖኪስታን መካከል ያለው ውጥረት የተባባሰው ከሁለት ሳምንት በፊት ሕንድ በምትቆጣጠረው የካሽሚር ክፍል ውስጥ ከ20 በላይ ቱሪስቶች በታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ ሕንድ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ የበቀል ጥቃት በፓኪስትን ይዞታዎች ላይ መውሰድ ስትጀምር ነው።
ባለፉት ቀናት ሁለቱም አገራት አንዳቸው ሌላኛውን በድሮን እና በከባድ መሳሪያ ጥቃት በመፈጸም ሲከሱ የቆዩ ሲሆን እስካሁን ከሁለቱም ወገን ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸው እየተዘገበ ነው።
በሁለቱ ኒውክሌር ታጣቂ አገራት መካከል ባለፉት ቀናት እየተባባሰ ያለው ግጭት እንዲረግብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የተለያዩ አገራት መሪዎች ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለፓኪስታን ጦር ሠራዊት እና ለሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስልክ በመደወል መወያየታቸውን እና አገራቱ ውጥረቱን እንዲያረግቡ መጠየቃቸውን መሥሪያ ቤታቸው አስታውቋል።
ሩቢዮ በአገራቱ መካከል ተጨማሪ ግጭቶች እንዳይፈጸሙ የሚያስችል "ገንቢ ንግግር" እንዲያደርጉ አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ እንደምትፈልግ አሳውቀዋል።