“የማያልቅ ጦርነት ውሃ በወንፊት ነው፤ ዝም ብሎ እየተዋጉ መኖር አይቻልም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

የፎቶው ባለመብት, @PMEthiopia
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዛሬ ፓርላማ ውሏቸው ሰላምና ብልጽግና ለማስቀጠል ጦርነት ማቆም ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ተናገሩ።
“የማያልቅ ጦርነት ውሃ በወንፊት ነው፤ ዝም ብሎ እየተዋጉ መኖር አይቻልም። የሰላም መጥፎ የጦርነት ጥሩ የለውም፤ እያሸነፉም ቢሆን መጥፎ ነው። የምናስባቸውንም ነገሮች ማሳካት አንችልም” ሲሉም ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የተናገሩት በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ ስለተፈረመው ግጭትን የማቆም ዘላቂ ስምምነት አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ስለሰላም አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተዋል።
“ከሰላም የምታተርፈው ኢትዮጵያ ናት። ሰው ይገደላል፤ ዶላር ይተኮሳል። ዶላር እየወጣ እና ሰው እየተገደለ የሚገኝ ጥቅም እና ጥሩ ነገር የለም” ብለዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት በሁለቱ አካላት ስለተደረሰው ስምምነት ይዘት፣ እንዲሁም ሰላሙን ስለማይፈልጉ አካላትም ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል።
በተለይም ህወሓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ ከመፈረጁ ጋር ተያይዞ እንዴት ትደራዳራላችሁ? ለሚል ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቦላቸዋል።
“ከአሸባሪ ጋር ድርድር ማድረግ የሚከለክል አዋጅ የለም። ድርድር፣ ውይይት ለኢትዮጵያ ሰላም ዕድገት፣ ብሔራዊ ጥቅም ከሆነ እናደርጋለን” ብለዋል።
ሆኖም የሰላም ስምምነቱን የማይፈልጉ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው “ሰላም የሚያስከፋቸው ሰዎች የጦርነት ነጋዴዎች ናቸው” ሲሉ ወቅሰዋል።
ሆኖም የሰላም ድርድሮች ከተፈረሙም በኋላ በመተማመን እጦት ምክንያት ይበላሻሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረሰው ድርድር እንዲጸና ቃል በመጠበቅና ድጋፍ በመስጠት መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
“የወልቃይት ጉዳይ በሕግ እና በሥርዓት አግባብ ይመለሳል”
ሌላኛው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸው ጥያቄ ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል ስር ያለው የምዕራብ ትግራይ ወይም ወልቃይት ጉዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወልቃይት ጉዳይ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሰረት በሥርዓት እና በምክክር በሰላም መቋጨት እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ከፌደራል መንግሥት ጋር እያገናኙ የሚነገሩ ሽረባዎች ውሃ የማይቋጥሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
“ይህን በሕግ እና በሥርዓት ብንፈጽም ለወልቃይት ይጠቅማል። ለአማራ ይጠቅማል። ለትግራይ ይጠቅማል። የሚጎዳው ነገር የለም። በሕግ እና በሥርዓት እንፈጽም የሚለውን ነገር ከብዙ ተንኮል ጋር ማያያዝም አስፈላጊ አይደለም። እዚያ አካባቢ ጥያቄ ረዘም ላለ ጊዜ ነበረ። ከዚህ ቀደም ኮሚሽን ያቋቋምነው ለዚያ ብለን ነው። አሁንም ያኔም የነበረን አቋም በሕግ አግባብ በምክክር በውይይት ይፈታ የሚል ነው።”
በኢትዮጵያ ውስጥ ከወልቃይት በተጨማሪ ሌሎችም አካባቢዎች የይገባኛል ጥያቄ እንዳሉ ጠቅሰው፣ በጉልበትና በኃይል ሳይሆን በሕግ እና በሥርዓት አግባብ መፈታት መቻል እንዳለበት ጠቅሰዋል።
“ወልቃይት ብቻ አይደለም፤ ሰሜን ሸዋ ላይ ኦሮሚያ እና አማራ ጥያቄ አላቸው። እሱም ደቡብ አፍሪካ ይሂድ? ሲዳማ እና ወላይታ፤ ብላቴ ላይ ጥያቄ አላቸው። እሱም ደቡብ አፍሪካ ይሂድ? ቦታው አይደለም። የተስማማነው በኢትዮጵያ ሕግ እና ሥርዓት ይፈጸም ነው።”
