'ጠጅ' ኢትዮጵያ ምን ትሠራለች?

የፎቶው ባለመብት, MIKIYAS GIRMA
ጠጅ ትባላለች። በርግጥ ወላጆቿ ተዥ ወይም ተጅ-ሬይ ብለው ነው የሚጠሯት። ኑሮዋን ኢትዮጵያ ካደረገች ወዲህ ግን ስሟ ጠጅ ሆኗል እርሷም አልተቃወመችዉም።
እንደውም እ.አ.አ በ70ዎቹ በአሜሪካ ያሳደጓት ወላጆቿ ከ8 ዓመቷ ጀምሮ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጰያ ምግብ ቤት አዘውትረው ይወስዷት እንደነበር በፈገግታ ታሰታውሳለች። ዕድሜዋም ከፍ ካለ በኋላ ጠጅ ይታዘዝላት አንደነበርም ትናገራለች።
የያኔዋ ተጅ ሬይ ስሟ ከሌሎች ሁሉ ይለይ እንደነበር ታስታውሳለች።
የጓደኞቿ ስም በመጻሕፍት ውስጥ ገፀባሕሪ ሆኖ ሲመጣ፣ በልብስ ላይ ታትሞ ሲለበስ፣ መጫወቻዎች ላይ በቀላሉ ሲገኝ የእርሷ ግን በኢትዮጵያ ምግብ ቤት ውስጥ ብቻ ነበር የሚገኘው።
በኢትዮጵያ ምግብ ቤት ውስጥ በብርሌ ተሰይሞ በልጅነቷ ያየችው ጠጅ እና የእርሷ የአትዮጵያ ቁርኝት በዚህ መንገድ ይሰምራል ብላ አስባ ታውቅ ይሆን?
'ጠጅ'
"ወላጆቼ ስሜን ፈጥረዉ ነዉ ያፀደቁት" የምትለው ጠጅ በፈረንጆቹ 70ዎቹ "ጉግል አልነበረም፤ ወላጆቼም ለየት ያለ ያልተለመደና ተሰምቶ የማይታወቅ ስም ሊሰጡኝ ፈልገው እንዴት እንደመጣላቸዉ ባላውቅም 'ጠጅ' ብለውኛል።"
ወደ ኢትዮጵያ ከመጣች ሦስት ዓመታት ያስቆጠረችዉ 'ጠጅ' ላለፉት 30 ዓመታት በየሁለት ሦስት ዓመቱ በባለቤቷ ሥራ ምክንያት በተለያዩ አገራት ስትዞር ቆይታለች።
"ደራሲ ስለሆንኩኝ የትም ሆኜ መሥራት እችላለሁ። ጋዜጠኛም ሆኜ የሠራሁበት ወቅት ነበር። አሁን የሕፃናት መጸሐፍት እየፃፍኩኝ ሲሆን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛም ተተረጉሞ ታትሞልኛል" ትላለች።
ጠጅ መጽሐፏ ወደ አማርኛ እንዲተረጎም የፈለገችዉ ኢትዮጵያውያን ልጆች አንብበው እውቀት እንዲቀስሙ ብቻ አለመሆኑን በመጥቀስ "አማርኛ መማር ፈልጌ ስለነበር በትርጉሙ በኩል ብዙ ተምሬአለሁ። እንደኔ እንግሊዘኛ መማር የሚፈልጉ ደግሞ ሊማሩበት ይችላሉ" ትላለች።
ጠጅ ኢትዮጵያን ቤቴ ብላ የሰየመቻት ሲሆን ለኢትዮጵያ ያላት ፍቅርና አክብሮት የሚመነጨዉ ከስሟ መመሳሰል የተነሳ ብቻ አለመሆኑን ትናገራለች።
"ኢትዮጵያውያን ለሚኖሩበት ማኅበረሰብ የሚሰጡት ቦታና ዋጋ በጣሙን ልቤን ይነካዋል። የትም ላገኘው ያልቻልኩት የመፋቅር፣ የመዋደድና የመከባበር ስሜት ነው ያገኘሁት። ለእኔ ደግሞ ማኅበረሰባዊ ኑሮና መቀራረብ በጣም ትልቅ ቦታ አለው። ስለዚህም ኢትዮጵያ ለእኔ በጣም ትልቅ ቦታ አላት።"
