አዲሱ የአል ቃኢዳ ‘መሪ’ ሳይፍ አል አድል ማነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአል ቃኢዳ መሪ አይማን አል ዛዋሂሪ በአሜሪካ መገደሉን ተከትሎ በቀጣይ አል ቃኢዳን ማን ይመራል? የሚለው እያነጋገረ ይገኛል።
አል ዛዋሂሪ አፍጋኒስታን፣ ካቡል ውስጥ በሰው አልባ አውሮፕላን አማካይነት መገደሉ አይዘነጋም።
በአሸባሪነት የተፈረጀውን አል ቃኢዳ ሊመራ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው ትውልደ ግብፃዊው ሳይፍ አል አድል ነው።
የአል ዛዋሂሪ ምክትሎችና ከአል ቃኢዳ ዋነኛ አምስት መሥራቾች መካከል በሕይወት የቀረው አል አደል ብቻ ነው።
አል ዛዋሂሪን ይተካል ተብሎም ይጠበቃል።
አል አደል የአል ቃኢዳ መሪ የሚሆነው በቀላሉ አይደለም።
አል አድል አሁን በኢራን በተገደበ ሁኔታ እየኖረ እንደሆነ ጥርጠሬ አለ።
አል አድል ማነው?
ከአል ቃኢዳ መሥራቾች አንዱና የኦሳማ ቢን ላደን ታማኝ ተከታይ ነው።
ምሥጢራዊ ኑሮ የሚገፋው ይህ ግለሰብ፣ ገናና ከሆኑ ጂሀዲስቶች መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳል።
እአአ በነሐሴ 1998 በታንዛኒያ እና በኬንያ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ በተከታታይ ከደረሱ የቦንብ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ይወነጀላል።
በእነዚህ ጥቃቶች ሳቢያም 220 ሰዎች ተገድለዋል።
በሌላ በኩል ከ20 ዓመታት በፊት በኒው ዮርክ እና በዋሽንግተን የተፈጸሙትን የመስከረም 11 ጥቃቶችን በመቃወም ስሙ ይነሳል።
በ2021 የወጣ ሰነድ እንደሚጠቁመው፣ አል አድልን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የአል ቃኢዳ አመራሮች አሜሪካ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘር አሜሪካን እጅጉን ያስቆጣል ሲሉ ተከራክረው ነበር።
ዌስት ፖይንት በተባለው የአሜሪካ ወታደራዊ አካዳሚ አጥኚዎች የተዘጋጀ አንድ ሰነድ እንደሚለው፣ እነዚህ አመራሮች አሜሪካ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት አሜሪካ በምላሹ አፍጋኒስታንን እንድትወር ምክንያት ይሆናል ብለው ነበር።
አፍጋኒስታን በወቅቱ ለአል ቃኢዳ ኦፕሬሽኖች ምቹ አገር ነበረች።
አል አድል ከዚህ ቀደም ስለ ደኅንነት፣ ስለላ፣ ውጊያ እና አብዮት በሰፊው ጽፏል።
ስለ አል አድል ምን እናውቃለን?
አል አድል አል ቃኢዳን ከመቀላቀሉ በፊት ስለነበረው ሕይወት እምብዛም መረጃ የለም።
ኤፍቢአይ እንደሚለው፣ አል አድል የተወለደው እአአ በ1963 ወይም ከዚያ ሦስት ዓመታት ቀድሞ ነው።
ግለሰቡ አል ቃኢዳ ውስጥ ጉልህ ቦታ ቢኖረውም፣ በብዛት በአል ቃኢዳ ፕሮፓጋንዳ ውስጥ ስሙ አይነሳም።
ብዙም ይፋዊ መረጃዎች ስለ አል አድል አይገኙም።
ስለ ትክክለኛ ማንነቱም ግልጽ አይደለም።
ሳይፍ አል አድል የሚለው ስም አል ቃኢዳን ከተቀላቀለ በኋላ የሚጠራበት የጂሃድ ስያሜው እንደሆነ ይገመታል።
ሳይፍ አል አድል የአረብኛ ትርጉሙ 'የፍትሕ ጎራዴ' ነው።
የዌስት ፖይንት አጥኚዎች እንደሚሉት፣ አል አድል ብዙውን ጊዜ መሐመድ ኢብራሂም ማካዊ ከሚባለው የቀድሞ የግብፅ ልዩ ኃይል ኮሎኔል ጋር ይምታታል።
