የሙጋቤ ልጅ ዱባይን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች 25 ቤቶች እንዳሏት የፍርድ ቤት ሰነድ አረጋገጠ

ቦና ሙጋቤ ከሦስት ዓመት በፊት በአባቷ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከባለቤቷ ሲምባ ቺኮሬ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቦና ሙጋቤ ከሦስት ዓመት በፊት በአባቷ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከባለቤቷ ሲምባ ቺኮሬ ጋር

የሟቹ የዚምቧብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሴት ልጅ 25 መኖርያ ቤቶች በስሟ እንዳሉ፤ ዱባይ ውስጥ የተንጣለለ ውድ መኖርያ ቤት እንዳላት አንድ የፍርድ ቤት ሰነድ አረጋገጠ።

የ33 ዓመቷ የሙጋቤ ልጅ ያሏት እነዚህ ቤቶች በድምሩ 80 ሚሊዮን ዶላር ይገመታሉ።

ቢቢሲ በተመለከተው እና ለፍርድ ቤት በቀረበ የፍቺ ጥያቄ ላይ የተካተተ አንድ ሰነድ እንዳረጋገጠው፣ ቦና ሙጋቤ ያላት ንብረት ከዚህም የሚልቅ ነው።

ቦና ሙጋቤ የፍቺ ጥያቄ ለፍርድ ቤት ያቀረበችው አውሮፕላን አብራሪ ከነበረው ባለቤቷ ሲምባ ቺኮሬ ጋር ለመለያየት ነው።

ካፒቴን ቺኮሬ በበኩሉ ሃብታቸውን ለመካፈል ጥያቄ አቅርቧል።

ቦና ሙጋቤ በቀድሞ ባለቤቷ የሃብት እንካፈል ጥያቄ ገና ምላሽ አልሰጠችም።

ለሙጋቤ ቤተሰብ ቅርብ የሆኑ ታማኝ የቢቢሲ ምንጮች እንደመሰከሩት፣ የቦና አባት ሮበርት ሙጋቤ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ሃብት ንብረት በስማቸው አልነበረም።

ይሁንና የጡረታ ጥቅማ ጥቅሞች በሚል ከአገሪቱ 10 ሚሊዮን ዶላር ይሰጣቸው ነበር።

ይህን ዜና ተከትሎ የዜምቧብዌ ዜጎች ቁጣ እና አግራሞታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ቢቢሲ በተመለከተው የፍቺ ሰነድ ላይ፣ ከእነዚህ ውድ ቤቶች በተጨማሪ ቅንጡ መኪናዎች፣ የእርሻ መሣሪያዎች፣ በመቶ ሺዎች የሚገመት ገንዘብም ተጠቅሷል።

ቦና ሙጋቤ ከአባቷ እና ከእናቷ ግሬስ ጋር በሙጋቤ 92ኛ ዓመት ልደት በዓል ላይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ቦና ሙጋቤ ከአባቷ እና ከእናቷ ግሬስ ጋር በሙጋቤ 92ኛ ዓመት ልደት በዓል ላይ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሙጋቤ ቤተሰብ 21 ሰፋፊ እርሻዎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህ እርሻዎች የተያዙት ከአውሮፓውያኑ 2000 ወዲህ የነጮች እርሻዎች ለጥቁሮች ይመለሱ በተባለ ጊዜ ነው።

ነገር ግን ከነጮች የተወረሱ እርሻዎች አንድ እርሻ ለአንድ ሰው በሚል ሕግ ነበር የተላለፉት። የሙጋቤ ቤተሰብ እንዴት 21 ሰፋፊ እርሻዎችን እንደወሰደ ግልጽ አይደለም።

የቦና ሙጋቤ ባለቤት ካፔቲን ቺኮሬ ሃብት እና ንብረት እንካፈል ጥያቄን ከማቅረቡም ባሻገር ሦስት ልጆቻቸውን በጋራ እንዲያሳድጉ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ቺኮሬ እንደሚለው ንብረቶቹን በጋራ እና በተናጥል ነው ያፈሩት። አንዳንዶቹም ከፕሬዝዳንት ሙጋቤ በስጦታ እና በውርስ የተገኙ ናቸው።

ቺኮሬ እንደሚለው አሁን የሃብት እንካፈል ጥያቄ ያነሳባቸው ንብረቶች ባለቤቱ ቦና ሙጋቤ ካላት ንብረት ጋር ሲነጻጸር ባሕርን በጭልፋ የመውሰድ ያህል ነው።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የቀድሞ የሙጋቤ ቃል አቀባይ እና የአሁኑ የኤመርሰን ምናንጋግዋ ቢሮ ባልደረባ ጆርጅ ቻራምባ፣ የሙጋቤ ልጅ ቦና ሙጋቤ 21 እርሻዎች በስሟ አሉ የሚባለው ሐሰት ነው ሲሉ ዜናውን አስተባብለዋል።

“ሁሉም የእርሻ መሬቶች የመንግሥት ናቸው። ገበሬዎች በሊዝ ነው መሬት የሚወስዱት” ሲሉ በትዊተር ሰሌዳቸው አስፍርዋል።

ይህ በዋና ከተማዋ ሐራሬ እየታየ ያለው የፍቺ ሂደት መቼ እንዲመጠናቀቅ አልታወቀም።

የቦና ሙጋቤ እና የካፒቴን ቺኮሬ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት የተፈጸመው በፈረንጆቹ 2014 ሲሆን፣ በዚህ ድል ባለ ሠርግ ሥነ ሥርዓት በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ከመገኘታቸውም በላይ ሙሉ ሥነ ሥርዓቱ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ለሕዝብ በቀጥታ ተላልፏል።

ሙጋቤ ከነጻነት ጀምሮ የሙጥኝ ካሉት መንበር በአሁኑ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በመፈንቅለ መንግሥት ከተነሱ በኋላ ነበር በ2019 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

ሙጋቤ በተወለዱ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የተውት ኑዛዜ የለም። ሙጋቤ ከሴት ልጃቸው ከቦና ሙጋቤ ሌላ ሁለት ወንድ ልጆች እና አንድ የእንጀራ ልጅ ነበራቸው።

ሮበርት ሙጋቤ ዚምባብዌን የመሩት ለ37 ዓመት ነው።