የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ከኃላፊነታቸው ተነሱ

ኦሌክሲ ረዝኒኮቭ ምናልባት አምባሳደር ሊሆኑ ይችላሉ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ኦሌክሲ ረዝኒኮቭ ምናልባት አምባሳደር ሊሆኑ ይችላሉ

የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲ ረዝኒኮቭ ከሥልጣናቸው ተነሱ።

የመከላከያ ሚኒስትሩ መነሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩክሬን ባለሥልጣናት ዘንድ እየተስፋፋ ነው ከሚባለው ሙስና ጋር የተያያዘ ይሁን አይሁን የተባለ ነገር የለም።

ሚኒስትር ረዝኒኮቭ የሩሲያ ወረራ ከተጀመረበት ከየካቲት 2022 ዓ/ም ጀምሮ በኃላፊነት ቆይተዋል።

ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ትናንት ማምሻውን ባደረጉት ንግግር ሚኒስትሩን ያነሳኋቸው በጦርነቱ ‘አዲስ አካሄድ’ እንደሚያስፈልግ በመታመኑ ነው ብለዋል።

የተነሱትን መከላከያ ሚኒስትር እንዲተኩ በእጩነት የቀረቡት ረስቴም ኡሜሮቭ ይባላሉ።

ኡሜሮቭ የዩክሬን የመንግሥት ንብረትና ፈንድ ባለሥልጣን ኃላፊ ናቸው።

የዩክሬን መገናኛ ብዙኃን አሁን ከመከላከያ ሚኒስትርነት የተነሱት ኦሌክስ ረዝኒኮቭ በሎንደን የዩክሬን አምባሳደር ሊሆኑ እንደሚችሉ ዘግበዋል።

ረዝኒኮቭ ከዩኬ ባለሥልጣናት መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል።

የ57 ዓመቱ ረዝኒኮቭ ከጦርነቱ ወዲህ በዩክሬንና በምዕራቡ ዓለም ስማቸው እየጎላ ከመጡ ባለሥልጣነት አንዱ ናቸው።

በበርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች በመገኘት ንግግር በማድረግ እንዲሁም ምዕራቡ ዓለም ለዩክሬን አስፈላጊ የጦር መሣሪያዎችን እንዲለግስ በማግባባት በይበልጥ ይታወቃሉ።

ምንም እንኳ ዘለነስኪ በጦር ሜዳ ‘አዲስ አካሄድ በማስፈለጉ ነው’ ሚኒስትሩ የተነሱት ይበሉ እንጂ የርሳቸው መነሳት መሬት ላይ የሚለውጠው ነገር ላይኖር እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ።

ⶏርነቱን የሚመሩት ጄኔራል ቫለርይ ዛሉዥኒ አሁንም በኃላፊነት ነው ያሉት።

የሚኒስትሩ መነሳት ዘለንስኪ የጸረ ሙስና ዘመቻውን ባጧጧፉበት ወቅት የተከሰተ ነው።

ዩክሬን የአውሮፓ ኅብረትን ለመቀላቀል ለዓመታት ፍላጎት ብታሳይም አንድ ማነቆ ሆኖ ያቆያት ከፍተኛ ሙስና የተንሰራፋበት አስተዳደር በመኖሩ ነበር።

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ዩክሬን ከ180 አገራት በሙስና 160ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።

ምንም እንኳ ተሰናባቹ መከላከያ ሚኒስትር ስማቸው በሙስና ባይነሳም እርሳቸው በሚመሩት መከላከያ ሚኒስትር ግን ከንብረት ግዥ ጋር በተያያዘ ገንዘብ መመዝበሩ አይዘነጋም።

ከዚሁ ምዝበራ ጋር ተያይዞ የርሳቸው ምክትል የነበሩት ሻፖቫሎቭ ከሥልጣናቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።

ዩክሬን መልሶ ማጥቃት ዘመቻ ከፍቻለሁ ካለች ወዲህ በጦር ሜዳ የተጠበቀውን ያህል ድል ባይቀናትም በደቡባዊ ግንባር መጠነኛ ገዥ መሬቶችን ከሩሲያ ማስመለሷን ትናገራለች።