የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሥልጣን፣ ደመወዝ፣ እና ጥቅማ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት የሚፎካከሩት የቀድሞው የማዳጋስካር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድራያማንድራቶ (በስተግራ)፣ የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ (መሀል)፣ የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሐሙድ አሊ ዩሱፍ (በስተቀኝ)
የምስሉ መግለጫ, ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት የሚፎካከሩት የቀድሞው የማዳጋስካር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድራያማንድራቶ (በስተግራ)፣ የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ (መሀል)፣ የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሐሙድ አሊ ዩሱፍ (በስተቀኝ)

ሙሳ ፋኪ መሐማት የሁለት ዙር የሥልጣን ዘመናቸው ተጠናቅቆ ቦታቸውን ለአዲስ ሊቀመንበር ለማስረከብ ዛሬ ምርጫ ይካሄዳል።

የሥልጣን ዘመናቸው ያበቃውን ሙሳ ፋኪ ማሐማትን ለመተካት የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ፣ የጂቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የቀድሞው የማዳጋስካር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድራያማንድራቶ ይፎካከራሉ።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ አንድ ሰው በሥልጣን ላይ መቆየት የሚችለው ለሁለት የሊቀመንበርነት ዘመን ለስምንት ዓመታት ብቻ ነው።

የሊቀመንበር ምርጫው በምሥጢር ድምፅ በመስጠት የሚከናወን ሲሆን፣ አሸናፊ የሚሆነው ግለሰብ ከ50 አባል አገራት መካከል የ36 አገራትን ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን መቀመጫው የኅብረቱ ጽህፈት ቤት ሲሆን፣ የኅብረቱን የዕለት ተዕለት ሥራዎችን ይመራል ይቆጣጠራል።

የተመራጩ ሊቀመንበር ኃላፊነት ምንድን ነው?

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ከዋና ፀሐፊነት ባሻገር፣ የኅብረቱ ሕጋዊ ወኪል ሲሆን፣ የኅብረቱ ዓመታዊ በጀትን በበላይነት ይመራል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንን በሊቀመንበርነት ዋናው ኃላፊነትን የሚረከበው ግለሰብ፣ የአፍሪካ ኅብረት አስተዳዳሪ እና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን ያገለግላል።

ሊቀመንበሩ በቢሊዮኖች የሚቆጠረውን የኅብረቱን በጀት ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን የማስተዳደር ኃላፊነትም ከሥራ ድርሻዎቹ መካከል ይገኝበታል።

በዲፕሎማሲው መስክ ደግሞ ሊቀመንበሩ የአፍሪካ ኅብረትን ዓላማዎች እና ፍላጎቶች በዓለም አቀፍ መድረክ ይዞ ከፊት የመገኘት ሥልጣን ተሰጥቶታል።

ስለዚህ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ በተለያዩ አህጉራዊ ጉዳዮች ማለትም የአሜሪካ-አፍሪካ ጉባኤ፣ የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ እና ሌሎችም አህጉራዊውን ተቋም በሚመለከቱ ጉባኤዎች ላይ መገኘት ይጠበቅበታል።

ከዚህም ባሻገር ተመራጩ ሊቀመንበር አህጉራዊ አጀንዳዎችን በበላይነት ይመራል። በኮሚሽኑ ውስጥ የሚሾሙ ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ባለሥልጣናትን የመመደብ ሥልጣን አለው።

የሚመረጠው ሊቀመንበር የአፍሪካ ኅብረት የፈጸማቸውን ስምምነቶች እና ሕጎች ተቀብሎ ማስፈፀምም ይጠበቅበታል።

ሊቀመንበሩ የአፍሪካ ኅብረት አካላት የሚያካሄዷቸው ስብሰባዎች ከኅብረቱ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶች ጋር ተጣጥመው መሄዳቸውን ያረጋግጣል።

ሌሎች የሊቀመንበሩ ሥልጣን ደግሞ ከአባል አገራት መንግሥታት፣ ከሌሎች ተቋማት እና ከክልላዊ ኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች ጋር በአፍሪካ ኅብረት እንቅስቃሴዎች ላይ ማማከር እና ማስተባበር እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረትን ዲፕሎማሲያዊ ውክልና መፈፀምን ያካትታሉ።

ይኹን እንጂ ሊቀመንበሩ ለአገራት ርዕሰ ብሔሮች ተጠሪ ነው። ስለዚህ ለኅብረቱ እና ለአህጉሪቱ ውሳኔ እንዲሰጡ የሚያግዙ ሪፖርቶችን ማዘጋጀት ከሥራ ድርሻዎቹ መካከል አንዱ ነው።

የጂቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሐሙድ አሊ ዩሱፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጂቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሐሙድ አሊ ዩሱፍ

ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም

የአህጉራዊው ድርጅት ሊቀመንበር ኃላፈነቱን ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ የአፍሪካ ኅብረት ዋነኛው ዲፕሎማት በመሆን በአባል አገራት፣ በዓለም አገራት እንዲሁም በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት የተለያ ተሰሚነት እና ቦታን ያገኛል።

ኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር መቀመጫው አዲስ አበባ ሲሆን፣ በኃላፊነቱ ከሚያገኘው ስም እና ዝና ባሻገር ለሚያከናውነው ተግባር ለእራሱ እና ለቤተሰቦቹ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን ከኅብረቱ ያገኛል።