በተጨማሪም በምትኖርበት አካባቢ የማኅበረሰቡ አንድ አካል ለመሆን ጊዜ እንዳልፈጀባትና ይህም ደግሞ ጥልቅ ፍቅር እንዳሳደረባት የምትገልጸው ጠጅ "ኢትዮጵያውያን ለትምህርት፣ ለእውቀትና ለመረጃ የሚሰጡት ቦታ ያስደስተኛል። መጽሐፌን ካሳተምኩበት ጊዜ አንስቶ እንኳን ብዙ ትምህርት ቤቶችን መጎብኘት ችያለሁ። በዓይኖቻቸዉ የንባብ ጥማት ከተሞሉ ልጆችም ጋር አብረን አንብበናል" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, MIKIYAS GIRMA
የ'ጠጅ' መጽሐፍ
የመጽሐፉ ሃሳብ የመጣላት ከመንገድ ላይ ወድቃ የተገነች ውሻን ለማሳደግ በወሰነች ጊዜ መሆኑን ትናገራለች።
ልታሳድግ ወደ ቤቷ ያመጣቻት ውሻ በቤታቸዉ በራፍ አምቡላንስ ባለፈ ቁጥር አብራ እንደምተጮኽ ጠጅ አስተዋለች።
አተኩራ ስትከታተላትም ዉሻይቱ እርሷም አምቡላንስ የሆነች መስሏት እንደሚሆን ተረዳች። የመጽሐፉም ፍሬ ሃሳብ በዚህ መልክ ተጠነሰሰ።
ጠጅ ከመንገድ የወደቁ ዉሾችን ሰበስቦ ከሚንከባከብ ድርጅት ጋር በቅርበት ትወያይ ነበር። እነርሱም ስለምታሳድጋት ውሻ ጤንነት፣ ፀባይና በተለይ ደግሞ ከጠጅ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጣራት በየጊዜዉ ይደውሉላት ነበር።
በዚህ ወቅት ነበር የጠጅ እና የድርጅቱ ግንኙነት ከውሻዋ አልፎ ድርጅቱ ስለሚሠራው ሥራና ምን ዓይነት እርዳታዎች አንደሚያስፈልጓቸው ወደ መወያየት የተሸጋገረው።
'አዲስ አኒማል ፕሮጄክት' ዉሾችን ብቻ ሳይሆን አህዮችንና ሌሎችንም የተጣሉ፣ የተረሱና የማይፈለጉ እንስሳት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ድርጅት ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ በበጎ ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚመራ ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በተደረገ ጥናት መሠረት በአዲስ አበባ በአጠቃላይ ሩብ ሚሊዮን እንስሳት በመንገድ ላይ መኖራቸውንም የደረሰችበት ጠጅ የሆነ ነገር መደረግ እንዳለበት ታስባለች።
"ምክንያቱም ሰዎችና እንስሳት አብረው ነዉ የሚኖሩት። በተሻለ ሁኔታ እንዲኖሩ ማድረግ ደግሞ ይቻላል" ትላለች።
ድርጅቱ በአዲስ አበባ ያሉ የመንገድ ላይ ውሾችን ቁጥር የመቀነስ ዓላማ ይዞ የተነሳ መሆኑንና ይህንንም ለማድረግ ለዉሾቹ ሕክምና፣ እንክብካቤና መኖርያ በማመቻቸት መሆኑን ይነግሯታል።
የጠጅም ልብ ይነካል። እርሷ ለማሳደግ የወሰደቻትን ውሻ መነሻ በማድረግ ለኢትዮጵያውያን ሕፃናትና ልጆች መንገድ ላይ የተተዉ እንስሳትን ስለመንከባከብ የሚያሰተምር ታሪክ መፃፍ ጀመረች።
ጓደኛሞቹ
ጠጅ የመጽሐፉን ታሪክ የጀመረችው በአንዲት ትንሽ ሴት ልጅና በአንዲት ቡችላ ነው።
ታሪኩ መልካም ጓደኛሞች የሆኑት ልጅቷን እና ዉሻይቱን ቢከተልም ዋናው መልዕክት ግን ዉሾች በመንገድ ላይ ስለሚደርስባቸዉ መከራ ነው።
ይህን ታሪክ ስትፅፍ በ'እኔ የተሻለ አውቃለሁ' ወይም 'እንዴት አታውቁም' መንፈስ አለመሆኑን ትናገራለች።