በ1980ዎቹ አፍጋኒስታንን ከሶቪየት ኅብረት ለመከላከል በተደረገው ውጊያ ከቢን ላደን ጎን ተሰልፏል።
አል ቃኢዳም የተመሠረተው በዚህ ወቅት ነበር።
አል አድል ኋላ ላይ ኑሮውን በሶማሊያ አደረገ።
በሶማሊያ የእርስ በእርስ ጦርነት አሜሪካውያን ወታደሮችን የሚዋጉ ታጣቂዎች ያሠለጥን ነበር።
ይህ ወቅት ሞቃዲሾ ውስጥ ሁለት የአሜሪካ ኤምኤች-60 ብላክ ሀውክ ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ተመተው የወደቁበት ነው።
‘ብላክ ሀውክ ዳውን’ በሚል ርዕስ በ2001 በሆሊውድ ፊልም ተሠርቶበታል።
ሄሊኮፕተሮቹን ለመጣል ከተተኮሱት ሮኬቶች አንዱን የተኮሰው ቱኒዝያዊው የአል ቃኢዳ አባል እንደነበር ይታመናል።
አል አድል በ1990ዎቹ አጋማሽ ወደ አፍጋኒስታን ተመለሰ።
ይህ ወቅት ታሊባን አፍጋኒስታንን በቁጥጥሩ ሥር ማስገባት የጀመረበት ነው።
አሜሪካ በ2001 አፍጋኒስታንን ስትወር በድጋሚ አፍጋኒስታንን ለቅቆ ወጣ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደኅንነቱ በተጠበቀ ቦታ ተሸሽጎ አል ቃኢዳ ኢራን ላይ የሚፈጽማቸውን ኦፕሬሽኖች ይመራ ነበር።
በ2003 በኢራን አመራሮች ታስሮ እንደነበር ይገመታል።
ከ12 ዓመታት በኋላ በእስረኞች ልውውጥ ከሌሎች የአል ቃኢዳ አባላት ጋር ነጻ እንደወጣም ይነገራል።
ለዓመታት ቢታሰርም በአል ቃኢዳ ያለው ተጽዕኖ ፈጣሪነት አልተሸረሸረም።
ቢን ላደን በአሜሪካ ልዩ ኃይል ፓኪስታን ውስጥ በ2011 ከተገደለ በኋላ፣ አል ዛዋሂሪ የአል ቃኢዳን መሪነት እንዲጨብጥ አግዟል።
አል አድል በቀላሉ ወደ መሪነት ይመጣል ተብሎ እንደማይታሰብ የአሜሪካ የሽብር ጉዳዮች ተንታኝ ኮለን ፒ ክላርክ ይናገራሉ።
አንደኛ አል አድል ኢራን ውስጥ "በከፊል የቁም እስር" ላይ ይገኛል።
ይህም ወደ ቡድኑ መሪነት እንዳይመጣ ሊያሰናክለው ይችላል።
የሺዓ እስልምና እምነት ማዕከል በሆነችው ኢራን ውስጥ ሆኖ ዓለም አቀፍ የጂሀዲስት ንቅናቄን መምራት አይታሰብም።
የደኅንነቱ ጉዳይም አጠያያቂ ነው።
ሌላ ከፍተኛ የአል ቃኢዳ አባል የሆነው አቡ መሐመድ አልማስሪ በ2020 ቴህራን ውስጥ በእስራኤል ኮማንዶዎች መገደሉ አይዘነጋም።
ከአል አድል ውጭ አልቃይዳን ማን ሊመራ ይችላል?
ከአል አድል ውጭ ወደ አል ቃኢዳ አመራርነት ይመጣሉ ተብለው የሚጠበቁ ብዙም አይደሉም።
ለዚህም ምክንያቱ ባለፉት ዓመታት እንደ አል ዛዋሂሪ የአል ቃኢዳ አመራሮች መገደላቸው ነው።
ምናልባትም አል ቃኢዳ ወደ አጋር ድርጅቶቹ አመራሮች ፊቱን ሊያዞር ይችላል።
ይህም የሶማሊያውን አል ሻባብ፣ የየመኑን ኤኪውኤፒ እና የማሊውን ጄኤንአይኤምን ይጨምራል።
አል ቃኢዳ ይሄንን ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ባይጠበቅም፣ በአል ዛዋሂሪ አመራር ዘመን ቡድኑ ውስጥ የተፈጠረው ያልተማከለ አስተዳደር ወደዚህ ውሳኔ ቢገፋው ብዙም አያስገርምም።
በ2013 የኤኪውአይኤም መሪ ናስር አል ውሃይሺ፣ የአል ዛዋሂሪ ምክትል ነው ተብሎ በስፋት ተነግሮ ነበር።
ይህም የአጋር ቡድን አመራሮች ወደ ማዕከላዊ አመራርነት ቦታ ሊመጡ እንደሚችሉ ይጠቁማል።
አል ውሃይሺ በ2015 በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ተገድሏል።
አል ዛዋሂሪን ማንም ይተካው ማንም እንደ ቀድሞዎቹ የአል ቃይዳ መሪዎች በአሜሪካ ላለመገደል ትግል ይጠብቀዋል።