የኅብረቱ ሊቀመንበር በወር ከ15 ሺህ 500 የአሜሪካ ዶላር በላይ ደሞዝ የሚያገኝ ሲሆን፣ ልጅ ካለ በእያንዳንዱ ልጅ ስም የ250 ዶላር ድጎማ፣ በተጨማሪ ለቤት ኪራይ፣ ለመብራት እና ለውሃ የሚውል በየወሩ 6000 ዶላር ተመድቦለታል።

እንዲሁም የኅብረቱ ሊቀመንበር ልጆች በአፍሪካ ውስጥ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ከሆነ የትምህርት ወጪያቸው ሙሉ ለሙሉ ይሸፈንላቸዋል። ከአውሮፓ እና ከሰሜን አሜሪካ ውጪ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ከሆነ ሙሉ በሙሉ ወጪያቸው እንደሚሸፈን የኅብረቱ መተዳደሪያ ደንብ ያሳያል።

የሊቀመንበሩ ልጆች በአውሮፓው ወይም በሰሜን አሜሪካ የሚማሩ ከሆነ ለእያንዳንዳቸው የትምህርት ወጪያቸውን የሚሸፍን 15 ሺህ ዶላር ክፍያ በዓመት ያገኛሉ። በተጨማሪም ከአህጉሪቱ ውጪ ለሚኖሩት ልጆች ለቤት ኪራይ ስድስት ሺህ ብር ድጎማ አላቸው።

ዕጩ ተፎካካሪዎቹ ምን ለመሥራት ቃል ገቡ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኬንያዊው ራይላ ኦዲንጋ፣ ጂቡቲያዊው ማሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የማዳካስካሩ እጩ ሪቻርድ ራንድራያማንድራቶ የኮሚሽነርነቱ ሥልጣን ቢሰጣቸው ምን መሥራት እንደሚፈልጉ በዝርዝር በምረጡኝ ዘመቻዎቻቸው ወቅት ተናግረዋል።

ከዕጩዎቹ ቅስቀሳ ለመረዳት እንደሚቻለው የኮሚሽነርነት ሥልጣንን ቢያገኙ በአህጉሪቱ ሰላም እና መረጋጋትን ማምጣት፣ ጠንካራ ተቋም መገንባት እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ይሠራሉ።

ኦዲንጋ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ቢመረጡ አህጉራዊ ውህደት፣ መረጋጋት እና ደኅንነት እንዲኖር እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

የጂቡቲው ዕጩ ማሐሙድ አሊ ዩሱፍ እንዲሁ ሰላም እና ደኅንነት ላይ እንደሚያተኩሩ፣ የኢኮኖሚ እና የመሠረተ ልማት ዕድገት ላይ እንደሚሠሩ በተጨማሪም ተቋማዊ አቅምን ማሳደግ ላይ እንደሚያተኩሩ ገልጸዋል።

የማዳጋስካሩ ዕጩ ሪቻርድ ራንድራያማንድራቶ ደግሞ ዋነኛ ትኩረታቸው የአፍሪካ የፖለቲካ እና የደኅንነት ጉዳዮችን መፍታት እንደሆነ ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ቁልፉ መሠረታዊ ያለመረጋጋት ምንጮችን መፍታት እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ነው የሚሉት ኦዲንጋ ይህን ለማሳካት ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የጂቡቲው ዕጩ ተፎካካሪ በበኩላቸው የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲዎችን ማበረታታት፣ አፍሪካን በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ ማድረግ፣ የአፍሪካ የትምህርት ፖሊሲን መደገፍ ትኩረታቸው እንደሆነ አስታውቀዋል።

በተለይ ደግሞ የወጣት አህጉር በሆነችው አፍሪካ ከሥራ ፈጠራ ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎች ላይ መሥራትን አሳካቸዋለሁ ካሏቸው ነጥቦች መካከል ናቸው።

ራይላም የዘላቂ እና ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲኖር እንደሚሠሩ ያነሱ ሲሆን፣ አፍሪካውያን የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥን ማሳደግ እና የመሠረተ ልማት ዕድገትን ማፋጠን እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።

አፍሪካ በፋይናንስ ራሷን ወደ መቻል እንድትመጣ የግሉ ዘርፍ ሚና እንዲጎላ እና ኅብረቱ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርግ ፍላጎታቸው መሆኑን በፕሮግራማቸው አሳውቀዋል።

የፆታ እኩልነት እና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንም ከትኩረት መስኮቻቸው መካከል መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።

የማዳጋስካሩ ዕጩ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ደግሞ ሪቻርድ ራንድራያማንድራቶ ኅብረቱ ከሌሎች ጥምረቶች እና ትስስሮች እንዲሁም አቻ ተቋማት ጋር በሚኖረው ግንኙነት ሁሉ የአፍሪካን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሠሩም ገለጸዋል።

የአፍሪካ የሰው ኃይል ዘመኑ የሚጠይቀው እንዲሆን ለማድረግ የሚሠሩ ሥራዎችን ለመደገፍ እና አህጉራዊ ውህደትን የሚያፋጥኑ ተግባራትን እንደሚያከናውኑም ዕቅዳቸውን አሳውቀዋል።