የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ሰልፍ እንዳያደርግ መከልከሉን ገለጸ

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለማክበር የያዘው ፕሮግራም ክልከላ ስለገጠመው መሰረዙን አስታወቀ።
ኮንፌዴሬሽኑ በየዓመቱ ሚያዝያ 23 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሠራተኞች በዓልን በአዲስ አበባ እና ቅርንጫፎቹ በሚገኙባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ለማክበር ዕቅድ እንደነበረው ገልጿል።
ነገር ግን ዝግጅቱ በከተማው ባለሥልጣናት መከልከሉን ኮንፌዴሬሽኑ የገለጸ ሲሆን፣ ፖሊስም በአዲስ አበባ ውስጥ በዕለቱ የሚካሄድ የሚያውቀው ሰልፍም ሆነ ስብሰባ የለም ብሏል።
48ኛውን ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን - ሜይ ዴይን ምላሽ የሚፈልጉ የአገሪቱ ሠራተኞች ጥያቄዎችን ናቸው ያላቸውን በመያዝ ለማክበር አቅዶ ነበር።
ለዚህም የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን በዓሉን ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ እንደነበር አመልክቶ፣ ነገር ግን ለዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 23/2015 ዓ.ም. መስቀል አደባባይ ላይ ይካሄዳል የተባለው ክብረ በዓል መሰረዙን ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የፀጥታ ቢሮ “ስለከለከለን መረሃ ግብሩን ለመሰረዝ ተገደናል” ሲል የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽኑ አስወታውቋል።
ኮንፌዴሬሽኑ በዋናነት ለሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግ፣ ዝቅተኛው የሠራተኞች ደመወዝ ወለል እንዲሻሻል እና እንዲወሰን የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን በዓል ዝግጅት ላይ በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ አቅዶ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስም ዓለም አቀፉን የሠራተኞች ቀንን አስመልክቶ የከተማው ፖሊስም ሆነ የአስተዳደር አካላት የሚያውቁት ምንም ዓይነት ስብሰባ አለመኖሩን አስታውቋል።
ስለዚህም በከተማዋ ውስጥ ሰኞ ሚያዝያ 23/2015 ዓ.ም. “ምንም አይነት የአደባባይ ኩነት ወይም ሰልፍ አለመኖሩ” ያሳወቀ ሲሆን፣ “ሕግን የማስከበር ተግባሩንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል” አሳስቧል።
ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን - ሜይ ዴይ በየዓመቱ ሚያዝያ 23 በአውሮፓውያኑ ሜይ 1 በዓለም ዙሪያ የሠራተኞችን የመብት ጥያቄዎችን በማንሳት በሰልፎች እና በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
ዕለቱም በዓለም ዙሪያ ባሉ ከ80 በላይ በሚሆኑ አገራት ውስጥ ብሔራዊ በዓል ሆኖ የሚከበር ሲሆን፣ መደበኛ ሥራም ዝግ ይሆናል።