"ሃሳቤ ውይይቱን ማስጀመር ብቻ ነበር። ቢያንስ ልጆች ስለ መንገድ ላይ እንስሳት ችግሮች ግንዛቤው ካላቸው ትልቅ ሆነው ለማኅበረሰባቸውና ለአገራቸው አሰተዋፅዖ ለማድረግ ሲደርሱ ነገሮችን ለመቀየር ይችሉ ይሆናል በሚል እሳቤ ነበር" ትላለች።
ጠጅ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመገኘት ለልጆች መጽሐፉን በምታነብላቸው ወቅት "ቤት ውሻ አላችሁ?" ስትል ትጠይቃቸዋለች።
ሕፃናቱ አብዛኛውን ጊዜ በ5 እና 8 ዓመት ዕድሜ ክልል ያሉ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ አለን ሲሉ ገሚሶቹ ደግሞ እንደሌላቸው ይነግሯታል።
ጠጅ ቀጥላ የምትጠየቃቸዉ ጥያቄ "ዉሻ ትወዳላችሁ?" የሚል ነው።
አሁንም በድጋሚ ክፍሉ ግማሽ ግማሽ ይሆናል ትላለች። አንዳንዶቹ ይወዳሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ይጣላሉ።
"ገና ታሪኩን አንብቤ ሳልጨርስ ግን ... እንደተጋመሰ መላው ክፍል ለዉሻዋ እጅግ በጣም ማዘን ይጀምራል። መከራዋም እንዲቆምላት ምኞታቸውን መግለፅ ይጀምራሉ" ትላለች።
ንባባቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ውይይታቸውን ለእንስሳት በተለይም ደግሞ ለዉሾች መደረግ ስላሉባቸው እንክብካቤዎች መማከር ይጀምራሉ።
ልጆቹም የተለያዩ አማራጮችንና ሃሳቦችን ያቀርባሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለዉሾች ትልቅ ቦታ ስለማይሰጥ መሠረታዊ ሊመስሉ የሚችሉ ነገሮች በሁሉም ዘንድ አይታወቁም ትላለች።
ይህንንም ግንዛቤ ለማስፋትና ለማካፈል መጽሐፉ ዕድል እንደከፈተላት ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, MIKIYAS GIRMA
ሰዎች ምን ይላሉ?
ጠጅ እንደምትለው አልፎ አልፎ የተቸገሩ ሰዎች እያሉ እንስሳት ላይ ትኩረት ማድረጓ ትችትን አስከትሎባት ያውቃል።
"እኔ ለሰው ልጅ የምሰጠው ቦታ በጣም ትልቅ ነው። ቅድሚያ ሊሰጧቸው የሚገቡ ጉዳዮችም መኖራቸውን አምናለሁ። ስለ እንስሳትና ስለ ውሾች ችግርና መከራ በማነሳበት ወቅት ጉዳዮችን እያበላለጥኩ ሳይሆን፣ አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ነው" ትላለች።
ጠጅ እንደምታስረዳው ሩብ ሚልዮን እንስሳት ጎዳና ላይ አሉ ማለት ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር "እንስሳቱ እየተባዙ ሲቀጥሉ እንዴት ነው የምንሆነው?" በማለት ጭንቀቷን ትገልፃለች።
"ለዚህም ነው ነገሩ ሳይባባስ . . . ቀደም ብለን ሰብዓዊ የሆኑ መፍትሔዎችን ከወዲሁ እየሠራንባቸው መምጣታችን ጥቅሙ የታየኝ" በማለት ጠጅ ተነሳሽነቷንና ፍላጎቷን ታስረዳላች።













