ሩሲያ በቀይ ባሕር ላይ የጦር ሰፈር ለመመሥረት ከሱዳን ጋር ተስማማች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሱዳን ሩሲያ በቀይ ባሕር ላይ የጦር ሰፈር መመሥረት የሚያስችላትን የመጨረሻውን ስምምነት ከሩሲያ ጋር መፈራረሟን አሳወቀች።
ስምምነቱ መጀመሪያ ላይ የተደረገው ከሥልጣን ከተወገዱት ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አል በሺር ጋር ሲሆን፣ በኋላ ላይ የአገሪቱን መንበር የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግሥት ጉዳዩን እየተመለከተው መሆን ተናግሮ ነበር።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ የሱፍ ረቡዕ ዕለት ከሩሲያ ጋር የባሕር ኃይል የጦር ሰፈር ምሥረታ ላይ "ሙሉ ስምምነት" ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
የቀረው ስምምነቱን ማፅደቅ ብቻ ነው ብሏል።
አሜሪካ፣ ቻይና እና ፈረንሳይ ወሳኝ የንግድ መስመር በሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የጦር ሰፈር አላቸው።
ዩሱፍ ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ሞስኮ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "ሱዳን እና ሩሲያ የሩሲያን የባሕር ኃይል ጦር ሰፈርን በሚመለከት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፤. . . ጉዳዩ በጣም ቀላል ነው… በሁሉም ነገር ተስማምተናል" ሲሉ ተናግረዋል።
በመግለጫው ወቅት ምንም ተጨማሪ ነገሮች ያልቀረቡ ሲሆን፣ ላቭሮቭም በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የሁለቱ አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2019 በአል በሽር አስተዳደር ወቅት በጉዳዩ ላይ ንግግር የጀመሩ ሲሆን፣ ወታደራዊ አመራሮች ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላ በኅዳር 2020 የመጀመሪያ ፊርማቸውን አኑረዋል።
ነገር ግን በ2023 ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የስምምነቱ ዕጣ ፈንታ ሳይወሰን ቆይቷል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉበት የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የጀመረው ሠራዊቱ እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ከገቡ በኋላ ነው።
ሞስኮ ለዓመታት በፖርት ሱዳን አቅራቢያ የጦር ሰፈር ለማቋቋም ስትፈልግ ቆይታለች።
ለ25 ዓመታት የሚቆየው የወደብ ስምምነት፣ሩሲያ የባሕር ኃይል ሎጂስቲክስ ማዕከል እንድትመሠርት፣ እስከ 300 የሚደርሱ ሠራተኞችን የሚይዙ የጦር መርከቦች፣ በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ለማስፈር ያለመ ነው።
ቀይ ባሕር ለዓለም አቀፍ ንግድ፣ ለመከላከያ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ወሳኝ ስትራቴጂካዊ መስመር ነው።
በሶሪያ ያለውን ወታደራዊ ይዞታዋን የማጣት ስጋት የተደቀነባት ሩሲያ በፖርት ሱዳን የጦር ሰፈር የመገንባት ፍላጎቷ እያደገ መምጣቱ ተነግሯል።
የሶሪያ አዲሱ መንግሥት ሩሲያ ከአገሪቱ ጋር ገብታ የነበረውን የረዥም ዓመት ሊዝ ካቋረጠ በኋላ ከአገሯ ውጪ የሚገኘውን ብቸኛውን የባሕር ኃይል ሰፈሯን ለመዝጋት ተገድዳለች።
ከቅርብ ወራት ወዲህ የሩሲያ ባለሥልጣናት በጦርነቱ ወቅት የሱዳን ዋና ከተማ በመሆን እያገለገለ የሚገኘውን ፖርት ሱዳንን የጎበኙ ሲሆን፣ በእርስ በርስ ጦርነት ከሚሳተፉ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ሲሞክሩ ቆይተዋል።
ሩሲያ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ወታደራዊ የትብብር ስምምነቶችን በመፈራረም እና የምዕራባውያን አገሮችን በማስወጣት ተጽእኖዋን እያሰፋች ትገኛለች።