በኃይልና በጉልበት ለመቋጨት የሚደረግ ጥረት ዘላቂ ሰላም አያስገኝም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወልቃይትን ሕዝብ ማዕከል ባደረገና በአገሪቱ ሕግና ሥርዓት አግባብ እንደሚፈታም ነው የተናገሩት።
“ከሕገ መንግሥት በፊት ህወሓት በግድ ስለወሰደ አሁን እኛ ደግሞ በግድ ወስደን፤ እዚያ ዘመኑን በሙሉ ወታደር ልናቆም አንችልም። በስምምነት ካልሆነ በወታደር ነው የሚሆነው። በወታደር ከሆነ ዘላቂ አይሆንም። ጊዜ ይፈታዋል። አሁን ያለን ሰዎች ስናረጅ፣ ስንደክም፤ ልክ አሁን የተፈጠረው ይፈጠራል።”
በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች ላይ እየተሰጠ ስላለው ምላሽ
ሌላኛው በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን በተመለከተ መንግሥታቸው ሦስት እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ አስረድተዋል።
በዚህም በሰብዓዊ እርዳታ በመደገፍ፣ መሠረተ ልማቶችን መገንባት እና የተፈናቀሉ ሰዎችን መመለስ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
እስካሁን ባለው የኤሌክትሪክ አግልግሎት በተቋረጠባቸው ለምሳሌ ሰቆጣ፣ አላማጣና ኮረም እንደተመለሰ ገልጸው፤ “ሰላም ተብሎ ሳምንት እንኳን ሳይቆጠር ፈጣን ምላሽ ነው የሰጠነው” ብለዋል።
ከስምምነቱ ትግበራና ይዘቶቹ በተጨማሪ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች፣ የዲፕሎማሲ፣ የምጣኔ ሃብት፣ ኢንቨስትመንት እና የዋጋ ግሽበትን የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፋ ያለ ሰዓት ወስደው መልስ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን ንግግር በተመለከተ ማብረሪያና ከምክር ቤቱ ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።
“ከክላሽ ባሻገር ለመነጋገር በሩ ክፍት ነው”
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ወይም መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው ኃይልን በተመለከተ በሽብር የሚገኝ ነጻነት፣ ዲሞክራሲ እንደሌለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ከሸኔም ጋር ቢሆን ትጥቁን ከፈታ ለመነጋገር መንግሥታቸው ዝግጁ ነው ብለዋል።
ሆኖም ሸኔ የአመራር ሥርዓት እና የዕዝ ሰንሰለት የሌለው እንዲሁም የሚልኩትንም ግራ ያጋባ ነው ብለዋል።
“ንጹሃንን በመግደል እና መኪና በማቃጠል የሚገኝ ጥቅምም ትርፍ የለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሸኔ ለኦሮሞ ቆምኩ የሚል ኦሮሞን እና ኦሮሚያን የሚያፈርስ፣ ፍላጎቱ የማይታወቅ ነው” ብለዋል።
ሆኖም ከክላሽ ባሻገር ለመነጋገር ከተፈለገ በሩ ክፍትም እንደሆነም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የተከለከሉ ዜጎችን በተመለከተ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ በፍትህ ሥርዓቱ ያለውን ክፍተት፣ ሙስና ሌብነትንም በተመለከተ ምላሽ ሰጥተዋል።
የዜጎች እንቅስቃሴ የተገደበው አዲስ አበባን ለማሸበርና ለማናጋት ሰፊ እቅድ የተያዘ በመሆኑ ለሰላምና ለደኅንነት ሲባል መጉላላቱ ቢፈጠርም ለአገር ሲባል የተደረገ ነው በሚል መታየት አለበት ብለዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ሌብነት፣ እንዲሁም የፍትህ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን አምነው “የቴሌግራም ቡድን ከፍተው ጉቦ የሚቀባበሉ ዳኞች አሉ። ይሄንን አሰርኩ፤ ይሄንን ፈታሁ” ይላሉ በከፍተኛ ደረጃ ሪፎርም መደረግ አለበት ብለዋል።
ዲፕሎማሲን በተመለከተ
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ መገለጫ እኩልነት፣ ነጻነትና ፍትሃዊነት ነው እንደሆነም ገልጸው ከዘመን ዘመን አይቀያየርም ብለዋል።
በተጨማሪም “የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሄ መበጀት አለባቸው” እንዲሁም ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት ሥርዓት የተመሰረተ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በባለፉት ሦስት ወራት ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን ጥሩ ሥራ በመስራት መልካም ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
በተለይም ከሱዳን ጋር የማያግባበቡ ችግሮች መልክ ይዘው በጥሩ ግንኙነት ላይ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በመጨረሻው ውጊያ ሱዳን ምንም አይነት ድጋፍ ሳታደርግ ከኢትዮጵያ ጋር ቆማለች እንዲሁም በነበረው ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን ቆማ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በተለይም ጦርነቱ በሰላም እንዲቋጭና ለሰላም ስምምነቱ የኬንያ መንግሥት ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካና ሌሎችም አገራት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጨማሪም ምጣኔ ሃብቱ ላይ ከፍተኛ እመርታ መታየቱን በተናገሩበት በዛሬው ፓርላማ ተናግረው የታዩ እመርታዎችን ጠቅሰዋል።
“ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ ግዙፉ ምጣኔ ሃብት ማድረግ ችለናል”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከምሥራቅ አፍሪካ ግዙፉ ኢኮኖሚ በመሆን በአንደኛ ስፍራ መቀመጥ መቻሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ሦስተኛ ግዙፍ ምጣኔ ሃብት ደረጃ ላይ እንደሆነም የዓለም ባንክ መረጃን ነው የጠቀስኩት ሲሉ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2014 የበጀት ማጠናቀቂያ 6.16 ትሪሊየን ብር (127.6 ትሪሊየን ዶላር) ደርሷል። ከመቶ ቢሊዮን፣ ትሪሊየን ማለፍ ፈታኝ በሆነበት ሁኔታ ብልጽግና አላማውም ግዙፉ ምጣኔ ሃብት የማድረግ አቅዶ የነበረ ሲሆን እሱም ተሳክቷል ብለዋል።
በተጨማሪም የነፍስ ወከፍ ገቢ 1212 መድረሱም ተገልጿል።
በባለፈው ዓመት የጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 6.4 በመቶ የተመዘገበ ሲሆን፣ አሁን የተፈጠረውን የሰላም ሁኔታ ማስጠበቅ ከተቻለ 7.5 ለማሳደግ መታቀዱንም ነው ያስረዱት።
መረጃው የዓለም ባንክ እንደሆነ ገልጸው በዚህ አሃዝ መንግሥታቸው አይስማማም ብለዋል።
ለዚህም ያነሱት በአገሪቱ ውስጥ ያለው የኢ-መደበኛ የንግድ ልውውጥ እና የሃብት እንቅስቃሴ የምጣኔ ሃብቱ አካል ሆኖ ባለማከተቱ እንደሆነ ጠቅሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ዓለም ባንክ ከጠቀሰው አሃዝ “በእጅጉ የገዘፈ ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ባለፉት ዓመታት ሰው ስራሽ እና የተፈጥሮ ፈተናዎች ገጥመውታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከእነዚህም ውስጥ በአገር ውስጥ ያለው ጦርነት፣ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽና ድርቅን ጠቅሰውታል።
እነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ምጣኔ ሃብቱን ቢደቁሱትም በቀላሉ የማይሰበር እንደሆነ አሳይ ነው ብለዋል።
ፈተናዎቹ የራሳቸው ስብራት ቢኖረውም መንግሥታቸውን የበለጠ እንዲሰራ አድርገውታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ያጋጠመውን ጫና መሻገሩ በርካታ ዓለም አቀፍ ተንታኞችን ያስደነቀና ያስደመመ ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም ኢንዱስትሪ መር እና የግብር መር የሚለው ተትቶ በርካታ ዘርፎችን ባካተተ እንዲመራ መደረጉም ለዚህ አስተዋፅኦ እንዳደረገም ተገልጿል።
በኢንቨስትመንት ዘርፉም ከፍተኛ እመርታ ታይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውጭ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው ኢንቨስትመንት (ፎሬይን ዳይሬክት ኢንቨስትመን) ከ4 በመቶ በላይ እንደሆነ ገልጸው ይህም በምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ዕድገት ካሳዩዋቸው ዘርፎች መካከል ግብርና ጠቅሰው 6.1 በመቶ ዕድገት ማሳየቱም ተነግሯል።
በዚህም በከፍተኛ ሁኔታ አበረታች ውጤት እያሳየ ያለው ስንዴ ልማት እመርታ ያሳየ ሲሆን በተጫማሪም ብዙም ያልተነገረለት የሩዝ ምርት በተለይም በአማራ ክልል አመርቂ ውጤት እንዳሳየም ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የሩዝም ምርት የሚጠበቅ ሲሆን አገሪቷ በሩዝ ምርት ከውጭ የምታስገባውን ታስቀራለች ብለዋል።
በተጨማሪም በአገሪቷ ውስጥ ያሉ የማኑፋክቸሪንግ፣ ሰርቪስና የፋይናንስ ሴክተሩ ከፍተኛ እመርታ ማሳየቱም ተነግሯል።
አገሪቷ በከፍተኛ ሁኔታ ጠንከራ ከሰራች “ኢትዮጵያን የዳቦ ቅርጫት ማድረግ የሚያስችል መሰረት መጣል ያስችላል” ብለዋል።
የዋጋ ግሽበት ቅናሽ እያሳየ ነው
በዛሬው ዕለት ከምክር ቤት አባላት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አገሪቷ እያጋጠማት ያለው የዋጋ ግሽበት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ምላሽ ሲሰጡ በዋጋ ግሽበት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ብዙ አገራት እየተፈተኑ እንዳሉ ገልጸው፣ ለዚህም የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን፣ እንዲሁም በጦርነት ምክንያት የአቅርቦት መስተጓጎል ማጋጠሙን ጠቅሰዋል።
ግሽበት ለማክሮ ምጣኔ ሃብት ስብራት ቢሆንም በባለፉት አራት ወራት የዋጋ ግሽበት መቀነስ እያሳየ ነው ብለዋል።
ለዚህም መንግሥታቸው አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰዱን ጠቅሰው በዚህም መንግሥት ጣልቃ በመግባት ምርቶችን ማቅረብና አርሶ አደሮች አዲስ አበባ መጥተው የእሁድ ገበያ መዘርጋቱ ለገበያው መረጋጋት ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
በተጨማሪም 9.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ መግባ እያስተማረች ነው ብለዋል። ይህም አገሪቷ እየሰራች ያለችው አኩሪ ሥራ ነው ብለው ይህም ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን ነዋሪዎች መደጎም እንዲያስችል እንደሆነም አስረድተዋል።
በተጨማሪም ምንም ገቢ ለሌላቸው ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች በአዲስ አበባ 11 መመገቢያዎች ሄደው ምግብ የሚቀርብበት የማዕድ ማጋራት እየረዳ ነው ብለዋል። ይህ ሁሉ ጥረት ተደርጎም የገበያ ትስስር ክፍተት አሁንም የቀጠለ ችግርና ብዙ ሥራም የሚጠብቀው ነው።
በቅርቡም የነበረውን አይኤምኤፍ እና ወርልድባንክ ግምገማ መረጃንም በመጥቀስ 2 በመቶ የዋጋ ግሽበት እንደሚቀንስ ተንብየዋል ብለዋል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ 38 የሸቀጥ አይነቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ማገዷን ተከትሎም ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
ኢትዮጵያ 18 ቢሊዮን ዶላር ከብሔራዊ ባንክ በኩል የምታወጣ ሲሆን፣ ይህም ለስድስት ሺህ ሸቀጥ አይነቶች ነው ብለዋል።
እገዳ የተጣለባቸው 38 ሸቀጦች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ ገልጸው ይህም ለማዳበሪያ ከሚወጣው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነም ነው የጠቀሱት።
ይህ ውሳኔ ሰፊ ጥናት እንደተደረገበት ገልጸው እንደ ምክንያት የጠቀሷቸው ለአገር ውስጥ ምርት ዕድል ለመስጠት፣ ለጥቁር ገበያ መጋለጥና መሠረታዊ ሸቀጦች አለመሆን ተካትተዋል።
“እነዚህ ሸቀጦች መኪና፣ ውስኪ፣ ፀጉር የተካተቱበት ሲሆን አሁን አገሪቱ ባለባት ጫና ቢቆዩ አይጎዱም በሚል እገዳ ተጥሎባቸዋል” ብለዋል።
በተጨማሪም መሬት ጋር ተያይዞ መጠነ ሰፊ ችግሮች ጋር እንደተያያዘ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት የመንግሥት፣ የሕዝብም አይደለም የደላሎች እና የሌቦች ሹመኞች ሆኗል፤ ይህ ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል። ቢያንስ በከተሞች መሬት ወደ ግል መዘዋወር ይኖርበታል ብለዋል” ሆኖም ውይይት መካሄድ አለበት ብለዋል።












